Saturday, September 21, 2013

አራት ኪሎ መቃብር እየተናደ መንገድ ላይ የወዳደቁ አጽሞች አልተነሱም

አራት ኪሎ መቃብር እየተናደ መንገድ ላይ የወዳደቁ አጽሞች አልተነሱም


አዲስ አበባ አራት ኪሎ ከፓርላማ ጀርባ የሚገኘው የመቃብር ስፍራ አጥር በመፍረሱና ዛፎች በመውደቃችው፣ መቃብሮች እየተናዱ የሙታን አፅሞች ከሳጥን ወጥተው ሜዳ ላይ እንደወዳደቁ ሁለት ሳምንት አለፋቸው፡፡ አዲስ አበባ መስተዳድር እና የመቃብር ስፍራውን የሚያስተዳድረው ደብር በጉዳዩ ላይ እየተወዛገቡ ነው፡፡ በፓርላማ ጀርባ ባለወልድ ቤ/ክርስትያን ቅጥር ግቢ አጠገብ በሚገኘው መንገድ ጠዋትና ማታ የሚመላለሱት ወ/ሮ አምሳለ ከበደ፤ የግቢው አጥር ለመንገድ ስራ ከፈረሰ ከአምስት አመት በላይ እንደሆነው ገልፀው፣ ሁለት ዛፎቹ ስራቸው እየተንሸራተተ ሲወድቁ መቃብሮች እየተፈነቃቀሉ መንገድ ላይ ወድቀዋል ብለዋል፡፡ መንገዶች ላይ የወዳደቀ የሙታን አጽም እያየን ነው የምናልፈው ያሉት ወ/ሮ አምሳለ፤ ሦስት ሳምንት ሆኖታል፤ የጭንቅላት፣ የእግር፣ የእጅ አጽም ያለ ክብር ወዳድቆ ማየት ልብን ይነካል ብለዋል፡፡
ከፍ ብለው የሚገኙት መቃብሮችም ተፈነቃቅለው ለመውደቅ አፋፍ ላይ ደርሰዋል በማለት የተናገረችው ወ/ሪት ቤተልሄም፤ ህፃናት የሙታንን አጽምና ጭንቅላት በእግራቸው እየመቱ ሲራመዱ ያሳዝናል ብላለች፡፡ ቤተሰብ ለማስታወሻ ብሎ ያስገነባቸው ሀውልቶች እግረኛ መንገድ ላይ ወድቀው በማየታችን ለደብሩ ሃላፊዎች ብንናገርም ምንም መልስ አልሰጡንም ብላለች ወ/ሪት ቤተልሄም፡፡ ልጃቸውን ከትምህርት ቤት ሲመልሱ ያገኘናቸው አቶ ሚኪያስ ዳንኤል በዚሁ መንገድ አዘውትረው እንደሚጠቀሙ ገልፀው፤ ከፍ ብሎ ከሚገኘው የመቃብር ስፍራ አጽሞች ወደ መንገድ መውደቅ የጀመሩት ከሁለት ሳምንት በፊት ነው ብለዋል፡፡
የሰው ልጅ አጽም ክብር አጥቶ ሜዳ ላይ ወድቆ ሰናይ፣ በሞት የተለዩ ቤተሰቦቻችንን እያሰብን እንሸማቀቃለን ያሉት አቶ ሚኪያስ፤ የደብሩ አስተዳደር ለሙታኑ ቤተሰቦች በማሳወቅ የሙታኑን አጽም እንዲያነሱ ማድረግ ነበረበት፤ ካልሆነም አጽሞቹን ሰብስቦ በክብር አንድ ቦታ መቅበር አለበት ብለዋል፡፡ የደብሩ ፀሐፊ የዚህ ችግር ሪፖርት አልደረሰኝም ያሉ ሲሆን፤ የደብሩ ተቆጣጣሪ አባ አክሊሉ ገ/አምላክ በበኩላቸው፤ የአዲስ አበባ መስተዳድር ለመንገድ ስራ ግንቡን እንዳፈረሰ ጠቅሰው፣ በዝናብ አፈሩ እየተናደ አጽሞቹ እንደወደቁ ተናግረዋል፡፡ ግንቡን መልሶ የመገንባት አቅም የለንም ያሉት አባ አክሊሉ፤ የአዲስ አበባ መስተዳድር ያፈረሰውን ግንብ የመገንባት ግዴታ አለበት፤ እኛ የወደቁትን አጽሞች ለቅመን በአንድነት እንቀብራለን ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሲሳይ ወርቅነህ፤ መንገዱ ሲገነባ ለደብሩ ካሳ እንደተከፈለ ጠቅሰው፤ በአስፋልቱ በኩል ያለውን አጥር መገንባት ያልጀመርነው ስምንት ያልተነሱ መቃብሮች ስላሉ ነው ብለዋል፡፡ በመንገድ ስራ ምክንያት ሳይሆን በዛፎች መውደቅ ሳቢያ የተፈነቃቀሉ መቃብሮችና የፈረሱ ግንቦች የደብሩን አስተዳደር እንጂ እኛን የሚመለከቱ አይደሉም ያሉት አቶ ሲሳይ፤ ወደ ግንፍሌ በሚያወጣው መንገድ ላይ ሁለት ትልልቅ ዛፎች ቢወድቁም የደብሩ አስተዳደር እስካሁን አላነሳቸውም ብለዋል፡፡

No comments: