Wednesday, September 18, 2013

ከ380 ሺህ ብር በላይ ያጭበረበሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዳማ ዲስትሪክት ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ሞያሌ ላይ ተያዙ


አዲስ አበባ ፣ መስከረም 8 ፣ 2005 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባልታወቀ መንገድ ከ380 ሺህ ብር በላይ ይዞ ወደ ኬንያ ሲኮበልል የተያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዳማ ዲስትሪክት ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ሞያሌ ላይ ተይዞ በቁጥጥር ስር ዋለ።
ተሻለ ታደሰ የተባለው የቅርንጫፉ ስራ አስኪያጅ  እና ተስፉ አበበ የተባለው እና በንግድ ስራ የሚተዳደር ግብራአበሩ ናቸው በፌደራል የስነምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ህግ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት።
ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው አቶ ተሻለ ታደሰ ከርሱ ጋር ለተጠረጠረው ግብራአበር ተስፉ አበበ የሌለውን ገንዘብ በስሙ እንዲገባለት በማድረግ ለሌላ ቅርንጫፍ ሂሳቡን ያስተላልፍለታል።
አቶ ተስፉ አበበ በስራ አስኪያጁ የተዘዋወረለትን የ380 ሺህ ብር ቼክ በመቀበል መልሶ አስረክቦታል የሚል ነው በክሱ ላይ የተጠቀሰው።
የኮሚሽኑ ጥርጣሬ ገንዘቡ ዶርማንት አካውንት ማለትም አንዳንድ ደንበኞች ቆየት ላለ ግዜ ካላንቀሳቀሱት ሂሳብ ላይ በተጭበረበረ መንገድ ተገኝቷል የሚል ነው  ።
ባንኩ ያደረገው የኦዲት ስራ የሚያስረዳውም እንዲህ ባለ የግለሰቦቹ የማጭርበርበር ስራ 380 ሺህ ብር ሳይሆን ከ 1 ሚልየን ብር በላይ መመዝበሩም ተረጋግጧል።
የኮሚሽኑ የምርመራ ቡድን ባደረገው ክትትል የባንኩ ስራ አስኪያጅ መንዝሯል የተባለውን 1 ሺህ ዶላር ገደማ እንደያዘ ኬንያ ለማግባት ሲሞክር ነው ሞያሌ ላይ በቁጥጥር ስር የዋለው።
ግብራአበሩ አቶ ተስፉ አበበም በተመሳሳይ አዋሽ ላይ የተያዘ ሲሆን ፥ የምርመራ ቡድኑ በግለሰቦቹ ላይ ተጨማሪ ምርመራ ለማከናወን ከፌደራል ከፍተኛ ፍርድቤት ተረኛ ችሎት የ10 ቀን የምርመራ ግዜ ተፈቅዶለታል።

No comments: