Tuesday, September 24, 2013

መስቀል አደባባይ! የኢትዮጵያውያን ታህሪር?

መስቀል አደባባይ! የኢትዮጵያውያን ታህሪር?
------------------------------------------------------------------------------

ኢህአዴግ ድሮ ጀምሮ ከሚጠላው የአደባባይ ሰልፍ ራሱን አደባባዩን ወደመፍራት አፈግፍጓል፡፡ በተለይ መስቀል አደባባይ የኢትዮጵያው ታህሪር እንዳትሆን አብዛቶ ፈርቷል፡፡ ላለፉት ስምንት አመታት የሚከለከለው ራሱ ሰላማዊ ሰልፍ ነበር፡፡ ሰማያዊና አንድነት ከግንቦት ጀምሮ ያደረጓቸው ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ኢህአዴግ ሲከላከል የሰነበተው ቀዳሚ ጉዳይ ህዝብ በብዛት እንዳይሳተፍ ነው፡፡ ለዚህም ቅስቀሳ የሚያደርጉት ወጣቶች እስካሁንም ድረስ እያሰረ ቀጥሏል፡፡ መስሪያ ቤቶችም በካድዎች ትዕዛዝ ሰላማዊ ሰልፍ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያንን ከስራቸው እያበረሩ ነው፡፡

ኢህአዴግን ያስፈራው ሌላው ጉዳይ ግን ሰላማዊ ሰልፍ የሚካሄድበት አደባባይ ነው፡፡ ቅስቀሳ የሚያደርጉትን እያሰረም ቢሆን ሰላማዊ ሰልፎችን በጠባብ ጎዳናዎች ላይ ብቻ በመወሰን ጭንቀቱን ለማቅለል ሞክሯል፡፡ 97ት ላይ ክፉኛ የደነገጠበት መስቀል አደባባይ ለድጋፍ ሰልፍ እንጅ ለሰላማዊ ሰልፍ ክልክል ሆኗል፡፡ ሰማያዊ ወደ መስቀል አደባባይ ሲያመራ ሰልፉን ረግረጋማውና ፖሊስ ህዝብ እንዳይሳተፍ ለማጎር ምቹ የሆነው ጃን ሜዳ ላይ እንዲያደርግ ‹‹አማራጭ›› አቅርቦ ነበር፡፡ ሰማያዊ መስቀል አደባባይን ኢህአዴግ ባዘጋጀለት ጃን ሜዳ ከመቀየር ይልቅ መስቀል አደባባይ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ የሚደረግበት ቀን ሩቅ እንዳልሆነ በማሰብ በክብር ወደ ቢሮው ተመልሷል፡፡

ሰላማዊ ሰልፍ የሚያስበረግገው ‹‹አብዮታዊ›› ፓርቲ አሁንም በርካታ ህዝብ እንዳይሳተፍ ቅስቀሳ የሚያደርጉትን የአንድነትን ወጣቶች ማሰሩን ቀጥሏል፡፡ ኢህአዴግ እንደፈለገ የሚጨፍርበትን አደባባይ ‹‹ግንባታ እየተካሄደበት ነው›› በሚል ለሰልፍ እንደማይፈቀድ መንቦጅቦጁን በግልጽ አሳይቷል፡፡ መቼም በሚቀጥለው አርብ የመስቀል በዓልን ‹‹ግንባታ እየተካሄደ ስለሆነ›› ልክ እንደ ጥምቀት ጃን ሜዳ አድርጉት አይልም፡፡

በእርግጥ ጉዳዩ እራሱን ነው አንድ እርምጃ እያፈገፈገበት ወዳለው ገደል የሚገፋው፡፡ ስለሆነው ለኢህአዴግ የመስቀል አደባባዩ ግንባታ የሚደናቀፈው ህዝብ ስለ ነጻነት ጮኸቱን ሲያሰማ ነው፡፡ ኢህአዴግ አምባገነንነቱን ከመቼውም በላይ እየገነባ ነው፡፡ ይህን አብዮታዊ ግንባታ ደግሞ የሚደረምሰው የወጣቶች ድምጽ መሆኑን ከግብጽ ተምሯል፡፡ የኢትዮጵያውያን ታህሪር ደግሞ መስቀል አደባባይ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ ግብጾቹ 97 ላይ ሞክረው ተጨናግፎባቸዋል፡፡ ያኔ ኢህአዴግ ሰልፍን በጊዜያዊ አዋጅ፣ በኋላም በቋሚ አዋጅ ለስምንት አመት በኋላ ለማፈን ችሎ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ስለ ህግና አዋጅ እያወራ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ፈቅዶም ቢሆን ባልተጻፈ ህግ ቀስቃሾቹን እያሰረ ነው፡፡ አደባባዮችን ለመልቀቅ ማንገራገሩን ቀጥሏል፡፡ ልክ እንደሙባረክ!

መስቀል አደባባይ ሆይ! መቼ ይሆን ኢህአዴግ እንደሚፈራው የኢትዮጵያውያን ታህሪር የምትሆኝው?

No comments: