ወገን በቃ እንበል
አምባገነኖች ወደ ስልጣን የሚመጡት የህዝብን ቋንቋ እየተናገሩ ነው፡፡ የአገርንና የህዝብን ችግር መነሻ አድርገው የህዝብ ተቆርቋሪ ለህዝብ መብትና ጥቅም የተቆጨ መስለው ይጮሐሉ፡፡ የህዝብን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚታገሉ ህዝብ ከጐናቸው እንዲቆም ይለፍፋሉ፡፡ ሥልጣኑን ከያዙ በኋላ ህዝቡን ይረሱታል፡፡ ተገልብጠው ህዝብን ይሳደባሉ፡፡ በመሳደብ ሳያቆሙ ያስራሉ ይደበድባሉ ይገላሉ፡፡ የአገርንና የህዝብን ሀብት ለግላቸው ይዘርፋሉ ያዘርፋሉ፡፡ በተለያየ ዘመን በዓለማችን ላይ የተነሱት አምባገነኖች ያስተማሩን ይህንኑ ነው፡፡ በአገራችን የተንሰራፋው የኢህአዴግ አምባገነናዊ መንግስትም እየፈፀመ ያለው ይህንኑ ነው፡፡ አርቴፊሻል የዴሞክራሲያዊ ተቋማትን በማቋቋም እጅግ አደገኛ የሆኑ የአፈናና የሰብአዊ መብት ረገጣ ተቋማትን ሲገነባ ቆይቷል፡፡ የህዝብን ሀብት እየነጠቀ ወደ ተለያዩ የኢህአዴግ ኩባንያዎች ለኢህአዴግ አባላት ያድላል፡፡ ዜጐችን ከመኖሪያና ከሥራቸው እያፈናቀለ ለረሃብ ለቤት ችግርና ለእርዛት ዳርጓል፡፡ ህገ መንግስቱን ተማምነው ሥርዓቱን በህጋዊና ሠላማዊ መንገድ የሚታገሉ የሠላም አርበኛና ነፃ ጋዜጠኞች እጣ ፈንታቸው በፈጠራ ክስና በማስገደድና በማስፈራራት ምስክሮች የሚሰጡትን ቃል እያየን ነው፡፡አምባገነኖች የሚያደምጡት ራሳቸውን ነው፡፡ ለአገርና ለህዝብ የሚጐዳ ተግባራቸው ሁሉ ለሥልጣናቸውና ሀብት ለመሰብሰብ እስከ ጠቀማቸው ድረስ ቅዱስ ነው፡፡ ማሰርም፣ መግደልም፣ ማስራብ እና ቤት ማሳጣት እርዛት መፍጠር ለአምባገነኖች ምናቸውም አይደለም፡፡ የህዝብ እንባና ሮሮ አያስበረግጋቸውም፡፡ እንዲያውም የበለጠ ልባቸውን ያደነድናቸዋል፡፡ ትናንት የሚናገሩት የህዝብ ቃል ሥልጣን ከያዙ በኋላ አያውቁትም፡፡ ኢዲያሚን ዳዳ፣ ቦካሳ፣ ጋዳፊ ያሳዩን ይህንኑ ነው፡ ተቃዋሚዎቻቸውን ተቺዎቻቸውን አስረዋል፣ ገለዋል፡፡ ህዝብን ይሳደባሉ፡፡ እነሱ ያሉትን ያልተቀበሉ ሁሉ በእነሱ ሚዛን ወንጀለኞች ናቸው የኢህአዴግ መሪዎችም የሚፈጽሙት ይህንኑ ነው፡፡ የኢህአዴግ ሠላም ህሊናን ለኢህአዴግ ዘረኛ አስተዳደር፣ ለኢህአዴግ ሙስና አስተዳደር፤ ለኢህአዴግ ኢ-ዴሞክራሲዊና ኢ-ሰብአዊ አስተዳደር፤ ለኢህአዴግ ፍርደገምድል ዳኝነት፣ ለኢህአዴግ ተቋማዊ ዝርፊያ አሚን ብሎ መገዛት ነው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ህጋዊና ሠላማዊ ሰው ነው ለመባል የኢህአዴግን ወንጀል ልማት አድርጐ መቀበል ነው፡፡ ኢህአዴግ የህዝብ ጥያቄን ሁሉ ጊዜ በብልጣብልጥነትና በአምባገነናዊ የአፈና ሥልት ማለፍ ይፈልጋል፡፡ ግን እስከመቼ? ስንት ዓመት ዜጐችን ማታለል ይፈልጋል፡፡ 21 ዓመት ሙሉ በጠብመንጃ ተገዝተናል፣ 21 ዓመት ሙሉ በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ነፍዘናል፡፡ ይህ አልበቃ ብሏቸው ሌላ 40 ዓመት እንገዛችኋለን እያሉን ነው፡፡ ምኞታቸው ቀላል አይደለም፡፡ ዴሞክራሲ ህገ መንግስት እነሱ ዘንድ ትርጉም የሚሰጣቸው ለመድረክ ማድመቂያ ለወንበራቸው ማስጠበቂያ ብቻ ነው፡ ፡ ሥልጣናቸው የመጣው ከኮሮጆ እንዳልነበረ ሁሉ ወደ ፊትም ከኮሮጆ እንዳንጠብቅ እየነገሩን ነው፡፡ መፍትሔው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ መላውን የአገሪቱን ህብረተሰብ ነፃነቱ እንዲያስከብር ማደራጀት ነው፡፡ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በህዝብ ትግል ይከበራል፡፡
ኢትዮጲያ ለዘላለም ትኑር
No comments:
Post a Comment