በቋንቋ፡ በዘርና ሃይማኖት ተለይቶ የመደራጀት ጦስ
በቋንቋና በዘር ተለይቶ መደራጀት በጣም አደገኛ ነው፡ ምክንያቱም እኛና እነሱ
ወደሚለው የመለያየት፤ የመጠራጠር እንዲያ ሲልም የመጠላላት አባዜ ተከትሎ
ስለሚመጣ ነው። ይህ ደግሞ ወያኔ አስለቶ ሰርቶበት አሁን ላለንበት የብሄራዊ
ውርደት አብቆቶናል።ከዚህ አልፎ ለልዩነት ሃይማኖት ሲጨመርበት ደግሞ የመርዝነቱ
መጠን በጣም የጠነከረ ይሆንና አብሮ መኖር ሳይሆን መጠፋፋትን ያስመኛል።
የራስንም ባህልና ክብር ያስረሳል፡ ወደ ገደልም ይዞ ይገባል።
ለምሳሌ፡ እኔ እንደማውቀው ወያኔ ቋንቋን መሰረት አድርጎ እንደ አንባሻ ሳይሸነሽነን፡
አንድ መጤ ወይም ላካባቢው እንግዳ የሆነ ሰው ባሌ ወይም አርሲ ቢሰደድና ጎጆ
ቀልሶ ቢኖር፤ አጋጣሚ እንግዳው ቤተሰብ ህጻን ልጅ ካላቸው፡ ለህጻኗ ወተት ተብሎ
ጥገት ላም ከነጥጃዋ ለእንግዶቹ ይሰጥ እንደነበር አውቃለሁ። ይህን ሲያረጉ ግን
ቋንቋውን፤ ሃይማኖቱን ወይም የመጣበትን አካባቢ መሰረት ያደረገ ሳይሆን ሰው
በመሆኑ ብቻ ነበር። እኛ ብዙ ነን ቁጥራቸው ያነሰውን እናጥቃ የሚል ባህል ሳይሆን፤
እንርዳው፡ እንንከባከበው የሚል ባህል ነበር እኔ የማውቀው፡ ያ ባህል አሁንም
ይኖራል ብየ አምናለሁ፡ ይኖራልም።
አንዳንድ ግለሰቦች እንኳን ለሰው ልጅ ለእንሰሳ እንኳ ሊጠቀሙበት የማይገባና
የሚጠገንን ቃላቶችን በጓዳ በሃሜታ ሳይሆን ባደባባይ በስብሰባ ሲናገሩ መስማት
እንደ ሃገር፤ እንደ ዜጋ በጣም ያሳፍራል፡ ያውሬን ባህርይ የተላበሱ ስለሚያሰኝ
ለመናገርም በጣም አስቸጋሪና አስደንጋጭ ነው፡:እንደዚህ አይነት ሰዎች ከነሱ የተለየ
ቋንቋ ተናጋሪዎች፤ ከነሱ የተለየ እምነት ተከታዮች ጋር አብሮ የመኖር ፍላጎትም
ትዕግስትም እንደሌላቸው በግልጽ ያሳያል። የሚናገሩት ሊያደርጉ የሚወዱትንና
የሚመኙትን ነው፡ የሚወዱትን ለማድርግ የሚያግዳቸው ደግሞ ያቅም ጉዳይ ብቻ
ነው የሚሆነው፡ ስለዚህ እንደነዚህ ያሉ ያውሬ ስብዕና የተላበሱ ሰዎችን ከማህበረሰቡ
ማግለልና በጥንቃቄ መከታተል ያስፈልጋል። ማንም ሰው ለሚናገረው ነገር ሃላፊነት
መውሰድ እንዳለበትም ሊታወቅ የግድ ነው።
ድል ለጭቁኑ ህዝብ !!!
No comments:
Post a Comment