መጨረሻ የሌለው መጨረሻ
የምርጫ “ውጤት” እጅግ ዘላቂ ተጽእኖ የሚፈጥርበት ሌላው መስክ የተቃዋሚዎች ጎራ ነው፤ በአጠቃላይም የተቃውሞ ፖለቲካ። ኢሕአዴግ እጅግ በጠበበው ሜዳ አብረውት “ለመጫወት” የፈቀዱትን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ቡድኖች እንኳን ታግሶ የሚያጫውትበት አነስተኛ ፈቃድ እንደሌለው በማያሻማ መልክ አሳይቷል። የቱንም ያህል በቃላት ጋጋታ ለመደበቅ ቢሞክር ከእርሱ ውጭ ያሉ ፍላጎቶችን ሁሉ ዲበአካላዊ ጠላት (ኤግሲቴንሺያል ኢነሚ) አድሮጎ መመልከቱን አጠናክሮ ቀጥሎበታል። እጅግ በተወሰነ አቅም በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎችን እና ገለልተኛ ድምጾችን ጥሪ ማስተናገድ ቀርቶ መስማት እንኳን እንዳለበት ከማያምንበት ደረጃ እየደረሰ ይመስላል። በአጭሩ ፖለቲካዊ ማን አህሎኝነት (ፖለቲካል አሮጋንስ) የፖለቲካው መርህ ሆኗል።
ይህን በመሠረታዊ ተፈጥሮው ፍጹም ጸረ ዴሞክራሲያዊ የሆነ፣ ነገር ግን በቃላት እና በሰነድ ስሞች እየተሞካሸ የሚቀርብ አመለካከት እና አሠራር ለማስቆም የሚችል የተገኘ አይመስልም። በአሁን ይዞታው ኢሕአዴግ ማድረግ የማይችለው አንዳችም ነገር የለም። ይህም በአብዛኛው ሕዝብ እና አገር ውስጥ በሚገኙ የፖለቲካ ቡድኖች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ የመጣ ነው። የዴሞክራሲ አንዱ ምናልባትም ዋናው ግቡ ሕዝብን ከመንግሥት መጠበቅ ነው። የመንግሥት ሥልጣን የያዘ ፓርቲ/ቡድን የፈለገውን እንዳያደርግ ልጓም ማበጀት አንዱ የዴሞክራሲ ጸጋ ነው። አሁን አገር ውስጥ በሚገኙት ተቃዋሚዎች መካከል ያለው አንዱ የስትራቴጂ ልዩነት ምንጩ ይህ የኢህአዴግ “ሁሉን ቻይነትና ሁሉን አዋቂነት” ባህርይ ነው። አንዳንዶቹ “ኢሕአዴግ መጠነ ሰፊ ጉልበት ስለፈጠረ አሁን እርሱን በማንኛውም መንገድ መገዳደር ጥፋቱ ለአገር ሊተርፍ ይችላል” በሚል እምነት እርሱ በፈቀደው መጠን እየተጠቀሙ ትግላቸውን ማካሄድ መርጠዋል።
የኢሕአዴግ ማንአለብኝነት እነዚህን ቡድኖች በእጅጉ የሚያዳክም ብቻ ሳይሆን ተስፋ ለማስቆረጥም አቅም ያለው ነው። የኢሕአዴግ ሰዎች ለዘብተኛ ተቃዋሚዎችን ማግኘት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ እንኳን ከማያስተውሉበት ደረጃ ደርሰዋል። ይህም አንዳዶቹን ተቃዋሚዎች ወደ ጠርዝ ሊገፋቸው ይችላል። ፍላጎታቸውን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማቅረብ የሞከሩ ዜጎች እና ቡድኖች በዘንድሮው ዓይነት ሁኔታ ወደ ጠርዝ በተገፉ መጠን ማኅበረሰባዊ ተቃርኖ እየጦዘ መሄዱ የማይቀር ነው። በእርግጥ ኢሕአዴግ ከዚህ መሰሉ መካረር ጥቅም ሊያገኝ እንደሚችል ማስላቱ አይቀርም። ሕዝቡን በተለያዩ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች የተካረረ አቋም እንዲይዝ በመግፋት ብቸኛው “አሸማጋይ” ሆኖ ለመውጣት መፈለጉ የሚጠረጠር አይደለም። ክፋቱ ግን፤ ይህን መሰሉ መካረር ራሱን ኢሕአዴግን ብቻ ሳይሆን አገሪቱንም ሊበላት የሚችል መሆኑ ነው።
ኢሕአዴግ በባለፈው ምርጫ ያሳየው አቋም ተቃዋሚዎች ስለሚቀጥለው ምርጫ እንኳን ተስፋ እንዳያደርጉ የሚያስገድድ ነው።የተፈለገው ውጤትም ይህ ይመስላል። የሚቀጥለው ምርጫ እንደ ባለፈው አገራዊ ቀልድ እንደማይሆን ማስተማመኛ የሌለው ተቃዋሚ ፓርቲና አባሎቹ ግን ጊዜያቸውን በከንቱ ማባከን አይፈልጉም።
ከአንድናት ኢትዮጵያ ብሎግ
ኢትዮጵያ
በክብር ለዘላለም ትኑር!
No comments:
Post a Comment