የመንግስትን የሃይማኖት ጣልቃ ገብነት የሚያሳይ ተጨማሪ ሰነድ ተገኘ
የመንግስትን የሃይማኖት ጣልቃ ገብነት የሚገልጹ ተጨማሪ ሰነዶች በእጃችን ገቡ፡፡ ሰነዶቹ በ2004 መጀመሪያ አካባቢ ሲደረጉ የነበሩ የአሕባሽ ስልጠናዎች ዋነኛ አስተባባሪ እና አዘጋጅ መንግስት መሆኑን ያሳያሉ፡፡ በሰነዱ ላይ እንደተመለከተው በወቅቱ ይሰጥ ነበረው ስልጠና በመንግስት ሚዲያዎች እንደተገለጸው በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት አዘጋጅነት ብቻ ሳይሆን በመንግስትም ጭምር የተዘጋጀ እንደነበር ያሳያል፡፡ ‹‹የኢ/እ/ጉ/ጠ/ም/ቤት (መጅሊስ) ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የአህለሱናንና የሃይማኖት (የዲን) አስተምህሮት በተቀላጠፈ ሁኔታና ፍጥነት ለማካሄድ እንዲቻል የ200 አሰልጣኞች ስልጠና ለአንድ ወር (30) ለማካሄድ የሚያስፈልግ ዝርዝር የወጪ ግምት ለመጠቆም ተዘጋጅቶ የቀረበ ፕሮፖዛል›› በሚል ርእስ በቀረበው ይኽው ሰነድ ላይ፤ መንፈሳዊ የተባለው የአህለ ሱንና ስልጠና በመንግስት አዘጋጅነት የተካሄደ መሆኑን ያሳያል፡፡
መንግስት ከአሕባሽ ስልጠና ጋር በተያያዘ እጁ እንደሌለበትና የድርጊቱ ባለቤት መጅሊሱ እና ኡለማ ምክር ቤቱ መሆናቸውን ደጋግሞ ሲገልጽ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ሟች ጠቅላይ ሚኒስትርም ይህንኑ እውነታ ክደው በፓርላማ ንግግር ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ ሆኖም በተለያዩ ጊዜያት ከመንግስት ባለስልጣናትና ከመጅሊሱ ቢሮዎች አፈትልከው የወጡ የሰነድ ማስረጃዎች መንግስት ነውጠኛውን የአሕባሽ አስተምህሮ በግድ በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ ለመጫን ሐሳብ ከማመንጨትና ጥናት ከማድረግ አንስቶ እስከትግበራው ድረስ ዋነኛው ተዋናይ እንደሆነ አሳይተዋል፡፡ በቪዲዮ እና በድምጽ የተገኙ ማስረጃዎችም እውነታውን በዛ መልኩ ሲገልጡ ቆይተዋል፡፡
ይኸው አሁን የተገኘውም ሰነድ ከዚህ በፊት በስፋት ህብረተሰቡ የሚያውቀውን እውነት የሚያጠናክርና መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ መግባት የሚከለክለውን ሕገ መንግስት በመጣረስ በሃይማኖት ውስጥ መጤ አስትምህሮ እንዲነግስና ሙስሊም ዜጎችም በዚህ ምክንያት ለችግር እንዲዳረጉ ጥረት እያደረገ መቆየቱን አመላካች ነው፡፡ ለተባሉት ስልጠናዎች የፋይናንስ ወጪ የሚያደርገው መንግስት መሆኑንና ለመጅሊሱ ገቢ ተደርጎለትም በመጅሊሱ በኩል ወጪ እንደሚደረግ ከዚህ በፊት የወጡ ተመሳሳይ ሰነዶች ማመላከታቸው አይዘነጋም፡፡ በተጨማሪም ስልጠናው ለሚካሄድነትና የመንግስት ተቋም ለሆነው ኢትዮጵያ ፖሊስ ኢንስቲትዩት ለዝግጅቱ ማሳኪያ የሚረዳ ገንዘብ ለኢንስቲትዩቱ ገቢ እንዲሆን የተጠየቀበትና ገቢ የሆነባቸውም ሰነዶች በእጃችን ገብተዋል፡፡
No comments:
Post a Comment