Wednesday, July 24, 2013

ወያኔን ኃይ ባይ ይጥፋ? "አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ "


ወያኔን  ኃይ ባይ ይጥፋ?  "አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ "

የኢህአዴግ አስተሳሰብ አያሳምንምና አያስከብርም እንጂ በጣም ግልጽ ነው።  እንደ ኢህአዴግ ፓርቲ አስተሳሰብ እንደ እነ አንዱዓለም አራጌ፣ እስክንድር ነጋ፣ ዘሪሁን ታዬ፣ በቀለ ገርባ፣ ኦልባና ለሊሳ፣ ርዕዮት ዓለሙ የመሳሰሉ እስረኞች የፖለቲካ እስረኞች አደሉም። በኢህአዴግ አስተሳሰብና አካሄድ መሠረት እነዚህ ሰዎች በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው፣ ተከስሰው፣ በማስረጃ “ተረጋግጦባቸው”፣ ፍርድ ቤት የፈረደባቸው “ወንጀለኞች” ናቸው። ይህ የተለመደ የኢህአዴግ ደረቅ መንገድ ነው። የቀረበባቸው ክስ የፈጠራ ክስ ነው። የቀረበባቸው ማስረጃ አሳማኝ አይደለም። የፈረደባቸው ፍርድ ቤት ነፃና ገለልተኛ ሊባል አይችልም። የክሱ ዓላማ ለነፃነት፣ ለፍትሕና ለዲሞክራሲ የሚታገሉ የፖለቲካ ጀግኖችን በሕግ ሽፋን ለማጥቃትና ሕዝብን ለማሸማቀቅ እንጂ ሕግን ለማስከበርና የሃገር ደህንነትን ለመጠበቅ አይደለም። በዚህ ሁኔታ የታሰሩ ዜጎች የፖለቲካና የህሊና እስረኞች እንጂ ወንጀለኞች አይደሉም። የፖለቲካና የህሊና እስረኛ ሆነውማ የሠለጠነውና ለፍትሕ፣ ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አክብሮት ያለው ዓለም እየመሰከረላቸው ነው። ብዙዎቹንም እየሸለማቸው ነው።

አጼ በጉልበቱ ሆነውና ሃይ የሚላቸው ኃይል ጠፍቶ አሊያም አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ ሆኖ ሕዝብ ሀሳቡን በነፃነት የመግለጽና መረጃ በነፃነት የማግኘት መብቱ ተረግጦ ይነጋል፣ ይመሻል።
ኢህአዴግ ታሪካዊ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው። ሁለት አማራጮች አሉት። አንደኛው አማራጭ   ትክክል መንገድ ነው በሚል (የተሳሳተ) እምነት “የመለስን ራዕይ እውን ማድረግ” በሚል መፈክር የአንድ አምባገነን አውራ ፓርቲ ሥርዓትን በተለመደው የአፈናና የጭቆና መንገድ እንዲቀጥል ማድረግ ነው። ይህን ማድረግ ደግሞ እውነተኛ የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያውያን ህልም ሆኖ እንዲቀር ማድረግ፥ በቁሳዊ ልማትና በሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ የማይታይ የዕድገት ፕሮፓጋንዳ የሕዝብን አዕምሮ አደንዝዞ መግዛት፣ ሙስና እየተስፋፋ ሄዶ በሌሎች አንዳንድ አገሮች እንደሚታየው መቆጣጠር እማይቻልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ መፍቀድ፣ በተዛባ የሀብት ክፍፍል ሥርዓት ጥቂት ሀብታሞች ከሥርዓቱ ጋር ለጋራ ጥቅም በመሻረክ ይበልጥ ሀብታሞች እየሆኑ እንዲሄዱ፣ ብዙሃኑ ድሆች ደግሞ በሥራ አጥነትና በኑሮ ውድነት እየተደቆሱና የባሰ ድሃ እየሆኑ እንዲሄዱ የሚያደርግ ሁኔታ መፍጠር፣ ወጣቱ ትውልድ ጥራት ያለው ትምህርት ለማግኘት ካለመቻሉም በላይ ሠርቶ የማደር ተስፋው እየመነመነ በመሄዱ በሀገሩ ተስፋ ቆርጦ የሚሰደድበትና ለበረሃና ለባህር ላይ ሞት፣ ከዚህ አደጋ ከተረፈም ለውርደትና ለስቃይ ህይወት የሚዳረግበትን ሁኔታ ማስቀጠል ማለት ነው። በአጭሩ፣ ቀደም ሲል እንደተገለጸው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከድህነትና ከኋላ ቀርነት የመላቀቅ፣ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመመራትና በነፃነት፣ በሠላምና በአንድነት የክብር ኑሮ የመኖር ተስፋው እየራቀ ይሄዳል ማለት ነው
እስቲ ልብ በሉ፣ ተቃዋሚዎች ምናቸው ያስፈራል? ደረትና ግንባር የሚመታ አነጣጥሮ ተኳሽ የላቸው፣ ሰው አይገድሉ፣ ወህኒ ቤት የላቸው አያስሩ፣ በፈጠራ ክስ በንግድ ድርጅት ላይ ወገብ የሚሰብር ግብር አይጭኑ ወይም እንዲታሸግና እንዲዘጋ አያደርጉ ወይም ፈቃድ አናድስም አይሉ፣ አያጉላሉ። አባቶቻችን “የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር” ይላሉ። ተቃዋሚዎች ቢያስፈሩ፣ የሚያስፈሩት ኢህአዴግን ነበር። ለዚያውም ግን “ኢጎኣቸው” በያሉበት ቸክሎ ይዟቸው ከታሪክ መማርና መተባበር አቅቷቸው ኢህአዴግ አውራ ፓርቲ ነኝ ብሎ ብቻውን እንዲያቅራራ ሜዳውን ትተውለታል።
ሕዝብም እየሰማ ዝም አለ፣ ኢህአዴግም እያወቀ እንደልቡ ያለውን አለ። በመሀል ግልጽነት፣ ቀጥተኝነት፣ ቅንነትና ሀቀኝነት መስዋዕት ሆኑ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨረቃን ከሰማይ አውርዱልን እያለ አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ እያለ ያለው ግልጽነትን፣ ቀጥተኝነትን፣ ቅንነትንና ሀቀኝነትን አውርዱልን ነው። ዴሞክራሲን አውርዱልን ነው። ቁሳዊ ልማት ብቻውን አይበቃም፣ ሰብአዊና መንፈሳዊ ልማትንም አውርዱልን ነው። አሸዋና ስሚንቶ ከኮረት ጋር ቀላቅለን፣ ማጠናከሪያ ብረት አክለን ግድብ ገደብንልህ፣ ፎቅ ሠራንልህ፣ መንገድ ዘረጋንልህ፣ ትምህርት ቤቶች፣ ክሊኒኮች፣ ኮንዶሚኒየም፣ ወዘተ ሠራንልህ፣... ከዚህ የበለጠ ምን ትፈልጋለህ በሚል የ24 ሰዓትና የ7 ቀን ፕሮፓጋንዳ አታሰልቹን ነው። እነዚህ ነገሮች ጥሩ ነገሮች ቢሆኑም ምንም ያህል ይሁኑ ብቻቸውን በቂ አይደሉም ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚለው ከቁሳዊ ልማቱ ጎን ለጎን፣ ነገ ሳይሆን ዛሬ ነፃነትን፣ የኢትዮጵያዊነት ክብርን፣ እኩልዴሞክራሲያዊ ከዘር የጸዳ ሥርዓትን፣ ፍትሐዊነትን፣ የሕግ የበላይነትን፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫን፣ የሰብአዊ መብቶች መከበርን... እንፈልጋለን ነው። እነዚህ ሰብአዊ ፍጡራንና የኢትዮጵያ ዜጎች በመሆናችን ብቻ የምጎናጸፋቸው በረከቶች የሚገኙት ትክክለኛ መንገድ በሆነው የግልጽነት፣ የቀጥተኝነት፣ የቅንነትና የሀቀኝነት መሥመር ሲኬድ ብቻ ነው።
ከአንድናት ኢትዮጵያ ብሎግ

ኢትዮጵያ ክብር ለዘላለም ትኑር!

No comments: