Monday, July 22, 2013

ቤተ መንግስቱ ፕሬዘዳንቱን አይመግብም ?

         ቤተ መንግስቱ ፕሬዘዳንቱን አይመግብም ?
የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች ማህበር ውስጥ መፈጸሙ ስለ ተነገረለት ከፍተኛ ሙስና እና ተጠርጣሪዎቹ የማህበሩን ፕሬዘዳንት ጨምሮ በክተኛው ፍርድ ቤት የዋስ መብታቸው ተጠብቆላቸው ጉዳያቸውን በውጪ እንዲከታተሉ መደረጋቸው የመነጋገሪያ ርዕስ ለመሆን በቅቷል፡፡
የማህበሩ የበላይ ጠባቂ የሆኑት ፕሬዘዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የተከሳሾቹ የክስ ሂደት ተቋርጦ በነጻ እንዲሰናበቱ መጠየቃቸው በስማችን ሲነገድብን ቆይቷል በማለት አቤቱታ ሲያቀርቡ የነበሩ የማህበሩን አባላት አስቆጥቷል፡፡እነዚህ አንጋፋ አባላትና አርበኞች ለፍኖተ ነጻነት በማስረጃ ባቀረቡት ደረሰኝ ከማህበሩ ገንዘብ ወጪ እየተደረገ ለፕሬዘዳንቱ በስጦታ መልክ በግ፣ሙሉ ሽንጥ ስጋና ጠርሙስ ችቫዝ መጠጥ ወደ ቤተ መንግስት ይገባላቸው እንደነበር በማጋለጥ ‹‹ምናልባት ፕሬዘዳንቱ ይህንን አቋም የያዙት የጥቅም ሽ ርክና ስለነበራቸው ይሆናል፡፡››ይላሉ፡፡
በ30/08/2003 ዓ.ም በሻለቃ ደጀኔ መሸሻ ፊርማ ለማኅበሩ ገንዘብ ያዥ አቶ አስማማው አበበ የተጻፈ የይከፈል ደብዳቤ ‹‹ለክቡር ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ስለ ተገዛ በደረሰኙ መሰረት ተተክቶ ወጪ የሆነ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰፈረበት አንድ ገጽ ደብዳቤ ግዢው አንድ የበግ ሙክት መሆኑንና ዋጋውም 1500 መሆኑን ይገልጻል፡፡
በ27/08/2001ማህተሙ የማይነበብ የሽያጭ ደረሰኝ እንደተከፈለበት በማተት ግዢው የተፈጸመው በጥንታዊ ኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር መሆኑን በመጠቆም የተገዛው ‹‹ሙሉ ሽንጥ ስጋ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ሙሉ ሽንጥ ስጋውን ለመግዛት ማህበሩ 2800 ብር ወጪ አድርጓል፡፡ይህ ስጋ የማህበሩ አባላት ሰብሰብ ብለው እንዲመገቡት የተሸመተ ከመሰልዎ ተሳስተዋል፡፡ምክንያቱን ለመዘርዘር የሰፈረው ማብራሪያ‹‹ለክቡር ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ለመስጠት ስለ ተገዛ በደረሰኙ መሰረት ወጪ የሆነ ››ይላል፡፡
ከጸጋዬ ብርመካ ግሮሰሪ በ600 ብር የተሸመተ ጠርሙስ ችቫዝ ለማን እንደተሸመተ የሚገልጽ ማብራሪያ ባይኖረውም አርበኞቹ መጠጡም ቤተ መንግስት ውስጥ ለሚገኙት መቶ አለቃ ግርማ መግባቱን ያወሳሉ፡፡
የማህበሩ አባላት በወር በጡረታ መልክ ከምትሰጣቸው 150 ብር ላይ ለአባይ ግድብ አዋጡ እየተባሉ ከእጅ ወደ አፍ ከሆነው ኑሯቸው እየተቆረጠ ሲታመሙ የሚታከሙበት እያጡ በቀላል በሽታ ጭምር ለሞት እየተዳረጉ የማህበሩ ፕሬዘዳንትና ጥቂት አጋሮቻቸው እንዲህ አይነት በደል መፈጸማቸው እንዳስገረማቸው ፍኖተ ነጻነት ያነጋገረቻቸው ሰዎች ይገልጻሉ፡፡
ፕሬዘዳንት ግርማ ከማህበሩ የሚመጣላቸውን ሽንጥ ስጋና ሙክት በግ በአንድ አጋጣሚ እንኳን ሳይመልሱ አሁን ሰዎቹ ለክስ ሲቀርቡ ለምን ይነካሉ ማለታቸውም የማህበሩን አባላት አሳዝኗል፡፡
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉና እድሜ የተጫጫናቸው የማህበሩ አንድ አባል ‹‹ቤተ መንግስቱ ፕሬዘዳንቱን አይመግብም ወይ ብላችሁ ጠይቁልን ብለዋል፡፡

No comments: