Wednesday, June 1, 2016

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚዲያ አዋጅን በዚህ ሳምንት እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል

·         የብሮድካስት ኔትወርክ አስተዳደር የተባለ የልማት ድርጅት ይቋቋማል

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የብሮድካስት ኔትወርክ አስተዳደር የተባለ የልማት ድርጅት የሚያቋቁመውን ረቂቅ ‹‹የሚዲያ አዋጅ›› እንደሚያፀድቅ ምንጮች ጠቆሙ፡፡
በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚዲያ አዋጁ በዚህ ሳምንት ከፀደቀ በኋላ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ፓርላማው ለዕረፍት ከመበተኑ በፊት እንዲያፀድቀው እንደሚላክለትም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ረቂቅ የሚዲያ አዋጁ በአገሪቱ የሚዲያ አገልግሎት ዘርፍ ከሚታየው ፈጣን የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር አብሮ የሚጓዝ ጥራቱን የጠበቀ የብሮድካስት አገልግሎት ማስፋፋትን ዓላማው ያደረገ ነው፡፡
ረቂቁ ‹‹ሚዲያ›› ለሚለው ቃል የብሮድካስት አገልግሎትን፣ በየጊዜው የሚወጡ ኅትመቶችን እንዲሁም በኢንተርኔት፣ በተንቀሳቃሽ ስልክ ወይም በምሥል የመረጃ መረብ አማካይነት የሚቀርብ የፕሮግራም ሥርጭትና ይዘትን ያካትታል በማለት ይተረጉመዋል፡፡
በረቂቁ መሠረት ሁለት ዓይነት የብሮድካስት ፈቃድ ዓይነቶች የሚሰጡ ሲሆን፣ እነሱም የብሮድካስት ኔትወርክ አስተዳደር ፈቃድና የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ ናቸው፡፡
የብሮድካስት አገልግሎት የፈቃድ ዓይነቶች ይዘት ለሚያቀርቡ የሕዝብ፣ የንግድና የማኅበረሰብ ሬዲዮ ወይም ቴሌቪዥን ብሮድካስት የሚሰጥ የፈቃድ ዓይነት ነው፡፡
የብሮድካስት አስተዳደር ፈቃድ የሚሰጠው ግን በሕግ ለሚቋቋም የመንግሥት የልማት ድርጅት ሲሆን፣ ድርጅቱም የጋራ ብሮድካስት ኔትወርክ የማቋቋምና የማስተዳደር እንዲሁም የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ ያላቸው የሚያቀርቡትን ይዘት የማሠራጨት ኃላፊነት እንደሚኖረውም ያስረዳል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚገኙ የግልም ሆነ የመንግሥት የሬዲዮ ጣቢያዎች በተለያዩ ቦታዎች የተከሉዋቸውን የማሠራጫ መሣሪያዎች፣ 70 በላይ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የማሠራጫ ጣቢያዎች መሣሪያዎችንና ይዞታዎች በሙሉ ለሚቋቋመው የብሮድካስት ኔትወርክ አስተዳደር የልማት ድርጅት እንደሚተላለፉ፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የልማት ድርጅቱ እነዚህን የማሠራጫ ጣቢያዎች እንዲረከብ ከመደረጉ በፊት የፋይናንስ ግምታቸው ተሰልቶ እንደሚከፍልም ጠቁመዋል፡፡    

No comments: