Wednesday, June 1, 2016

ሕገ መንግሥቱን አልተቀበሉም ተብለው ከዳኝነት የተሰናበቱት የሕግ ባለሙያ የጥብቅና ፈቃድም ተከለከሉ

·         ክልከላውን በመቃወም ወደ ሰበር እንደሚሄዱ ገልጸዋል

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት 2006 .. ጀምሮ በዳኝነት ሲሠሩ የነበሩትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‹‹ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ ሆነው አልተገኙም›› በማለት ጥር 28 ቀን 2008 .. ከዳኝነት ሥራቸው እንዲነሱ ያደረጋቸው የሕግ ባለሙያ፣ የጥብቅና ፈቃድም መከልከላቸውን ገለጹ፡፡
የዳኞች የሥነ ምግባር ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ በተደረገ ውይይትና የአገሪቱ መሠረታዊ ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር በተደረገ ውይይት ላይ፣ ባደረጓቸው ንግግሮች ወይም በሰጡት ሐሳብና 1997 .. ምርጫን አስመልክተው የተናገሩትን በመጥቀስ፣ ‹‹ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ አይደሉም›› ተብለው ከዳኝነት ሥራቸው የተነሱት አቶ ግዛቸው ምትኩ ናቸው፡፡ በስምንት ዓመታት የዳኝነት አገልግሎታቸው ዘመን ምንም ዓይነት የሥነ ምግባር ጉድለት ፈጽመው እንደማያውቁ የሕግ ባለሙያው አቶ ግዛቸው ይናገራሉ፡፡
አቶ ግዛቸው ከዳኝነት ሥራቸው ከተነሱ በኋላ በጥብቅና አገልግሎት ሥራ ለመቀጠል ፈቃድ ለመውሰድ ለፍትሕ ሚኒስቴር የጥብቅና ፈቃድና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክቶሬቱ የሰጣቸው አጭር መልስ ከዳኝነት የተነሱት ‹‹ሕገ መንግሥቱን አልቀበልም›› ብለው መሆኑን ጠቅሶ፣ ለፍትሕ ሥራ አካሄድ መልካም ሥነ ምግባር አስፈላጊ እንደሆነ በመግለጽ ፈቃድ እንደ ከለከላቸው ተናግረዋል፡፡ አቶ ግዛቸው የጥብቅና ፈቃድና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ጥብቅናውን የከለከላቸው፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፈቃድ አሰጣጥና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 199/1992 ከሚደነግገው ውጪ መሆኑን፣ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በእሳቸው ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከዳኝነት ያነሳበትን ዝርዝር ማስረጃ ዳይሬክቶሬቱ ሳይመረምርና ትችት ሳይሰጥበት መሆኑን ጠቅሰው ለፍትሕ ሚኒስትሩ አቤቱታ ያቀረቡ ቢሆንም፣ ሚኒስትሩም የዳይሬክቶሬቱን ውሳኔ አፅድቀው እንደከለከሏቸው አቶ ግዛቸው አስረድተዋል፡፡
የጥብቅና ፈቃድ መከልከላቸው አግባብ አለመሆኑንና የጥብቅና ፈቃድ ለማግኘት ሕገ መንግሥቱን አለመቀበል ፈቃድ እንደሚያስከለክል እንደ መሥፈርት አለመቀመጡን፣ ለስምንት ዓመታት በዳኝነት ሲሠሩ አንድም ጊዜ በሥነ ምግባር ጉድለት ተጠይቀው እንደማያውቁና ለዳኝነት ሲመለመሉ በዋና መሥፈርትነት ተቀምጦ የነበረውን ሕገ መንግሥቱን ማክበርና ማስከበር ሲተገብሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ከተመደቡበት የዳኝነት ሥራ ውጪ በተደረጉ ውይይቶች ላይ በሰነዘሩት ሐሳብ ‹‹ሕገ መንግሥቱን አልተቀበልክም›› ተብለው ከዳኝነት ሥራቸው በመነሳታቸው፣ የጥብቅና ፈቃድ ሊከለከሉ እንደማይገባ በመግለጽ ክስ መመሥረታቸውን ጠበቃቸው አቶ ዳማው አስፋው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ያቀረቡትን የክስ ማመልከቻ ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አምስተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎትም፣ የሕግ ባለሙያው የጥብቅና ፈቃድ ቢሰጣቸው የሚገናኙት ወይም አገልግሎት የሚሰጡት ወደ ዳኝነት አካሉ ሄደው መሆኑን ጠቅሶ፣ ‹‹ለፍትሕ ሥራ አካሄድ መልካም ሥነ ምግባር ያስፈልጋል›› በማለት የጥብቅና ፈቃድና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ጥብቅና ፈቃድ የከለከለበትን መንገድ ተቀብሎ ጥያቄያቸውን ውድቅ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ አለመሆን በየትኛውም ምዘና ለጥብቅና ፈቃድ ክልከላ ሊውል እንደማይችል የሚናገሩት ጠበቃቸው አቶ ዳማው፣ በሥነ ምግባር ደንቡ አንድ ጠበቃ በተደራቢነት የፖለቲካ ሥራ ሊሠራ እንደሚችል አስቀምጦ እያለ፣ ‹‹አንድ የሕገ መንግሥት አንቀጽ እንዲሻሻል ጠይቀሃል›› በሚል፣ ከዳኝነት የተነሳን ሰው በፍትሕ ሥራ ውስጥ ገብቶ እንዳይሠራ ፈቃድ መከልከል ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ አንድ ሰው ሙያውን መርጦ መሥራት እንደሚችል ደንግጎ እያለ፣ ‹‹ይህንን አመለካከት ይዘህ ላንተ ፈቃድ አልሰጥም›› ማለት፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 ላይ ለዜጎች እኩልነት የሰጠውን ድንጋጌ መቃረንና በዜጎች መካከል ልዩነት መፍጠር መሆኑንም አክለዋል፡፡
የዳኞች አስተዳደር ጉባዔም በውሳኔው ያስታወቀው አንድ ዳኛ በሥራ ላይ ባለበት ወቅት የራሱ የሆነ የፖለቲካ አመለካከት ሊኖረው ቢችልም፣ ያንን አመለካከቱን በዳኝነት ሥራው ላይ ሊያንፀባርቅና ወገንተኛ ሊሆን እንደማይችል እንጂ፣ ከሐሳብ ሊነፃ እንደማይችል መግለጹን ጠቁመዋል፡፡  
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም አቶ ግዛቸው ከዳኝነት ኃላፊነታቸው ባነሳበት ወቅትም፣ ስለወደፊት የጥብቅና ሥራቸው ምንም ያለው እንደሌለና አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ከጥብቅና ፈቃድ ጋር ተያይዞ ጥያቄ ሲያነሱ ምክር ቤቱ በዝምታ ማለፉን አስታውሰዋል፡፡ ይኼ የሚያሳየውም በአንድና በሁለት ስብሰባዎች ላይ በተሰነዘረ ሐሳብ ከሁሉም የሕግ ሥራዎች ላይ መነሳት ሳይሆን፣ ጉባዔው ባመነበትና ጠቅሶ ያሳለፈውን ውሳኔ ማፅደቅ ብቻ እንደሆነም አክለዋል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔም ሕገ መንግሥቱን የሚቃረንና ተገቢነት የሌለው በመሆኑ፣ አቤቱታቸውን ለፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት እንደሚያቀርቡ የአቶ ግዛቸው ጠበቃ አቶ ዳማው ተናግረዋል፡፡  

No comments: