Monday, June 13, 2016

ከእንቅልፋችን ስንነሳ የጦርነት( የዉጊያ) ወሬ ተቀበለን፡፡


ከእንቅልፋችን ስንነሳ የጦርነት( የዉጊያ) ወሬ ተቀበለን፡፡ ‹‹ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ full scale ጦርነት ከፈተች›› ይላል አዉራምባ የወያኔ የወሬ ምንጭ፡፡ ‹‹ፉልስኬል ጦርነት›› ማለት ምን እንደሆነ ማን እንዳስተማረዉ ባናዉቅም፡፡ 
ሌሎችም በስሱ እያስተነፈሱት ይገኛሉ፡፡ይፋ ያልሆነዉን የኤርትራ መንግሥት ‹‹ተወረርኩ›› ስሞታ ጨምሮ፣ ሕወሓቴዉ የማኅበራዊ ሚዲያ ካድሬ ዳንኤል ብርሃኔ፣ በፆረና በኩል የተኩስ ልዉዉጥ መኖሩን ይጠቁመናል፡፡ 
አዉራምባ እንደሚለዉ ‹‹ፉልስኬል›› የሚባል ነገር ባይኖርም ወታደራዊ ግጭት(ትንኮሳ) በድንበር አካባቢ መኖሩን የሚጠቁም ነገር መኖሩ እዉነት ነዉ፡፡ ጦርነት ሳይሆን ዉጊያ፡፡ ሁለቱ የተለያዩ ነገሮች ናቸዉና ነዉ፡፡
‹‹ከሆነስ ለምን?ማንስ ጀመረዉ? ›› የሚል ጥያቄ ይከተላል፡፡ ‹‹ለምን?›› ለሚለዉ ጥያቄ ግምታዊ ምላሹ ብዙ መቻሉ ብዙም ገፍተን እንዳንሄድ ሊያደርገን ይችላል፡፡ እናም ብዙ አንሄድም፡፡ 

‹‹ጦርነት›› በጥሬ ትርጉሙ የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈፀሚያ መሣሪያ ነዉ፡፡ 

ከወያኔ ወገን እንደሚወራዉ እኛም እናዉራ ካልንና ‹‹ሻዕቢያ ዉጊያ ከፈተ›› ብንል የትኛዉን ፖለቲካዊ ጥቅም ለማግኘት? የሚል ጥያቄ ወዲያዉ ይመጣብናል፡፡ወዲያዉ መልስ የማናገኝለት ጥያቄ፡፡
ቀጥሎም ኤርትራ በአሁኑ ጊዜ ጦርነትን መሸከም የሚችል ኢኮኖሚ፣ ዉጊያዉን ሊያግዝ የሚችል የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ድጋፍ አላት ወይ? ማለት ይቻላል:: ይህም በጥናትና በመረጃ የተደገፈ ምላሽ ይፈልግ ይሆናል፡፡
መሬት ላይ ያለዉን ደረቅ ሀቅ ካየን ግን፣ በአሁኑ ወቅት ኤርትራን ለማጥቃት ዉጊያ የሚገፋፋ ምክንያትም ሆነ አቅም ያለ አይመስልም፡፡
ዉጊያዉን በወያኔ ተቃዋሚዎች ለማሳበብ ቢሞከር እንኳ፣ በአሁኑ ጊዜ ከደፈጣና ከወረራ (ሽምቅ ዉጊያ ስልቶች) አልፎ መደበኛ ዉጊያ ለማካሄድ የሚያስችል አደረጃጀትና አቅም ያለዉ ተቃዋሚ ኤርትራ ዉስጥ አለመኖሩን በድፍረት መናገር ከባድ አይደለም፡፡ 
በወያኔ በኩል ካየን ግን ፣ቢያንስ ወደትንኮሳ ሊያስገባ የሚችል ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሁኔታ አለ ብሎ መቀበል ይቻላል፡፡
በአንድ በኩል፣ በሀገር ዉስጥ ያለዉ ፖለቲካዊ ቀዉስ ከሀገር አልፎ የዓለም መነጋገሪያ ከመሆኑም ባሻገር በአገዛዙ ሰዎች መሐከልም አለመግባባትን መፍጠሩ እዉነት ነዉ፡፡
ለሀገር ዉስጥ ቅዉስ ትኩረት ማስቀየሪያና አመራሩን ወደአንድ ሐሳብ ለማምጣት ‹‹የሀገር ሉዓላዊነት…›› ብሎ ጦርነትን መፍጠርና እዚያም ዉስጥ መግባት መፍትሔ ተደርጎ ሊታሰብ ይችል ይሆናል፡፡ የፈለገዉን ያህል ዋጋ ቢያስከፍልም፡፡ ዋናዉ ነገር በዚህም፣ በዚያም ሥልጣኑን ጠጋግኖ ማቆየት መቻል ነዉና፡፡ 
በሌላ በኩል ኤርትራዉ ውስጥ ያለዉን የተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ ወያኔ በቅርብና በትኩረት ይከታተላል፡፡ ከሥልጠና እስከ ግዳጅ ስምሪት ድረስ ያለዉን እንቅስቃሴያቸዉን አያዉቅም ማለት አይቻልም፡፡ የራሳቸዉን ሰዎች በተቃዋሚዉ ዉስጥ አስርገዉ ከማስገባት ጀምሮ እስከ ኢሳይያስ ቤተመንግሥት ድረስ ወሬ አቀባይ እናዳላቸዉ አለመጠርጠር ቢያንስ የዋህነት ነዉ፡፡
እናም የተቃዋሚዉ እንቅስቃሴ በሚያሰጋዉ ደረጃ ላይ መድረሱን ካመነ ማንቁርቱ ላይ እስከሚቆሙበት ድረስ አይጠብቅም፡፡ቢያዋጣዉም፣ባያዋጣዉም የተደራጀ ጠላቱ ካለበት ድረስ ዘልቆ ሄዶ ግጭት መፍጠር የሚጠበቅ ጉዳይ ነዉ፡፡ የሚገርመዉ ተቃዋሚዉ ‹‹ይህ ሊሆን አይችልም›› ብሎ ከተዘናጋ ወይም ራሱን ከጣለ ነዉ፡፡ 
ወያኔ ኤርትራ ዉስጥ ገብቶ ዉጊያ ቢጀምር ‹‹ ዓለም አቀፍ ጫና›› የሚባለዉ ነገር ሊበረታበት እንደማይችል ያምናል፡፡ ምክንያቱም በሰብዓዊ መብት ጥሰት ስም በኤርትራ መንግሥት ላይ እየቀረበ ያለዉ ክስና የአልሻባብ ጉዳይ ‹‹ያግዘኛል›› ብሎ ስለሚያስብ፡፡
‹‹የሀገር ሉዓላዊነት ተደፈረ›› ብሎ የሕዝብ ድጋፍ ማግኘት የመቻሉ አጠራጣሪነት ጥያቄ ዉስጥ ካልገባ በስተቀር ቢያንስ ቢያንስ የሚያሰለጥናቸዉን የፀረ ኢሳይያስ ኃይሎች ፊትአዉራሪ በማድረግ ወያኔ ከሻዕቢያ ጋር ግጭት ዉስጥ ቢገባ ሊያስገርም አይችልም፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ፣በሀገር ዉስጥ እየደረሰበት ያለዉን ተቃዉሞ ትኩረት ለማስቀየር ዉጊያ ዉስጥ መግባት መቻሉ እንዳለ ሆኖ፣ እነርሱ ወደዳር ሀገሩ ጦርነት ሲያተኩሩ ከመሐል ያለዉ ሕዝባዊ አመፅ ጉድ እንዳያደርገዉ መጠራጠሩም አይቀሬ ነዉ፡፡
ጠላትን ከጀርባ አስቀምጦ (ትቶ) ፊት ለፊት ያለዉን ጠላት ፍልሚያ መሄድ ቂልነት ነዉና፡፡ወያኔዎች ጀብደኞችና እብሪተኞች ቢሆኑም እንኳ፣ አፍንጫቸዉ ሥር እየነደደ ያለዉን እሳት እያዩ ሌላ እሳት ለመቆስቆስ የሚሹ ጅሎች አይመስሉም፡፡ ትርፍና ኪሳራቸዉን በማስላት በኩል የማይናቁ ቆቆች ናቸዉ፡፡
በአጠቃላይ በድንበር አካባቢ በተፋጠጡ ኃይሎች አካባቢ በቃኚዎች መሐከል ከሚደረግ ግጭት ጀምሮ፣ በመከላከያ ምሽግ ዉስጥ ያለን ጠላት የመሣሪያና የሰዉ ኃይል አሰላለፍ መረጃ ለማግኘት አንዳንዴ ይሁነኝ ብሎ ተኩስ መክፈት ያለ ነገር ነዉ፡፡ 
ይህ ማለት ግን፣ በአሁኑ ወቅት ወያኔ እያደረገ እንዳለዉ መቀሌ አካባቢ የሰፈረዉን ሜካናይዝድ ጦር ወደድንበር ማንቀሳቀስ ድረስ የሚሄድ ሊሆን አይችልም፡፡
የሆነዉስ ይሁንና የምር ‹‹ዉጊያ ተጀመረ›› ቢባል ማንን ነዉ መደገፍ ያለብኝ? ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነዉ›› ማለት እንድችል ጠላቴ ማነዉ? ብዬ ራሴን ልጠይቅ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እህት ወንድሞቼን እየገደለ ያለዉ ማን እንደሆነ ልቦናዬ ሲያዉቅ፡፡‹‹ አንደግፋችሁም›› ብንል በሌለንበት በሀገር ክህደት እንዳትከሱን አደራ፡፡
የሠይጣን ጆሮ አይስማዉና ነገሩ እዉነት ከሆነ የስንቱን ደሃ ልጅ ሕይወት ጭዳ ያደርጉ ይሆን?

Befekadu Moroda

No comments: