ሰኔ ፲፮ (አሥራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ለወራት የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ለመመልመል የተደረገው ሙከራ አለመሳካቱን ተከትሎ ድንጋጤ ውስጥ የገቡት የኢህአዴግ ከፍተኛ የደህንነት ሹሞች፣ ክልሎች ኮታቸውን እንዲያሙዋሉ አስቸኳይ ትእዛዝ ሰጥተዋል።
ሰራዊቱን እየጣሉ የሚጠፉ ወታደሮች መበራከት እንዲሁም ከኤርትራ ጋር ሙሉ ጦርነት ሊካሄድ ይችላል በሚል የወታደር ምልመላውን አጠናክሮ ለመቀጠል የተጀመረው እቅድ በአማራ፣ ደቡብ፣ ኦሮምያና ሃረሪ ክልሎች ከሽፏል።
በሃረር ከተማ የሁሉም የወረዳ የካብኔ አመራሮች ዛሬ ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ ፣ ክልሉ የወታደር ምልመላ ባለማድረጉ ወቀሳ ደርሶበታል። እያንዳንዱ ወረዳ 30 ሰዎችን እንደሚለምል ግዳጅ የተሰጠው ቢሆንም፣ በአንዳንድ ወረዳዎች አንድም የተመዘገ ሰው አለመኖሩ ሲገለጽ፣ በጥቂት ወረዳዎች እስከ 4 ወጣቶች መመዝገባቸው ሪፖርት ቀርቧል።
የተለያዩ ቅስቀሳዎች ቢደረጉም ወጣቱ ለመመዝገብ ፈቃደኛ አይደለም የሚል ሪፖርት መቅረቡንም የክልሉ ወኪላችን ገልጿል። በተመሳሳይ መንገድ በአማራ እና ደቡብ ክልሎች አሁንም ቅስቀሳው ተጠናክሮ ቢቀጥልም፣ የሚመዘገብ ወጣት ሊገኝ አልቻለም። በሰሜን ጎንደር በዳባትና አጎራባች ቀበሌዎች የሚገኙ ወጣቶች ተቃዋሚዎች ናችሁ በሚል ሰበብ እየተያዙ ወደ ጦር ግንባር በቅጣት ስም ለመላክ ዝግጅት መጀመሩንም ኢሳት መረጃዎች ደርሰውታል።
No comments:
Post a Comment