Thursday, June 30, 2016

ኢትዮጵያን እንደ አገር ለመቀጠል ከሚያሰጋቸው አገራት ተርታ ተመደበች

ሰኔ ፳፫ ( ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፰ / ኢሳት ዜና :- ዓመታዊው የአገራት ሰላምና ጸጥታ የሰፈነባቸውና ለሰው ልጆች ደኅንነት አስጊ የሆኑ አገራት ጥናት የደረጃ ሰንጠረዥ ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ በዓለማችን ላይ ያሉ ለወደፊቱ እንደ አገር ለመቀጠል ከፊት ለፊታቸው ሥጋት ከተደቀነባቸው 25 አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆናለች። በዓመታዊው የአገራት የደረጃ ሰንጠረዥ መሰረት ሰላምና ጸጥታ የሰፈነባቸው ለዜጎች ምቹ የደኅንነት ዋስትና ያላቸው በመባል የስካንዲኒቪያን አገራት በቀዳሚነት ይመራሉ።
ኢትዮጵያ ከሃያ አምስቱ አገራት 24 ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን 64 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ እድሜያቸው 25 ዓመት በታች ውስጥ እንደሚገኙና በከፍተኛ ደረጃ የሕጻናት ሞት ከሚከሰትባቸው 33 የዓለማችን አገራት ተርታ እንደምትመደብም ጥናቱ አመላክቷል።
ባለፈው ዓመት ብቻ በኢትዮጵያ በአገር ውስጥ 400 ሽህ በላይ ዜጎቿ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል። ይህም ለወደፊቱ እንደ አገር ለመቀጠል ከፊት ለፊታቸው ከፍተኛ የሆነ የደኅንነት ሥጋት ከተደቀኑባቸው አገራት ተርታ ኢትዮጵያ እንደምትገኝ ጥናቱ አመልክቷል።
ሁለቱ ጎረቤት አገራት ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ሲመሩ መሃከለኛው አፍሪካ፣ የመን፣ ሱዳን፣ ሶሪያ፣ ቻድ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣ አፍጋኒስታንና አይቲ ከአንድ እስከ አስር ያለውን ደረጃ በቅደምተከተላቸው ይዘዋል።


No comments: