ሰኔ ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ደጋማ ክፍል በእርዳታ ስም የተሰራጨው የቡና ዘር ምንነት ሳይመረመር በመሰራጨቱ በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ተናግረዋል። ማንነቱ ያልታወቀ የውጭ ዜጋ መስመሩን ባልተከተለ ሁኔታ ባለሙዎችን ሳያሳትፍ እና በቂ ገለጻ ሳያደርግ የዞኑን አመራሮች በመያዝ ወደ አርሶ አደሮች በመድረስ ዘሩን ማሰራጨቱ አግባብ እንዳልሆነ የአትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያው ተናግረው አንድ ዘር ወደ አርሶአደሩ ዘንድ ከመሰራጨቱ በፊት በምርምር ሊሞከር እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ ዘር ሲቀርብ በመጀመሪያ ደረጃ በዘርፉ ለሚሰሩ ባለሙያዎች ተገቢው ገለጻ ተደርጎና በሙከራ ተረጋግጦ ተስማሚነቱ መረጋገጡ የተለመደ ቢሆንም ሰሞኑን የቀረበው የቡና ዘር ግን ዘሩን ያመጣው ግለሰብ ከበላይ አመራሩ ጋር ብቻ በመነጋገር እንዲከፋፈል ማድረጉ ተገቢ ያልሆነ በወንጀል የሚያስጠይቅ ድርጊት መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ ወደ አርሶ አደሩ የተከፋፈለው ዘር የአምራቹ ድርጅት ስም፣ የተዘጋጀበት ቀንና ሃገር እንዲሁም የዘሩን መለያ ስም አካቶ የሚይዘው መለያ ያልተለጠፈበት መሆኑን ከስርጭቱ በኋላ በተደረገው ፍተሻ ለማረጋገጥ መቻሉን ባለሙያው ገልጸው፤የመለያው አለመኖር ዝርያው ለየትኛው አካባቢ የተሰራ መሆኑንና የዝርያውን ባህሪ ለማወቅ አስቸጋሪ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ወደ አርሶአደሩ መሰራጨቱ ጥቆማ ከደረሳቸው በኋላ ጉዳዩን ተከታትለው ለመመርመር ያደረጉትን እንቅስቃሴ በአመራሮች ተጽእኖ እንዲያቆሙ ግፊት እንደተደረገባቸው ተናግረው ፣ ይህ ያልተመረመረ ዘር መሰራጨቱ በአካባቢው ያለውን የቡና ዘር ሊበክል እና የመሬት ኪሳራ ሊያደርስ የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል ባለሙያው ስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡ አመራሮች ዘሩን ያቀረበው ግለሰብ ይህን በማድረጉ የሚያገኘው ጥቅም እንዳይቀርበት ብቻ በማሰብ በአቅራቢው ላይ የሚነሳ ጥያቄ እንዳይኖር ሲከላከሉ መታየታቸውን የሚገልጹት የአትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያ አቅራቢው ስለአቀረበው ዘር የሰጠው መግለጫ አለመኖሩ ሌላው ክፍተት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻ ያለ እውቅና የተሰራጨው ዘር እንደ ሃገር በቡና ላይ ያለውን የቴክኖሎጂ ስርጸት እና በቡናችን ላይ ያለው ተቀባይነት ዙሪያ የሚያመጣውን ክፍተት ቢያስረዱም ሰሚ በማጣት ክፍተቱ እንዳለ መቀጠሉን ባለሙያው ለሪፖርተራችን ገልጸዋል፡፡
No comments:
Post a Comment