በናትናኤል ፈለቀ
(ካለፈው የቀጠለ)
የማታው የመፀዳጃ ሰዓት አብቅቶ እስረኞችን ቆጥረው በሩን የሚቆልፉት ፖሊሶች መጡ፡፡ ሼህ ጀማል ዘወትር እንደሚያደርጉት የመጡት ፖሊሶችን ሰዓት ጠየቋቸው፡፡ አልፎ አልፎ በቁጣ ተሞልተው ከሚመጡት ፖሊሶች በስተቀር ሰዓት ለመናገር አብዛኞቹ ተባባሪዎች ናቸው፡፡ 12 ሰዓት ከ10 ደቂቃ እንደሆነ የተነገራቸው ሼህ ለመግሪብ ጸሎት የቀረው ግማሽ ሰዓት እንደሆነ ክፍሉ ውስጥ ለነበሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች አሳወቁ ኡመድ ለፈረሃን ተረጎመለት፡፡
ደቂቃዎች አልፈው የፀሎት ዝግጅት ላይ እያሉ ከሳይቤሪያ ኮሪደር መግቢያ ላይ የሚንቆጫቀጭ የካቴና ድምፅ በከስክስ ኮቴ ታጅቦ ተሰማ፡፡ ድምፁ ምን ማለት እንደሆነ ክፍሉ ውስጥ ያሉት 14ቱም ይገባቸዋል፡፡ በእስር ለቆዩት ሰዎች ግር ያላቸው ነገር ተቆጥረው በር ከተዘጋ በኋላ በዚህ ፍጥነት ለምርመራ የሚጠራ ሰው መኖሩ ነው፡፡ የካቴናው ድምጽ 7 ቁጥር በር ላይ ሲደርስ ቆመና በሩ ተከፈተ፡፡ ‹‹ፈረሃን ኢብራሂም›› ከውጭ የመጣው ጥሪ አስተጋባ፡፡ ለምርመራ ሲጠራ የመጀመሪያው የሆነው ፈረሃን ምን ማድረግ እንዳለበት ግር ብሎት ተደናበረ፡፡ ተነስቶ ቆመ፡፡ ‹‹ፈረሃን ኢብራሂም እዚህ አይደለም?›› ከውጭ የቆመው ፖሊስ ጠየቀ፡፡ ኡመድ ፈርሃን እንዲወጣ በምልክት ወደበሩ ጠቆመው፡፡ ፈረሃን ኮፍያ ያለውን ሹራብ ደረበና ወጣ፡፡
ውስጥ የቀሩት ሰዎች እርስ በርስ ለምን በዚህ ሰዓት ሊጠራ እንደቻለና ምን ሊከሰት እንደሚችል የራሳቸውን መላምት እየሰጡ ክፍሉን በጫጫታ ሞሉት፡፡ በሼህ ጀማል የተመራው ፀሎት ተጠናቆ ብዙም ሳይቆዩ ወደ 7 ቁጥር እየቀረበ የመጣ የእግር ኮቴ ሰምተው ደግሞ ማን ይሆን ባለተራ ብለው በሰቀቀን በር በሩን ያዩ ጀመር፡፡ በሩ ተከፈተና ፈረሃን ገብቶ በሩ ተዘጋ፡፡ ከሄደ ግፋ ቢል ግማሽ ሰዓት ቢሆነው ነው፡፡ በዚህ ፍጥነት የሚጠናቀቅ የመጀመርያ ምርመራ የለም፡፡ ቢያንስ በምርመራ ወቅት እስኪሰለች ድረስ በተደጋጋሚ የሚጠየቀው የሕይወት ታሪክ ከ30 ደቂቃ በላይ መፍጀት አለበት፡፡
ፈረሃን በተፈጠረው ነገር እንደተገረመ ፊቱ ላይ ያስታውቃል፡፡ ኡመድ ምን እንደተከሰተ ሊጠይቀው ሲል ፈረሃን ቀድሞ ጭንቅላቱን እየነቀነቀ ‹‹እነዚህ ሰዎች የሚደንቁ ናቸው!›› አለ፡፡ ‹‹እንዴት?›› የኡመድ ተጠባቂ ጥያቄ ነበር፡፡ ፈረሃን ጭንቅላቱን መወዝወዙን ሳያቋርጥ፡ ‹‹ኮሪደሩን እንደጨረስን የለበስኩትን ሹራብ አስወልቆ ፊቴ ላይ አሰረው፡፡ በጣም አጥብቆ ስላሰረው እንዳመመኝ እና መተንፈስ እንደተቸገርኩ ብነግረውም ምንም ውጤት አልነበረውም፡፡ ከዛ እየመራ የሆነ ክፍል ውስጥ ከተተኝ፡፡ ስሜን፣ ከየትኛው የሱማሌ ጎሳ እንደሆንኩኝና ለምን ወደኢትዮጵያ እንደመጣሁኝ ጠየቁኝና ጨርሰናል ብለው መለሱኝ፡፡›› ብሎ በእጁ አንጠልጥሎት የገባውን ሹራብ መልበስ ጀመረ፡፡ ‹‹ሲያናግሩህም ፊትህን ሸፍነውህ ነበር?›› ኡመድ ተገርሞ ጥያቄውን ቀጠለ፡፡ ‹‹ኮሪደሩን ስንጨርስ እንዳሰረኝ መልሰውኝ እዛው ስደርስ ነው ከፊቴ ላይ የፈቱልኝ፡፡›› ነገርየው ይበልጥ እንቆቅልሽ የሆነበት ኡመድ ሌላ ጥያቄ አስከተለ ‹‹ስንት ሆነው ነው ያናገሩህ?››፡፡ ‹‹ሁለት ድምፆች መስማቴን እርግጠኛ ነኝ›› አለ ፈረሃን፡፡ ፈረሃን በጥያቄዎቹ መሰላቸቱን ኡመድ ቢረዳም ጉጉቱን ግን ማሸነፍ አልቻለም፤ ‹‹ሊያናግሩ የወሰዱህን ክፍል አቅጣጫ ታስታሰዋለህ?›› ሲል ጠየቀ፡፡ ‹‹ደረጃ ይዘውኝ ስለወጡ ፎቅ ላይ መሆኑን ብቻ ነው የማውቀው፡፡›› ፈረሃን መለሰ፡፡ ኡመድ ማዕከላዊ በቆየባቸው አንድ ወር ከግማሽ ጊዜ ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር ሲገጥመው የመጀመሪያው ነው፡፡ በርግጥ እራሱም ወደ 11፡30 አካባቢ አንድ ቀን ተጠርቶ ነበር፡፡ የዛኔ ምርመራ ያደረገበት ምንም የማያውቅ ግን ብዙ የሚያውቅ ለማስመሰል የሚጥር ከደኅንነት መሥሪያ ቤት የመጣ ሰውዬ ነበር፡፡ ሰውየውን አይቶታል፡፡ ለምርመራ ሲወስዱትም ዓይኑን አልሸፈኑትም፡፡ ፈረሃን የነገረውን እየተረጎመ ለሌሎቹ ሲነግራቸው ፈረሃን በመኻል አቋረጠውና ‹‹የአንደኛው ሰውዬ ድምፅ ግን ካረፍኩበት ሆቴል ይዘውኝ ሲመጡ ሲቪል ለብሶ የነበረውን ሰውዬ ድምፅ ይመስላል፡›› አለ፡፡ ሁሉም በሰሙት ነገር ተገርመው እያወሩ እንቅልፍ አንድ በአንድ ጣላቸው፤ ሌንጂሳ እስኪጠራ ድረስ፡፡
በማግስቱ ማክሰኞ ፈረሃን በተመሣሣይ ሰዓት ተወስዶ ሩብ ሰዓት እንኳን የሞላ ምርመራ ሳይወስድ ተመለሰ፡፡ በዚህኛው ምርመራ ደግሞ ሲጠየቅ የነበረው ወደኢትዮጵያ አብሮት የመጣ የሚያውቀው ሰው እንዳለ እና ጢያራ ማረፊያ ተገኝቶ የተቀበለው አስጎብኚን ማን እንዳስተዋወቀው ነበር፡፡ ፈረሃን አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ጢያራ ማረፊያ ከመጣበት ጢያራ ሲወርድ ሰላምታ ከተለዋወጠው አንድ ሴንት ፓውል በመልክ ብቻ ከሚያውቀው ተለቅ ያለ ሱማሌ ውጪ ሌላ የሚያውቀው ሰው በመንገዱ ላይ እንዳላጋጠመው እና አስጎብኚ ያሉት ሰው የእናቱ የወንድም ልጅ እንደሆነ ፊቱን ሸፍነው ለሚመረምሩት ሰዎች አስረድቶ ተመለሰ፡፡
***
እጅግ አስቸጋሪ እና በአደጋ የተሞላ ቢሆንም ሳይቤርያ ያሉ እስረኞች መልዕክት የሚለዋወጡበት ዘዴ አበጅተዋል፡፡ የምርመራ ሂደታቸው ምን እንደደረሰ፣ እየተጠየቁ ያሉት ጥያቄዎች ምን ምን እንደሆኑ እና ከማዕከለዊ ውጭ ስላለ ነገር መረጃ ሲደርሳቸው ሌላ ክፍል ውስጥ ያለ ጓደኛቸው ጋር መልዕክት ይለዋወጣሉ፡፡ እንደዚህ በሚስጥር ካልሆነ በቀር ሁለት የተለያዩ የሳይቤሪያ ክፍሎች ውስጥ ያሉ ታሳሪዎች በፍፁም አይገናኙም፡፡ ይህንን የታዘበው ፈረሃን ኡመድን ውለታ ጠየቀው፡፡ አብረውት ፍርድ ቤት የቀረቡት ሱማሌዎች ያሉበትን ክፍል እና የምርመራቸው ሂደት እንዴት እንደሆነ እንዲያጣራለት ነበር የፈለገው፡፡
ኡመድ ሳይቤሪያ ሌላ ክፍሎች ውስጥ ባሉ አብረውት በታሰሩ ጓደኞቹ በኩል ባደረገው ማጣራት መውሊድ የሚባለው ከፈረሃን ጋር ፍርድ ቤት አብሮ የቀረበው ሱማሌ 3 ቁጥር ውስጥ እንደሚገኝ እና ኢብራሂም የሚባለው ደግሞ 4 ቁጥር ውስጥ እደሚገኝ አወቀ፡፡ ፈረሃን ለሁለቱም በያሉበት የድብቅ መልዕክት ልኮ ያሉበትን አጠቃላይ ሁኔታ እንዲያስረዱት ቢጠይቃቸውም መልስ ግን አልመጣም፡፡ ሁለት ቁጥር ውስጥ ታስሮ የነበረው አብሯቸው ፍርድ ቤት የሄደው ሽማግሌ ግን ‹‹እስካሁን ለምርመራ ወስደውኝ አልወሰዱኝም›› የሚል መልዕክት መለሰ፡፡ ፈረሃን ለሽማግሌው በላከው የመልስ መልስ ሽማግሌው ለምርመራ ከተወሰደና ‹‹ፈርሃንን ታውቀዋለህ ወይ?›› የሚል ጥያቄ ከተነሳበት ‹‹ፈረሃንን አውቀዋለሁ፤ በጣም ጥሩ ባሕሪ ያለው ልጅ ነው፡፡›› እንዲልለት ለመነው፡፡
***
ፋይሰል 8 ቁጥር ካሉት ክፍሎች ውስጥ በስተግራ በኩል ወዳለው የመጀመርያ ክፍል ነበር የተዘዋወረው፡፡ በመጀመርያ የገባ ቀን ጋህነም ውስጥ የከተቱት ነበር የመሰለው፡፡ የክፍሉ አየር መታፈን ሳያንስ የሚተኛበት ፍራሽ ደግሞ የሆነ የሚረብሽ ጠረን ነበረው፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ መርማሪዎቹ ደግሞ በተከታታይ እየጠሩ ታውቃለህ የሚሉትን እንዲያምንላቸው ልብሱን አስወልቀው ይደበድቡታል፤ የውስጥ እግሩን በኤልክትሪክ ሽቦ ይገርፉታል፡፡ ከዚህ ሻል ያለ ቅጣት በሚቀጣ ቀን እጁን ወደላይ ሰቅሎ ቁጭ ብድግ እንዲሰራ ይገደዳል፡፡
ለብቻው የታሰረበት ክፍል ውስጥ ስለታሰረበት ጉዳይ እንኳን ባይሆን ስለሌላ ተራ ጉዳይ የሚያወያየው ሰው ማጣቱ ጭንቅ ውስጥ ከቶታል፡፡ ሰው ማጣት እንደዚህ ያሰቃየኛል ብሎ አስቦ አያውቅም፡፡ ሌላ ግዜ በራሱ ፍላጎት ብቻውን ሲሆን እንኳን እንደሚያደርገው ቁርዓን እንዳይቀራ፣ ቁርዓን የለውም፡፡ ቢኖረውም ኖሮ በየትኛው ብርሃን ሊያነብ፡፡ የተወለደበትን ቀን አምርሮ ረገመ፡፡
ክፍሉ ውስጥ የሚተኛበት ፍራሽ፣ ለኡዱ ማድረጊያ በላስቲክ ቀድቶ የሚያስቀምጠው ውኃ እና ለመጸዳጃ የሚሆነው ባሊ አለ፡፡ የሚተኛበት ፍራሽ ቁመት ከክፍሉ ርዝመት ስለሚበልጥ በአግድሞሽ ካልሆነ እግሩን ዘርግቶ መተኛት አይችልም፡፡ ፋይሰል የሚያስበውም፣ የሚበላውም፣ የሚጸዳዳውም፣ የሚተኛውም እዚችው ክፍል ውስጥ ነው፡፡
8 ቁጥር አጠገቡ ካሉት ሦስት ክፍሎች ውስጥ አብረውት ፍርድ ቤት ከቀረቡት አምስት ሱማሌዎች መካከል አንዳቸውም እንደሌሉ አረጋግጧል፡፡ ለምን እሱ ላይ እንዲህ ያለ ሰቆቃ እየተፈፀመበት እንደሆነ ለመረዳት ተቸገረ፡፡ የአጎቱ ልጅ በፍርሐት ያልሆነ ነገር ተናግሮ እንደሆን ጠረጠረ፡፡ አብረውት ፍርድ ቤት ከቀረቡት መካከል ብቸኛው የውጭ ሀገር ፓስፖርት ባለቤት አለመሆኑ ለዚህ እንደዳረገው እንዴት ሊጠረጥር ይችላል?
***
በሳምንት አንድ ቀን ተራ ወጥቶላቸው ሳይቤርያ ያሉ ማረፊያ ቤቶች ለግማሽ ቀን ያክል ክፍሉ ውስጥ ባሉ ታሳሪዎች ይጸዳሉ፡፡ ሁሉም እስረኞች ገላቸውን መታጠብ የሚፈቀድላቸውም ክፍላቸውን በሚያጸዱበት ቀን ብቻ ነው፡፡ ረቡዕ ከሰዓት ፋይሰል ያለበትን ክፍል እንዲያጸዳ እና ገላውን እና ልብሶቹን እንዲያጥብ ታዘዘ፡፡ የተባለውን ለመፈፀም የሚተኛበትን ፍራሽ ወደኮሪደሩ ይዞት ሲወጣ ፍራሹ ላይ ያየው ነገር ሆዱን እረበሸው፡፡ ወዲያው ከፍራሹ ይወጣ የነበረው መጥፎ ጠረን ምን እንደሆነ ገባው፡፡ ከሱ በፊት እዛ ክፍል ውስጥ ታስሮ የነበረው ሰው ደም የፍራሹን ራስጌ ቀይ ቀለም አልብሶታል፡፡ እስከዛ ቀን ድረስ ደም ላይ ተኝቶ እንደነበር ሲያስብ የበላው ምሣ እንዳለ ወጣ፡፡
***
2 ቁጥር ውስጥ ያለው ሽማግሌ ለፈረሃን መልዕክቶች መልስ መመለስ አቁሟል፡፡ ፈረሃን በሁኔታው ግራ ተጋብቷል፡፡ በመጀመሪያ ቀን መውሊድ እና ኢብራሂም እንኳን መልዕክት መላክ ባልቻሉበት ግዜ ፈጥኖ መልስ የላከው እሱ ነበር፡፡ ከዛን ግዜ ወዲህ ግን በተገላቢጦሽ ከነመውሊድ ጋር በተደጋጋሚ መልዕክት ሲለዋወጥ ለሽማግሌው የሚልከው መልዕክት ግን የውኃ ሽታ ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡ መውሊድ እና ኢብራሂም ከፈረሃን የተለየ ምርመራ አልተደረገላቸውም፡፡ የተለየ ነገር የነበረው መውሊድ ከፈረሃን ጋር የት እንደሚተዋወቅ መጠየቁ ነው፡፡ ሽማግሌው ሰውዬ ግን ለምርመራ ይወሰድ አይወሰድ፣ ስለፈረሃን ጠይቀውት ጭራሽ አላውቀውም ይበል ወይንም ልመናውን ተቀብሎ ስለ‹ጥሩ› ባሕሪው ምስክር ሆኖለት ይሆን ማወቅ አልቻለም፡፡
ሴቷ ወጣት ሱማሌ ደግሞ ሳይቤሪያ ባሉ ማረፊያ ቤቶች ውስጥ ያሉ ታሳሪዎች በቀን ለ10 ደቂቃ የሚፈቀድላቸው የፀሐይ ብርሃን ከሚያገኙበት ቦታ ፊት ለፊት በተለምዶ ጣውላ ቤት በመባል የሚጠራው የሴት እስረኞች እና ጓደኞቻቸው ላይ ምስክር ለመሆን የተስማሙ ወንድ እስረኞች የሚቆዩበት ሕንፃ ላይ ያለ ክፍል ውስጥ ስለሆነ ያለችው ፈረሃን ከሷ ጋር መልዕክት መለዋወጥ አልቻለም፡፡
***
ፍርድ ቤት የቀረቡ ዕለት በሽማግሌው እና በወጣቷ ሴት መካከል ያስተዋለው መቀራረብ የቆየ ትውውቅ እንዳላቸው እንዲጠረጥር አድርጎት ነበር፡፡ ፋይሰል ጥርጣሬው ልክ እንደነበር የገባው ምርመራው ቀሎለት ከብቸኛ ክፍሉ ከ8 ቁጥር ወደ 10 ቁጥር ከተዘዋወረ በኋላ ከሽማግሌው ጋር ባደረገው የመልዕክት ልውውጥ ነበር፡፡ ሽማግሌው የዴንማርክ ነዋሪ ሲሆን ወደኢትዮጵያ የመጣው ሚስት ለማግባት ነበር፡፡ ዕቅዱ ተሳክቶለት ኢትዮጵያ በስደት ላይ የነበረችውን ለግላጋ ወጣት በእጁ አስገብቶ ወደ ዴንማርክ ለመመለስ አዲስ አበባ ሲመጣ ነው ከነሚስቱ ጫጉላቸውን ማዕከላዊ እንዲያሳልፉ የተገደዱት፡፡
ፈረሃን ስለሽማግሌው እዲያጣራለት ባዘዘው መሠረት አንዱ ቀን አመሻሽ ላይ ፋይሰል ለአጎቱ ልጅ መልዕክት ላከ፡፡ መልዕክቱ የሽማግሌውን እና ሴቷን ግንኙነት ካስረዳ በኋላ ሽማግሌው ለምን የፈረሃንን መልዕክት መመለስ እንዳቆመም ያትት ነበር፡፡ ሽማግሌው ከፈረሃን ጋር ግንኙነት ያቋረጠው የመጀመርያ ቀን መልዕክት ሲለዋወጡ ስለባሕሪው እንዲመሰክርለት የጠየቀው ፈረሃን የሆነ ጥፋት አጥፍቶ ለመሸፈን እየሞከረ እንደሆነ ስለተሰማው ነበር፡፡
***
ፈረሃን የሽማግሌውን ታሪክ ለኡመድ አጫውቶት ነበር፡፡ አንድ ቀን ከሰዓት ፀሐይ እየሞቁ ከፊት ለፊታቸው ካለው ጣውላ ቤት አንዱ ክፍል በር ላይ ፔርሙዝ እያጠበች የነበረችውን ሱማሌ እንዲያይ ፈረሃን ለኡመድ ጠቆመው፡፡ ኡመድ ልጅቷን ካያት በኋላ ፈረሃን ምን ሊነግረው እንደፈለገ ጠየቀ፡፡ ፈረሃን ወጣቷ ሱማሌ 2 ቁጥር ያለው ሽማግሌ ሚስት እንደሆነች ነገረው፡፡ 2 ቁጥር ውስጥ የነበረውን ሽማግሌ በደንብ የሚያውቀው ኡመድ በባልና ሚስቱ መኻከል ያለው የዕድሜ ልዩነት ደንቆት ጭንቅላቱን ወዘወዘ፡፡ ኡመድ መገረም የገባው ፈረሃን በእስር ቆይታው አሳክቶ የተናገራት የመጀመርያም የመጨረሻም ዓረፍተ ነገር ወረወረ፡ ‹‹ገንዘብ ካለህ በሰማይ መንገድ አለ፡፡›› ፈረሃን አማርኛ አሳክቶ መናገሩ ለኡመድ ሌላ ግርምት ሆነበት፡፡ በመጀመርያ ስለምን እንዳወሩ እንኳን የማያውቁት የ7 ቁጥር እስረኞች ፈረሃን በሰማይ መንገድ መኖሩን ለመጠቆም የተጠቀመበት የእጅ እንቅስቃሴ እና በአማርኛ በቅጡ ለመግባባት ሳይችል ይህችን ተረት መተረቱ ደንቋቸው እየተሳሳቁ 10 ደቂቃዋ አልቃ ወደክፍላቸው ተመለሱ፡፡
***
በእስር ቆይታው መጀመርያ ላይ ለሁለት ቀናት በድምር አንድ ሰዓት ለማይሞላ ምርመራ ከመወሰዱ ውጭ ሌሎች ክፍሉ ውስጥ ያሉ እስረኞች እየተመላለሱ ሲመረመሩና ሲደበደቡ እሱ ሌላ ምርመራ አልተደረገበትም፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ በጥዋት ሥሙ ተጠራ፡፡ አብረውት ፍርድ ቤት ከሄዱት ሱማሌዎች ውስጥ ከውጭ ሀገር የመጡት ሦስቱ በተለምዶ ሸራተን ወደሚባለው ምርመራ የጨረሰ ሰው ወደሚቆይበት ማረፊያ ቦታ ተዘዋውረዋል፡፡ ሳይቤሪያ የቀሩት እሱና የአጎቱ ልጅ ፋይሰል ብቻ ነበሩ፡፡ የነመውሊድ ዝውውር በተደረገ ማግስት በጥዋት ሲጠራ እሱም ወደሸራተን ሊሄድ እንደሆነ ገምቶ ነበር ነገር ግን ጥሪው እቃውን እንዲይዝ ትዕዛዝ ባለመጨመሩ ግምቱ የተሳሳተ እንደሆነ ተረዳ፡፡
የጠራው ፖሊስ ሁል ግዜ ምርመራ የሚሄድ ሰው እንደሚደረገው ፈረሀን እጅ ላይ ካቴና አጠለቀለት፡፡ ምርመራ በተደረገለት ሁለት ቀናት ሹራቡን አስወልቆ ፊቱን ያሰረበትን ቦታ ዝም ብሎ ሲያልፈው ‹ዛሬ መርማሪዎቼን ላያቸው ነው፡፡› ሲል አሰበ፡፡ ከ7 ቁጥር ጠርቶ ይዞት የመጣው መለዮ የለበሰ ፖሊስ ለሌላ ሲቪል ለለበሰ ፖሊስ አስረከበው እና ከአዲሱ ሰውዬ ጋር ሆኖ አሮጌ ጣውላ ደረጃዎችን አልፎ አንድ ቢሮ በር ላይ እንዲቆም ታዘዘ፡፡ በሩ ላይ ሲቪል የለበሰው ፖሊስ ፈረሃን እጅ ላይ የነበረውን ካቴና ፈትቶ ወደክፍሉ እንዲገባ በሩን ከፈተለት፡፡ ፈረሃን ክፍሉ ውስጥ ሲገባ የእናቱ ወንድም (የፋይሰል አባት) ከተቀመጡበት ተነስተው ተጠመጠሙበት፡፡ ሁለት ሳምንት የገቡበት ጠፍቷቸው ሲያፈላልጉ ቆይተው ከጎዴ መጥተው ነበር ያገኙት፡፡
ወደማረፊያ ቤት ሲመለስ ዓይኖቹ ቀልተው ፊቱ ፍም መስሎ ነበር፡፡ አጎቱን በማግኘቱ የደስታ እምባ ያነባውን ያክል ያለምክንያት እስር ቤት መወርወሩ ያጠራቀመበት እልህ ላይ የልጆቹ እና ሚስቱ ናፍቆት ተጨምሮበት በአንሶላ ተጠቅልሎ እዬዬውን አቀለጠው፡፡ ክፍሉ ውስጥ የነበሩት እስረኞች ‹‹ምን አግኝተውበት ደበደቡት?›› ሲሉ አንሾካሾኩ፡፡
ምሣ ሰዓት ከመድረሱ በፊት ከቤተሰብ የተቀበሉትን ስንቅ ለእስረኞች የሚያድሉት ፖሊሶች መጥተው የፈረሃን ሥም ተጠራ፡፡ ክፍሉ ውስጥ የነበሩት ሁሉ ጠዋት የተጠራው ቤተሰብ ለማግኘት እንደሆነ ገባቸው፡፡ ኡመድ ፈረሃንን ቀስቅሶ የመጣለትን ምግብ እንዲቀበል አደረገ፡፡ የፈረሃን አጎት ያመጡትን የሱማሌ እንጀራ ከሞፎ እና በሪስ ጋር በሉ፡፡ የሱማሌ እንጀራው ለኡመድ በጣም ስለተመቸው ሁልግዜ አጎቱ ሲመጡ ይዘው እንዲመጡ እንዲጠይቃቸው ፈረሃንን ተለማመጠው፡፡
***
አብረውት 7 ቁጥር ውስጥ የነበሩ እስረኞች ሁሉ በምርመራ ወቅት ተደብድበዋል መባሉን አምኗል፤ ከዝምተኛው መላጣ ሽማግሌ በቀር፡፡ ሰውየው ከአክሱም አካባቢ እንደመጡ ከተነገረው ጀምሮ እንደውም በጥርጣሬ ነው የሚያያቸው፡፡
አንድ ቀን እኝሁ ሽማግሌ ተጠርተው ወጡ፡፡ ግማሽ ቀን ሙሉ ቆይተው ሲመለሱ የሸሚዛቸው ቁልፎች ግማሾቻቸው ተበጥሰው ቀሪዎቹ ደግሞ ተዛንፈው ተቆልፈው ነበር፡፡ እንደተመለሱ ማንንም ሳያናግሩ ወደፍራሻቸው አምርተው ተኙ፡፡ ተደብድበው እንደሆነ ከፈረሃን በስተቀር ሁሉም አምነዋል፡፡ ቆይተው ሲነሱ ኡመድ አግባብቶ ምግብ እንዲበሉ ካደረገ በኋላ ምን እንደተፈጠረ ጠየቃቸው፡፡ የተፈጠረውን ለኡመድ ሲያስረዱት ዓይኖቻቸው እምባ አቅርረው፣ ድምፃቸውን ሲቃ እየተናነቀው እና የሰውነታቸው የደምስሮች ሁሉ ተገታትረው ነበር፡፡ ፈረሃን ሽማግሌው ለኡመድ የነገሩትን እንዲተረጉምለት ወተወተው፡፡ በሐዘን ድባብ ውስጥ ሆኖ ኡመድ ለፈረሃን የሆነውን ነገረው፡፡ እንዲህ ነበር የሆነው፤ አቶ ጎበዛይ ገ/ስላሴ ጭቅጭቅ እና እንግልቱ ሲሰለቻቸው ግዜ የማያውቁትን ‹አውቃለሁ›፣ ያልሰሩትን ‹ሰርቻለሁ› ብለው አምነው ለፖሊስ የተከሳሽነት ቃላቸውን ይሰጣሉ፡፡ ይህ አልበቃ ያለው ፖሊስ ይህንኑ ቃል ፍርድ ቤት ቀርበው ዳኛ ፊት ቃላቸውን እንዲሰጡ ፍርድ ቤት ይወስዷቸዋል፡፡ ፍርድ ቤት ዳኛ ፊት ሲቆሙ ፈፅመኻል ስለተባሉት ወንጀል ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለና እንደውም ፖሊስ አስገድዶ የተከሳሽነት ቃል እንደተቀበላቸው በመግለጽ ‹‹በሕግ አምላክ ፍረዱኝ›› ብለው ይጮኻሉ፡፡ በነገሩ እጅግ የበገኑት መርማሪዎቹ ከፍርድ ቤት ሲመለሱ በቀጥታ ወደምርመራ ክፍል ወስደው ልብሳቸውን አስወልቀው መሬት ላይ ጥለው እየረጋገጡ ደበደቧቸው፡፡
ፈረሃን በሰማው ነገር ግራ በመጋባት ‹‹ይህማ ሊሆን አይችልም!›› ሲል ድምፁን ከፍ አድርጎ ተናገረ፡፡ በዕድሜ የገፋ ሽማግሌ፤ ለዛውም እንኳን እንዲህ ሊንገላቱ ቀርቶ ጭራሽ ይታሰራሉ ብሎ ከማያስባቸው የትግራይ ተወላጅ ላይ ተፈፀመ የተባለውን ማመን አልቻለም፡፡ ኡመድ ‹‹አንድ ስለአቶ ጎበዛይ የማታቀው ነገር ልጨምርልህ፤ ሕወሓት ከደርግ ጋር ባደረገችው ትግል ውስጥ ለ11 ዓመታት አብረው የታገሉ ሰው ናቸው፡፡ እዚህ አብረውን የነበሩት ቄስ ጎይቶም ወደ 8 ቁጥር ከመቀየራቸው በፊት የውስጥ እግራቸውን ተገርፈዋል፡፡ እዚህ የምታያቸው ሼህ ጀማል የአስም ሕመማቸው እንዲያሰቃያቸው ነው ሽንት ቤት አጠገብ ያለ ክፍል ውስጥ የታሰሩት፡፡ ሌላ ብዙ ልልህ እችላለሁ፤ የማዕከላዊ ግፍ እና ማዋረድ በዕድሜ፣ በፆታ፣ በዘውግ ወይንም በሃይማኖት አባትነት የሚለይ አይደለም›› አለ ንዴቱ እንዳይታወቅበት እየጣረ፡፡
ፈረሃን ኢትዮጵያን እየገዛ ስላለው ስርዓት ያስብ የነበረው እና እራሱ እየመሰከረ ያለው ክፉኛ ተጋጭተው እስካሁን እውነቱን ለመፈለግ ያደረገው ሙከራ ትንሽነት አሳፈረው፡፡
***
ቀኑ መሽቶ እየነጋ 28 ቀን አለፈና የቀጠሮው ቀን ደረሰ፡፡ ብዙዎቹ አብረውት 28 ቀን ያሳለለፉት የ7 ቁጥር እስረኞች የሚለቀቅበት ቀን እንደሆነ ገምተዋል፡፡ ፖሊስ ከዚህ በላይ ፈረሃንን ማቆየት የሚፈልግበት ምክንያት አልታያቸውም፡፡ በ28 ቀን ውስጥ ሁለት ቀን ለዚያውም ተደምሮ አንድ ሰዓት እንኳን የማይሞላ ምርመራ የተደረገበት ሰው ለምን ለተጨማሪ ግዜ ይፈለጋል?
ጠዋት ሲጠበቅ የነበረው የፈረሃን ፍርድ ቤት ጥሪ ሳይመጣ ቀረ፡፡ ምሣ ሰዓት በመድረሱ የሁሉም ተስፋ አደገ፡፡ በቀጠሮው ቀን ፍርድ ቤት ካልተወሰደ፣ ፖሊስ ብቻውን ቀርቦ ምርመራዬን ስለጨረስኩ የግዜ ቀጠሮ መዝገቡ ይዘጋልኝ ብሏል ማለት ነው፡፡ ይህ ከተከሰተ ደግሞ ከሁለት ነገሮች አንዱ ይከተላል ማለት ነው፡፡ የመጀመርያው ከእስር መፈታት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የክስ ምስረታ ነው፡፡ በአንድ ሰዓት ምርመራ ደግሞ ክስ ሊመሰረት እንደማይችል እና እነዚህን መሳሰሉ ትንተናዎች እየተጨዋወቱ ምሣ ከበሉ በኋላ በድንገት በሩ ተከፈተና ፈረሃን ተጠራ፡፡ ክፍሉ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ሁሉ ሲጠበቁት የነበረው የፍቺ ጥሪ ግን አልነበረም፡፡
ፈረሃን ከሄደበት ተመልሶ ሲመጣ እጅግ ተስፋ መቁረጥ ይስተዋልበት ነበር፡፡ ተጨማሪ 28 ቀናት እንደተቀጠረበት ለኡመድ ሲያስረዳው ሁሉም ተደናገጡ፡፡ እየሆነ ያለውን በፍፁም ሊረዱት አልቻሉም፡፡ ‹‹ምን ዓይነት ዳኛ ናት? 28 ቀን ምን ሠራችሁ ብላ ሳትጠይቅ ሌላ 28 ቀን የምትሰጣቸው?›› ሲል ኡመድ አማረረ፡፡
***
ቅዳሜ ግንቦት 30ቀን 2006 ዓ.ም ከሰዓት ፈረሃን ካረፈበት ሆቴል ትንሽ የእግር ጉዞ ለማድረግ ፈልጎ እየወጣ እንዳለ የሆቴሉ የእግዳ መቀበያው ላይ አንድ የሚያውቀው ፊት ያየ መሰለው፡፡ ተጠግቶ ሲያረጋግጥ የሚኖርበት ሴንት ፖውል ሚያውቀው ሱማሌ ወጣት ነበር፡፡ ያረፈበት ሆቴል አዲስ አበባ ውስጥ ሱማሌዎች የሚበዙበት አካባቢ እንደሚገኝ እና ሆቴሉ ውስጥም በብዛት የሚያርፉት የሱማሌ ዲያስፖራዎች እንደሆኑ ፋይሰል ነግሮት ስለነበር በሺዎች ማይል ርቀት የሚያውቀው መውሊድን እዚህ ማግኘቱ ብዙም አልገረመውም፡፡ መውሊድ ፈረሃን ያቀረበለትን ግብዣ ተቀብሎ የአዲስ አበባ ከሰዓት አየር እቀዘፉ የቦሌን አካባቢ ቃኙት፡፡ ከመስቀል አደባባይ እስከ ቦሌ ዓለም አቀፍ ጢያራ ማረፊ ድረስ የተዘረጋው አፍሪቃ ጎዳና የተሠራበት ደረጃና ከጎዳናው ግራና ቀኝ የተሰለፉት ሕንፃዎችን አይተው ግርምታቸውን ተለዋወጡ፡፡ ፈረሃን አብሮት ላለው የሴንት ፖውል ወዳጁ ሌላ የተደመመበት ጉዳይንም አጫውቶት ነበር፡፡ አባቱን ለማስታመም የሚሄድበት ጎዴን ከጅግጅጋ የሚያገናኝ አዲስ የአስፋልት መንገድ በቅርቡ መዘርጋቱን እና ቀድሞ መንገዱ ከሚወስደው ግዜ አሁን በግማሽ እንደቀነሰ በአድናቆት አጫወተው፡፡
በአንፀባራቂ ሕንፃዎቹ መስታወት ውስጥ የድኃ ኢትዮጵያውያን ችጋር አልታያቸውም ነበር፡፡ አዲስ እና አሮጌ መኪኖች እንደፈለጉ የሚፈሱበት ጎዳና ኢትጵያውያን ላይ የተጫነው ጭቆና ማራዘሚያ እንደሆነ አልተገነዘቡም፡፡ ፈረሃን እና መውሊድ እነዚህን ጉዳች ለመረዳት በከባዱ መንገድ መማር ነበረባቸው፡፡ ከዛች አስደሳች ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በድጋሚ የተገናኙት ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበው ፖሊስ በሽብርተኝነት እንደሚጠረጥራቸው የሰሙ ግዜ ነበር፡፡
ሦስተኛ ተጠርጣሪ ሆኖ ችሎት ከጎናቸው የቆመው ኢብራሂም በትውልድ ኬንያዊ ሱማሌ ሲሆን ከሚኖርበት አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት በአሜሪካን ሚኒሶታ ግዛት ተገኝተው ኢትዮጵያ እና ክልላቸው ለኢንቨስትመት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠራቸውን እና ማንም ሰው ኢንቨስት ለማድረግ ቢመጣ በደስታ እንደሚያስተናግዱት የገቡትን ቃል አምኖ እና አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን በየግዜው ስለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት መመንደግ ሚያወጡት ዘገባ አጓጉቶት ከእናት ሀገሩ ኬንያ ይልቅ በኢትዮጵያ መዕዋለ ነዋዩን ቢያፈስ የተሻለ የትርፍ ሕዳግ እንደሚያገኝ ተማምኖ ነበር፡፡
***
ለሁለተኛ ግዜ ፍርድ ቤት በቀረበ ማግስት መጀመርያ ተጠሪ ፈረሃን ነበር፡፡ ማንም ባልጠበቀው ሁኔታ የማክሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም ጠዋት የመጣው ጥሪ ፈረሃንን ጓዙን ጠቅልሎ እንዲወጣ የሚያዝ ነበር፡፡ ፖሊስ ተጨማሪ 28 ቀን ፈረሃን እና ጓደኞቹ ላይ የጠየቀው ፍርድ ቤቱን ታዛዥነት ለማረጋገጥ ነው እንጂ ሌላ ምክንያት አልነበረውም፡፡ ፍርድ ቤቱም ታዛዥነቱን በሚገባ አረጋግጧል፡፡
በሕመም አልጋ ላይ የወደቁት አባቱን እንዲጎበኝ እንኳን ዕድል ሳይሰጠው ፈረሃን ወደመጣበት ሀገር እራሱ በቆረጠው ትኬት እንዲመለስ ቀጭን ትዕዛዝ ተሰጠው፡፡ የታዘዘውን ከማድረግ ውጪ አማራጭ አልታየውም፡፡ ምንያቱም ይህች በአዲስ ዓይኑ ማየት የጀመራት ኢትዮጵያ ናት፡፡ ፖሊሶች እየጎተቱ ከ7 ቁጥር ሲያስወጡት እምባው ጉንጩ ላይ እየወረደ እንዲህ አለ፤ ‹‹ኡመድ፤ የተበደላችሁትን አልረሳም፡፡ ሁሉንም እንደምናፍቃቸው ንገርልኝ፡፡››
---
ይህ ታሪክ ለአንባቢ ምቾት ሲባል ከተደረገለት ዘይቤያዊ ማስተካከያ በስተቀር እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡
---
ተፈፀመ
Source: Zone9
No comments:
Post a Comment