Saturday, January 30, 2016

ማን ነው ተጠያቂው ? – ግርማ ካሳ

Ethio Prlama
Ethio Prlama
በፓርላማ ዉስጥ ካሉት ከ547ቱ የፓርላማ አባላት ዉስጥ ከትግራይ ክልል የሆኑት 38 ብቻ ናቸው። በኢሕአዴግ ፖሊት ቢሮና በኢሕአዴግ የማእከላዊ ኮሚቴ ዉስጥ ከሕወሃት የሆኑት አንድ አራትኛ ብቻ ናቸው። በሚኒስትሮች ምክር ቤት ዉስጥ ከትግራይ የተወከሉት የማውቃቸው ሶስት ብቻ ናቸው ( ዶር ቴዎድሮስ አዳኖም፣ ዶር ደብረ ጽዮን እና ማንነው ያ ስለጥንቆላ የሚያወራው ጌታቸው ረዳ)
ታዲያ እንዴት ነው ሕወሃት ብቻ፣ በአገሪቷ እየተፈጠረ ላለው ቀዉስ ተጣያቂ የሚሆነው ? የፓርላማው ቃለ ጉባኤ አባ ዱላ አይደሉም እንዴ ? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወላይታው ሃይለማሪያም ደሳለኝ አይደሉም እንዴ ? አባ ዱላና አቶ ኃይለማሪያም በሕጉ መሰረት በአገሪቷ አንደኛ እና ሁለተኛ የሚባሉት ትላልቅ ስልጣናት ያላቸው አይደለም እንዴ ? (አንዱ የ executive branch ሌላው legislative branch መሪዎች)
አንዳንድ ሰዎች ህወሃት ደህንነቱን እና መከላከያውይን ተቆጣጥሯል ይላሉ። አዎን ልክ ነው። ግን አቶ ኃይለማሪያም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ናቸው። በማናቸውም ጊዜ የጦር ኃይሎች የ ኤታ ማጆር ሹም የሆኑትን ጀነራል ሶሞራን እና የደህንነቱን ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ በሕጉ መሰረት መሻር ይችላሉ። አባ ዱላም በፓርላማ አስጠርተው፣ እነ ሶሞራን እነ እነ ጌታቸውን ተጠያቂ ማድረግ ይችላሉ። ( oversight እንደሚላበው)
ወደ ክልል ሲኬድ ደግሞ የክልል አስተዳዳሪዎች በኦሮሚያ እነ ሙክታር፣ በአማራው ክልል እንደ ገዱ አናዳርጋቸው አይደሉም ወይ ?
እንግዲህ አስቡት፣ ብአዴን እና ኦህዴድ ከኢሕአዴግ ግንባር ወጥተው፣ የራሳቸው ግንባር ቢፈጥሩ ፣ በሕጉ መሰረት በፓርላማ ማጆሪቲ ስለሚኖራቸው ፣ አዲስ መንግስት ሊመሰርቱ ይችላሉ።
በኔ ግምት፣ የትግራይ ህዝብ ብቻ ነው ህወሃትን በቀጥታ ቢከስና ቢቃወም የሚያምርበት። ለምን ቢባል፣ በዚያ እየገዛ ያለው ህወሃት ስለሆነ ነው። በተቀረው ኢትዮጵያ ክልሎች ግን 100% ሊጠየቁ የሚገባው ከሕወሃት ዉጭ ያሉ የኢሕአዴግ ድርጅቶችና አጋር ደርጅቶች ናቸው ።
የሚካድ አይደለም። ህወሃት በብዙ ቦታዎች እጁ አለበት። ግን እጁ እንዲኖርበት የፈቀዱት ከሕወሃት ዉጭ ያሉ ደርጅቶች ናቸው። ለምሳሌ በሕወሃቶች የተሞላውና የ”አገር ደህንነትና የጸረ-ሽብር ግብረ ኃይል” ብሎ ራሱን የሚጠራ አሸባሪው ቡድን፣ በኦሮሚያ ግፍና ጭካኔ ሲፈጽም፣ የክልሉ ጨፌ አንድ አቋም ቢወስድ ኖሮ፣ እነ አቶ ሙክታር አቋም ቢወስዱ ኖሮ፣ አባ ዱላ በአስቸኳይ ፓርላማዉን ጠርተው እነ ሳሞራን አስጠርተው ቢጠይቁ ኖሮ፣ ይሄ ሁሉ ሰው ሰው አይሞትም ነበር። ሕዝቡ ያሳያዉን ድፍረት አንድ አስረኛ እንኳን የኦህዴድ ከፍተኛ አመራር አባላት ቢያሳዩ ኖሮ፣ ሌላው ይቅር በአስቸኳይ የአጋዚ ጦር ከኦሮሚያ ካልወጣ ከኢህአዴግ ግንብር እንወጣለን የሚል ማስጠንቀቂያ ቢሰጡ ኖሮ፣ ነገሮች አሁን ባለው መልኩ አይቀጥሉም ነበር።
- Source: satenaw

No comments: