Friday, January 22, 2016

“የምክር ቤት ሰብሳቢው የፓርቲውን አባላት እና የዮናታን ቤተሰቦችን፣ በይፋ ይቅርታ መጠየቅ አለበት”

አቶ ዮናስ ከድር
   የሰማያዊ ፓርቲ የምክር ቤት አባል

የሰማያዊ ፓርቲ ሥነ ሥርአት ኮሚቴ ባስተላለፈው የዲስፕሊን ቅጣት የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ እና የምክር ቤት አባሎችን ከፓርቲው አሰናብቷል። ከተሰናበቱ መካከል አቶ ዮናታን ተስፋዬ የቀድሞ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ አቶ እያስጴድ ተስፋዬ፣ አቶ ዮናስ ከድር እና አቶ ጋሻነህ ላቀ ይገኙበታል።
ለመሰናበታቸው መነሻ ተደርጎ የተወሰደው አመለካከታቸውን እምነታቸውን ሃሳባቸውን በራሳቸው መረዳት በማንጸባረቃቸው በመጻፋቸው መሆኑን በስፋት ይታመናል። በተለይ ነፃዊነት (Liberalism) የፓርቲው የማዕዘን ድንጋይ መሆኑን በአደባባይ በተደጋጋሚ በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ሲደመጡ ሲነገሩ መክረማቸውን ለሚገነዘቡ ባለድርሻ አካላት፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ የወሰደውን እርምጃ በጥርጣሬ ነው የተመለከቱት። በአመራሮቹ መካከል የተፈጠረ የውስጥ ትግል ልዩነት እንጂ ከፓርቲው መሰረታዊ እሳቤ ጋር ግንኙነት የለውም የሚሉ ቁጥራቸው በርካታ ነው።
ዝግጅት ክፍላችን በፓርቲው ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ “ከተሰናበቱት አመራሮች” መካከል የምክር ቤት አባል የነበሩትን አቶ ዮናስ ከድርን አነጋግሯቸዋል። ፓርቲው ከተመሠረተ ከሁለት ወራት በኋላ የተቀላቀሉት እና የተላለፈባቸውን ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት አለው በማለት ይከራከራሉ። በፓርቲው ውስጥ መከፋፈል ያለ ተደርጎም መወሰድ የለበትም ይላሉ። እኛም በዚህ መልክ አስተናግደናቸዋል። 
በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት አንቀጽ (11) የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን፣ አምስት አባላት ያሉት የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን በጠቅላላ ጉባኤ ያቋቋማል፡፡ ተጠሪነቱም ለጠቅላላ ጉባኤ ሆኖ የሚከተሉት ስልጣንና ኃላፊነቶች ይኖሩታል ተብሎ ከተዘረዘሩት መካከል፤ ቁጥር (5) በስራ አሰፈፃሚው እና በብሔራዊ ምክር ቤት መካከል አለመግባባት ሲፈጠር ጉዳዩ በውይይት እንዲፈታ ጥረት ያደርጋል ችግሩ ካልተፈታ አስቸካይ ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራት ችግሩ እንዲፈታ ያደርጋል ሲል ይደነግጋል፡፡ እንዲሁም፣ በቁጥር (7) በፓርቲ ውስጥ የሚከሰቱ የአባላትም ሆነ የአመራር አካላት የሥነ ሥርዓት ጉዳዮችን የሚያይ የሥነ-ሥርዓት ኮሚቴ ያቋቁማል፡፡ በተጨማሪም (8)የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን በስነ-ስርአት ኮሚቴ የተሰጡ ውሳኔዎችን ይግባኝ ይመረምራል፤የመጨረሻ ውሳኔም ይሰጣል፡፡ ይህም በመሆኑ የኮሚሽኑ ውሳኔ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡
ሰንደቅ፡- ከሰማያዊ ፓርቲ የተባረራችሁበት መሰረታዊ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
አቶ ዮናስ፡- በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ከሰማያዊ ፓርቲ አራት አባላት መባረራችን መዘገቡ ከመረጃ እጥረት ነው በሚል በቀናነት እንወስደዋለን። ሆኖም ግልፅ መሆን ያለበት ከሰማያዊ ፓርቲ አልተባረርንም። አሁንም የሰማያዊ ፓርቲ አባሎች መሆናችን መታወቅ አለበት።
ሰንደቅ፡- የፓርቲው የብሔራዊ ሥነ-ሥርዓት ኮሚቴ ጥር 2/2008 ዓ.ም. በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ በአንቀፅ 42 ከባድ የሥነ ሥርዓት ቅጣት የሚያስከትሉ ጥፋቶች ስር በቁጥር 5 የፓርቲውን ዓላማ፣ ፕሮግራም፣ ፖሊሲ በመፃረር ሌላ የፖለቲካ ድርጅትን ወይም ቡድንን የደገፈ እና አብሮ የሠራ ወይም የሌላ የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆነ የሚለውን ጠቅሶ ማባረሩን አስታውቋል። እርሶ በበኩልዎ ደግሞ አልተባረርንም እያሉ ነው። መከራከሪያችሁ ምንድን ነው?
አቶ ዮናስ፡- ክሱ ተመሰረተ የተባለው በምክር ቤቱ ነው። ምክር ቤቱ ስብሰባ ተቀመጠ የተባለውም ጥቅምት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ የተገኙት የምክር ቤት አባላት ብዛት ሃያ አምስት ናቸው። ክስ እንዲመሰረት 13 ድጋፍ ሲገኝ፣ ተቃውሞና ድምጸ ተአቅቦ ደግሞ 12 ድምፅ ነበር። ከዚህ መረዳት የሚቻለው የክሱ ይዘትም ሆነ አቀራረብ የምክር ቤቱ አብላጫ ድምጽ ያላገኘ መሆኑ ነው።
በመሰረታዊነት የሚነሳው የህግ ስህተት እራሱን የምክር ቤት አባል አይደለሁም ብሎ የሚያምን፤ የብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢው የምክር ቤት አባል አይደለም ብሎ የሚያምነው ግለሰብ በድምፅ ተሳትፏል። እሱም አቶ እንዳሻው እምሻው ይባላል፣ አብዛኛው አባል እንደሚረዳው አቶ እንደሻው የጽ/ቤት ኃላፊ ነው። በመተዳደሪያ ደንባችን መሰረት የፓርቲ ጽሕፈት ቤትና አስተዳደር ኃላፊ ለፓርቲው በሙያ ብቃት የድጋፍ አገልግሎት ብቻ የሚሰጥና በፖለቲካ ውሳኔ የማይሳተፍ አካል ነው። ተጠሪነቱም ለሊቀመንበሩ እና ለብሔራዊ ምክር ቤቱ መሆኑን ይደነግጋል። ስለዚህም የአቶ እንደሻውን ሕገወጥ ድምጽ ከምክር ቤቱ ብትቀንሰው፣ ክሱ ይመስረት የሚሉ እና የማይሉ አስራሁለት እኩል ድምጽ ይኖራቸዋል። የክሱ አነሳስ ከመሰረቱ የተሳሳተ መሆኑን ከላይ የቀረበው መከራከሪያ አስረጂ ነው።
ሰንደቅ፡- እርስዎ ካቀረቡት መነሻነት የፓርቲው የብሔራዊ ሥነ-ሥርዓት ኮሚቴ ክሱን እንዴት ሊቀበለው ቻለ?
አቶ ዮናስ፡- ለምን ተቀበሉት የሚለውን ኮሚቴው ነው የሚያውቀው። እዚህ ላይ ምንም ማለት አልፈልግም። ሆኖም ግን ክሱ በምክር ቤቱ የተመሰረተ መሆኑ ሲነገር እንዳልነበር የደረሰኝ የክስ ወረቀት ግን የሚለው ሌላ ነው። ይሄውም፣ በታህሳስ 09 ቀን 2008 ዓ.ም. ከብሔራዊ ሥነ-ሥርዓት ኮሚቴ በደብዳቤ ቁጥር ብ/ሥ/ኮ/019/2008 በተፃፈ ወረቀት ላይ የሰፈረው “ከሳሽ አቶ ይድነቃቸው ከበደ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ ያቀረቡት ክስ ከፓርቲው ደንብ እና ከብሔራዊ ምክር ቤቱ መመሪያ ጋር የማይፃረር ሆኖ የብሔራዊ ሥነ ሥርዓት ኮሚቴው አግኝቶታል” የሚል ነው።  
ሰንደቅ፡- እርሶ ያሉት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የፓርቲው ማሕተም ባረፈበት ደብዳቤ መሰናበታችሁ ይታወቃል። ይህ ማለት ስንብታችሁ በፓርቲው መስመር ውስጥ ያለፈ ከመሆኑም በላይ በሌሎች አመራሮች ጭምር የሚታወቅ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። ከዚህ አንፃር ስንብታችሁ ሕግን አልተከተለም ማለት ይቻላል?
አቶ ዮናስ፡- በየትኛውም የፓርቲው አመራር ደረጃ ያለ አካል ቢያውቀውም ባያውቀውም፣ የፓርቲው የብሔራዊ ሥነ-ሥርዓት ኮሚቴ ውሳኔ የሰጠበት መንገድ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብን የጣሰ ነው። ይህም ሲባል በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት በአንቀፅ 44    የሥነ-ሥርዓት ኮሚቴዎች አወቃቀር ቁጥር 2 እና 3 ላይ የሰፈረው፣ (2) የሥነ-ሥርዓት ኮሚቴ አባላት ቁጥር በብሔራዊ ደረጃ 7፣ በወረዳና በመሰረታዊ ድርጅት ደረጃ 5 ይሆናሉ፤ (3) የሥነ-ሥርዓት ክሶችን ለመስማት ከኮሚቴው አባላት ከግማሽ በላይ ከተገኙ ምልዓተ ጉባዔ እንደተሟላ ይቆጠራል። 
ከዚህ አንፃር ከሰባት የፓርቲው የብሔራዊ ሥነ-ሥርዓት ኮሚቴ አባለት መካከል አራቱ ብቻ ነው የተገኙት። እነሱም ሃና ዋለልኝ፣ ሻምበል ካሳሁን ተገኝ፣ አቶ ሃሳን ቡሴር እና አቶ ሲሳይ ካሴ ናቸው። አራቱ አባላት በክሱ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል። አቶ ካሴ ለፓርቲው ልሳን ባሳወቀው መሠረት በውሳኔው ላይ ልዩነት እንዳለው ከመግለጽም በላይ በተወሰነው ውሳኔ ቃለ ጉባኤው ላይ አለመፈረሙን አስታውቋል። ተሰናበትን ለተባልነው አባላት ደብዳቤ መድረሱንም ከሰው መስማቱን አስረድቷል።
ይህ ማለት በእኛ ላይ የተወሰነው ውሳኔ በሶስት አባላት የተሰጠ በመሆኑ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ የጣሰ ነው፡፤ ስለዚህም የማንም ፈቃድ ሳንጠይቅ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት መሆናችን መታወቅ አለበት። ማንም አካል ከሕግ በላይ ሊሆን እንደማይችል መታወቅ አለበት።
ሰንደቅ፡- አቶ ዮናታን በእስር እያሉ የተወሰደባቸው እርምጃ ብዙ ባለድርሻ አካላትን አነጋግሯል። በዚህ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ዮናስ፡- ዮናታን ስለሆነ ብቻ አይደለም፣ አንድ ሰው በተመሰረተበት ክስ እራሱን መከላከል በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ እያለ ምንም አይነት ውሳኔ ሊተላለፍበት አይገባም። የሚገርመው ዮናታን ከስራ ገበታው በጸጥታ ኃይሎች ተይዞ ሲወሰድ ማንም አያውቅም ነበር። ይህን ተከትሎ በሰንደቅ ጋዜጣ አቶ ይድነቃቸው በሰጡት ቃል ዮናታን የት እንዳለ ከዮናታን ቤሰተቦች ጋር እየፈለግን ነበር ብለዋል። በኋላም ዮናታን መታሰሩ ታውቋል። ይህ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ ነው አቶ ይድነቃቸው በዮናታን ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የጠየቁት። ቢያንስ ከሞራል አኳያ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው የፈጸሙበት።
የሚገርመው ግን አቶ የሸዋስ አሰፋ በማዕከላዊ እስር ቤት በነበሩበት ወቅት አቶ ይድነቃቸው ከበደ የህግ ጉዳይ ኃላፊ ነበሩ። በአቶ የሸዋስ ላይ በተነሱ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ምንም አይነት መጠይቅ እንዳይቀርብ ተከራክረዋል። መከራከሪያቸው አቶ የሸዋስ በእስር ላይ በመሆናቸው፣ ራሳቸውን መከላከል አይችሉም የሚል ነበር። ዛሬ ላይ ግን በዮናታን ላይ በህገወጥ መንገድ ከፓርቲው እንዲሰናበት የሚቻላቸውን አድርገዋል። የሚያሳዝን የማይረሳ ተግባር ነው።
ሰንደቅ፡- መሰረታዊ የህግ ጥሰት መኖሩን ለማስረዳት ብዙ ርቀት ሄደዋል። በመከራከሪያነት የቀረቡት ነጥቦችም ሚዛን የሚደፉ ይመስላሉ። የብሔራዊ ሥነ-ሥርዓት ኮሚቴው ፍላጎት ምን ሊሆን ይችላል ብለው ይገምታሉ? በፓርቲው ውስጥ መከፋፈል አለ ብሎ መውሰድ ይቻላል?
አቶ ዮናስ፡- የብሔራዊ ሥነ-ሥርዓት ኮሚቴ ከህግ አግባብ ውጪ ውሳኔ መስጠት ለምን እንደፈለጉ እነሱ ቢመልሱት ይሻላል። በፓርቲው ውስጥ መከፋፈል የሚባል ነገር የለም። በውሳኔ አሰጣጥ እና የተለያዩ ሃሳቦች በማንጸባረቅ መነሻ ብቻ በፓርቲው ውስጥ ልዩነት አለ ወደሚል መደምደሚያ የሚያደርስ አይመስለኝም።
ሰንደቅ፡- አሁን ለተፈጠረው አለመግባባት መፍትሄው ምንድን ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ዮናስ፡- አቶ ይድነቃቸው ከበደ ወደ ኋላ ሊመለስ የማይችል ስህተት ሰርተዋል። ስለዚህም የኢትዮጵያን ሕዝብ በተለይ ደግሞ በጣም ያስቀየማቸውን የዮናታን ቤተሰቦች በይፋ ይቅርታ መጠየቅ አለበት። ይህ ሲሆን ነው ነገሮች ወደነበሩበት መመለስ የሚችሉት። ይህ ከሆነ በኋላ አስቸኳይ የብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ተጠርቶ፣ አቶ ይድነቃቸው ስልጣኑን ለምክር ቤት መመለስ አለበት።
Source: sendek news paper

No comments: