በትናንትናው ዕለት በፖሊስ የተያዙትና በአሁኑ ወቅት ካሳንቺስ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው የሚገኙት ወይንሸት ሞላ፣ ኤርምያስ ስዩም፣ ዳንኤል ተስፋዬና ማስተዋል ፈቃዱ በነገው ዕለት ጠዋት ቄራ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ ወይንሸት ሞላ ገና ሰላማዊ ሰልፉ ሳይጀመርና መስቀል አደባባይ ሳትደርስ በደህንነቶች የተያዘች ሲሆን ኤርምያስ ስዩም፣ ዳንኤል ተስፋዬና ማስተዋል ፈቃዱ ሲያዙ ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ተገልጾአል፡፡
አራቱም የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ፖሊስና ደህንነቶች ‹‹ድንጋይ በመወርወር፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመሳደብ፣ የፀጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት በመፈፀምና ህዝቡን ለአመጽ በማነሳሳት›› በሚል እንደወነጀሏቸውና በትናንትናው ዕለት ለተፈጠረው ሁሉ ተጠያቂ ሊያደርጓቸው እንደሚገልጉ ገልጸዋል፡፡
ገና ሰላማዊ ሰልፉ ሳይጀመር በደህንነቶች ተይዛ ነገር ግን ባልነበረችበት በደህንነቶችና በፖሊሶች ‹‹ድንጋይ በመወርወር፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመሳደብ፣ የፀጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት በመፈፀምና ህዝቡን ለአመጽ በማነሳሳት›› የሚል ወንጀል ፈጽመሻል እየተባለች የምትመረመረው ወይንሸት ሞላ ከፍተኛ የሆነ ወከባ እና እንግልት እንደደረሰባት ገልጻለች፡፡ በተመሳሳይ ኤርምያስ ስዩም፣ ዳንኤል ተስፋዬና ማስተዋል ፈቃዱ ከሌሎቹ እስረኞች ተለይተው የታሰሩበት ቤት ተዘግቶባቸው እንደሚውል ገልጸዋል፡፡ ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮም ከፍተኛ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
No comments:
Post a Comment