በግፍ ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖቻችንን በተመለከተ የአርበኖች ግንቦት 7 መግለጫ
April 19, 2015
ሀያ ስምንት ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን አይ ሲስ በተሰኘ ህሊና ቢስ፣ ፀረ-ሰው እና ፀረ-ስልጣኔ ቡድን በሊቢያ በአሰቃቂ ሁኔታ የመገደላቸው መርዶ ዛሬ ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደርሷል። ይህ አሰቃቂ መርዶ ልብን የሚሰብር ነው። አይ ሲስ በጥንት በጭለማ ዘመን እንኳን ባልነበረ ጭካኔ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ሰዎችን በማረድ የሚደሰት፤ በሰው ዘር ሁሉ ላይ የመጣ አውሬ መሆኑን ነብዩ መሐመድ አትድረሱባቸው ያሏቸውንም ኢትዮጵያዊያንን ጭምር በማረድ አረጋገጧል። ይህ አሰቃቂ ተግባር ምንም ዓይነት አመክኖ ሊቀርብለት የማይችል አረመኔዓዊ የሽብር ጥቃት ነው።
አርበኞች ግንቦት 7:የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በወገኖቻችን ላይ በደረሰው አሰቃቂ ግድያ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልፃል፤ ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን ይመኛል። ኢትዮጵያዊያን ሁሉ አይ ሲስን በጥብቅ እንዲያወግዙ፤ በአመቻቸው መንገዶች ሁሉ እንዲታገሉት አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል።
በዚህ አጋጣሚ የአይሲስን የሽብር ተግባራት ከእስልምና እምነት ጋር ማያያዝ ፈጽሞ ትክክል እንዳልሆነ፤ ብዙሃን ሙስሊሞች የአይሲስና መሰል ቡድኖችን አካሄድ የሚቃመው መሆኑን አርበኞች ግንቦት 7 ማስገንዘብ ይሻል። ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ከክርስቲያን ወገኖቻቸው ጋር ተዋደውና ተፋቅረው የኖሩና እየኖሩ ያሉ ሲሆን የሁለቱ ሀይማኖቶች ተከታዮች ተደጋግፎ መኖር ለሀገራችን ህልውና ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ የአርበኞች ግንቦት 7 እምነት ነው።
በያዝነው ሣምንት በወገኖቻችን ላይ እልቂት ሲደርስ የሊቢያ ብቸኛ ክስተት አይደለም። በደቡብ አፍሪቃ ወገኖታችን ከነሕይወታቸው በእሳት ተቃጥለው ተገድለዋል፤ በስለት ተዘልዝለዋል፤ ንብረታቸውን ተዘርፈዋል። በዛሬው ዕለት 700 ዜጎች የሜዲተራኒያን ባህር በጀልባዎች ሲሻገሩ መስመጣቸው ተሰምቷል። በየመን ደግሞ በርካታ ወገኖታችን በጦርነት እሳት ውስጥ እየተማገዱ ናቸው።
ኢትዮጵያዊያን በአገራችን የሰፈነውን የነፃነት እጦት፣ የፍትህ መጓደልና የኑሮ መክበድ ሸሽተን በሄድነት አገር ሁሉ የሚጠብቀን አሰቃቂ ሞትና ውርደት ሆኗል። ኢትዮጵያ ለኑሮ ያልተመቸችን በህወሓት አገዛዝ ብሉሽነት መሆኑ ጥርጥር የለውም። ይህንን ብልሹ አገዛዝ አስወግደን በምንወዳት አገራችን ተከብረን መኖር እንችላለን። ለኢትዮጵያዊያን ከኢትዮጵያ የተሻለ አገር የለም።
አርበኖች ግንቦት 7: የኢትዮጵያዊያን መከራ እንዲያበቃ ስደት ይብቃ ይላል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንደዝንባሌውና እንደችሎታው በሕዝባዊ አመጽ አሊያም የሥራ ቦታውና መኖርያው ሳይለቅ በሕዝባዊ እምቢተኝነት በተደራጀ መንገድ የህወሓትን አገዛዝን ይታገል። በሕዝባዊ አመጽና በሕዝባዊ እምቢተኝነት የህወሓት ፋሽስቶችን አስወግደን በአገራችን በነፃነትና በክብር እንድንኖር ሀይማኖትም ሆነ የዘር ሀረግ ሳይለየን በጋራ እንታገል የሚል ጥሪ ያቀርባል።
ዘላለማዊ ክብርና እረፍት ለግፍ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን
No comments:
Post a Comment