• ‹‹የታሰርነው የሰማያዊ ፓርቲ አባል በመሆናችን ብቻ ነው›› የሰማያዊ ፓርቲ አባላት
• ‹‹የሰማያዊ ፓርቲ አባል መሆን ሊያሳስር አይገባም›› ዳኛው
• ‹‹የሰማያዊ ፓርቲ አባል መሆን ሊያሳስር አይገባም›› ዳኛው
መንግስት አይ ኤስ አይ ኤስ ሊቢያ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን የጭካኔ እርምጃ ለመቃወም በጠራው ሰልፍ ላይ ፖሊስ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ ፈጥረዋል›› በሚል የያዛቸውን የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ሌሎችም በርካታ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ሚያዝያ 16/2007 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ፍርድ ቤቶች አቀረበ፡፡ ከእነዚህ መካከል ቄራ የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት በርካት ያሉት ታሳሪዎች ቀርበዋል፡፡ በነ ወይንሸት ሞላ የምርመራ መዝገብ 12 ታሳሪዎች የቀረቡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ዳንኤል ተስፋዬና ኤርሚያስ ጸጋዬ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ በተጨማሪም በእነ ወይንሸት የምርመራ መዝገብ ከቀረቡት 12 ታሳሪዎች መካከል 7ቱ ሴቶች ሲሆን በሌሎች ተናጠል መዝገቦችም ሴቶች ቀርበዋል፡፡ በቄራ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ከቀረቡት መካከል 5ቱ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
በታሳሪዎቹ ላይ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ ማነሳሳት›› የሚል ክስ ያቀረበው ፖሊስ ምርመራዬን አልጨርስኩም በሚል 14 ቀን ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቆ የነበር ቢሆንም ዳኛው በበኩላቸው ‹‹14 ቀን ብዙ ነው፡፡ ለምርመራ 6 ቀን ይበቃል፡፡ በመሆኑም በ6 ቀን ውስጥ የምትመረምሩትን መርምራችሁ የምትለቁትን መልቀቅ አለባችሁ›› በሚል 6 ቀን ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡ ወይንሸት ሞላ ‹‹የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባል ስለሆንኩ ብቻ ነው የተያዝኩት፡፡ ሰልፍ ሳይጀመር ነው የተያዝኩት፡፡›› ስትል ፖሊስ ያቀረበውን ክስ ስትቃወም በተመሳሳይ ዳንኤል ተስፋዬ ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ አባል ስለሆንኩ ብቻ ሰልፉ ካበቃ በኋላ ነው ታድኜ የተያዝኩት›› ሲል ክሱን ተቃውሟል፡፡ ዳኛው በበኩላቸው ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ አባል በመሆናችሁ የታሰራችሁ ካላችሁ የሚጣራ ይሆናል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አባል መሆን ሊያሳስር አይገባም፡፡ ይህን ፖሊስ መመርመር አለበት›› ብለዋል፡፡
ከእነ ወይንሸት በተለየ መዝገብ ነገር ግን በተመሳሳይ ክስ የቀረበበትና የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነው ማስተዋል ፈቃዱ 10 ቀን ተቀጥሮበታል፡፡ በመሆኑም እነ ወይንሸት ሚያዚያ 22 ቀን እንዲሁም ማስተዋል ፈቃዱ ሚያዚያ 26 ቀን ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከተከሳሾቹ መካከል ኢንጅነር አምሃ ታደሰ የተባለ ግለሰብ ቪዲዮ ሲያነሳ እንደተያዘ ቢገልጽም ፖሊስ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት›› የሚል ክስ አቅርቦበታል፡፡ በቄራ የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ከሰዓትም የሚቀርቡ ታሳሪዎች እንዳሉ ታውቋል፡፡
በሌላ የፍርድ ቤት ዜና ሰልፉ ካለቀ በኋላ ከምሽቱ 12 ሰዓት አካባቢ በፖሊስ ታድኖ የተያዘው ብሩክ የኔነህ የተባለው የሰማያዊ ፓርቲ አባል ዛሬ አራዳ የፌደራል ምድብ ችሎት ቀርቦ 12 ቀን የተቀጠረበት ሲሆን ሚያዝያ 28/2007 ዓ.ም ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
No comments:
Post a Comment