ሰማያዊ ፓርቲ መንግሥት ከስም ማጥፋት ዘመቻ ይታቀብ አለ
በኢትዮጵያውያን ላይ የአይኤስ አሸባሪ ቡድን የፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ ለማውገዝ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በተደረገው ሠልፍ ላይ፣ ሆን ብለው ብጥብጥ ያስነሱትና ሁከት እንዲፈጠር ያደረጉት፣ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና
አባላት መሆናቸውን ማረጋገጡን የፌዴራል ፖሊስ ገልጾ፣ ክስ እንዲመሠረት ለዓቃቤ ሕግ ማስተላለፉን አስታወቀ፡፡ በክሱም የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችንና አባላትን ጨምሮ ከ100 በላይ ሰዎች ተካተዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ አሰፋ በዩ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ተዘጋጅተውና ልምምድ አድርገው፣ በንብረትና በሰው ሕይወት ላይ አደጋ ለማድረስ፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴንና መላውን ዓለም ያሳዘነውን ሐዘን ሽፋን በማድረግ ሁከት ለመፍጠር ተዘጋጅተው የነበረ ቢሆንም፣ ሊከሽፍ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
በወቅቱ ከ1,000 በላይ የሁከቱ ተሳታፊዎች በቁጥጥር ሥር ውለው የነበረ መሆኑን የገለጹት ጄኔራል ዳይሬክተሩ፣ ያለምክንያት በግርግሩ ውስጥ ከመገኘት ባለፈ ምንም ዓይነት ዝግጅትም ሆነ ሌላ ዓላማ የሌላቸውን በመለየት፣ በዕለቱ በየክፍላተ ከተማቸው በተደረገ ማጣራት አብዛኛዎቹ ተለቀው 100 ያህሉ ብቻ ታስረው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ ከተደረገባቸው ተጠርጣሪዎች መካከል ረብሻውን በዋናነት በማቀጣጠል፣ በማደራጀትና በመምራት ከ20 በላይ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት በዋነኛነት ተሳትፊ መሆናቸው መረጋገጡን አቶ አሰፋ ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ አባላትም እንዳሉ አክለዋል፡፡
ብጥብጡን ተቀላቅለው ንብረት ለማውደምና በሰው ሕይወት ላይ አደጋ ለማድረስ ተዘጋጅተው የነበሩ አክራሪዎችም እንደነበሩ የገለጹት አቶ አሰፋ፣ በአጠቃላይ ከ100 በላይ በሚሆኑ ሁከትና ብጥብጥ ፈጣሪዎች ላይ ክስ እንዲመሠረት የሚያስችል ምርመራ መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡
በወቅቱ በተከሰተው ብጥብጥና ሁከት በፖሊስ አባላት ላይ በተደረገ የድንጋይ ውርወራ 41 የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ጉዳት እንደደረሰባቸው የጠቆሙት ጄኔራል ዳይሬክተሩ፣ በተለይ አምስት አባላት ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡ ሦስት የሠልፉ ተሳታፊዎችም ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቀዋል፡፡
መንግሥት በፖሊስ በተደረገው ምርመራ የብጥብጡ ዋና ምክንያትና አቀነባባሪ ሰማያዊ ፓርቲ መሆኑ መረጋገጡን ያስታወቀ ቢሆንም፣ ሰማያዊ ፓርቲም በበኩሉ የመንግሥት ፕሮፓጋንዳ በእሱ ላይ በዋናነት ያነጣጠረው ከምርጫው ለማስወጣትና ያለማንም ተቀናቃኝ ለማሸነፍ መሆኑን ገልጿል፡፡
ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በአሸባሪው የአይኤስ ቡድን በሊቢያ በግፍ በተገደሉ ኢትዮጵያውያን ምክንያት በመስቀል አደባባይ የተጠራው ሠልፍ በግጭት እንዲጠናቀቅ ያደረገው ሰማያዊ ፓርቲ ነው ለሚለው ውንጀላ መንግሥትን ወቅሶ ከእንዲህ ዓይነት ስም ማጥፋት ዘመቻው እንዲታቀብም ጠይቋል፡፡
ፓርቲውን ይህን ያስታወቀው ሚያዝያ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው፡፡
በዕለቱ መግለጫውን የሰጡት የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ የሕግ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ከበደና የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ አቶ እያስፔድ ተስፋዬ ናቸው፡፡
‹‹ማንኛውም ክስተት ከምርጫው ጋር ተያያዘም አልተያያዘም የምርጫ ወቅት እስከሆነ ድረስ፣ ከምርጫው ጋር የሚያገናኛቸው በርካታ ጉዳዮች ይኖራሉ፤›› በማለት ከተቃውሞው ሠልፍ በኋላ የተፈጠረውን ክስተት፣ መንግሥት ፓርቲውን ለማጥቃትና ለማዳከም እየተጠቀመበት እንደሆነ አቶ ዮናታን ገልጸዋል፡፡
‹‹ከምርጫው ጋር በቀጥታ የሚያገናኘው ነገር በመኖሩ ፓርቲው ጉዳዩን በሕግ የሚያየው ይሆናል፤›› ያሉት አቶ ዮናታን፣ ፓርቲው ስሜን አጠፉ ያላቸው ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ክስ ለመመሥረት እየተዘጋጀ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የፓርቲው ኃላፊዎች በመግለጫው ወቅት እንዳስታወቁት፣ ሚያዝያ 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ምሽት የሁለት ሰዓት ዜና ላይ የፌዴራል ፖሊስ ሰባት ሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና ከ20 በላይ አባላትን ማሰሩን አስመልክቶ የሰጠው መግለጫ ‹‹ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው፤›› በማለት ተቃውመዋል፡፡
በፌዴራል ፖሊስ የቀረበው የታሰሩ የአባላቱን ቁጥር ከመቃወም ባሻገር፣ ‹‹በአሁኑ ጊዜ በእስር ላይ የሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ቁጥር ስድስት ብቻ ነው፤›› በማለት ፓርቲው አስታውቋል፡፡ ‹‹እነዚህ ስድስት እስረኞች የፓርቲው አባላት እንጂ አመራሮች አይደሉም፡፡ ስለዚህ የረቡዕ ዕለቱን ሠልፍ ተከትሎ ፓርቲው የታሰረበት አንድም አመራር የለም፤›› በማለት ገልጿል፡፡
ፓርቲው ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. አውጥቶት በነበረው መግለጫ ስምንት ያህል አባላቱ መታሰራቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ በመግለጫው ወቅት በቁጥጥር ሥር ውለው ከነበሩት አባላት መካከል ቀጨኔ አካባቢ ወረዳ 9 ታስሮ የነበሩት አቶ ብሩክ የኔነህ የተባሉ የፓርቲው አባል መለቀቃቸው ተገልጿል፡፡ አቶ ብሩክ ፍርድ ቤት ቀርበው የ12 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸው እንደነበርም እንዲሁ ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከሠልፉ መጀመር ሰዓታት አስቀድሞ አባላቱ መታሰራቸውን የገለጸው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ‹‹በሠልፉ ላይ ለተፈጠሩት ማንኛቸውም ድርጊቶች ፓርቲውን ተጠያቂ ማድረግም በእጅጉ መሠረተ ቢስ ነው፤›› በማለት ተቃውሟል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም፣ ‹‹በፌዴራል ፖሊስና በመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ተደጋጋሚ የስም ማጥፋት ዘመቻ እየደረሰ ይገኛል፤›› ብሏል፡፡
መንግሥትና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ከዚህ እኩይ ተግባራቸው የማይታቀቡ ከሆነ፣ የሰማያዊን ስም በሐሰት በማጠልሸት ሥራ ላይ የተሰማሩ የመንግሥት ተቋማትንና ግለሰቦችን በሕግ ፊት ለማቆም ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ፓርቲው አስታውቋል፡፡
Source:: Ethiopian Reporter
No comments:
Post a Comment