Monday, June 6, 2016
የኢህአዴግ ባለስልጣናት እርስ በርስ ተወራረፉ
ግንቦት ፳፱(ሃያ ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ምንጮች እንደገለጹት ሰሞኑን በፌዴሬሽን ም/ቤት አዳራሽ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ም/ል ጠ/ሚኒስትርና የኢኮኖሚ ክላስተር መሪ ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤን “ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ተሰርቆ መውጣቱን ቀድሞ ካወቃችሁ ለምን በደህንነት መስመር ፈተናውን አስወጥተህ ወዲያውኑ እንዲረጋገጥ አላስደረክም፣ አሳፋሪ መግለጫ እያወጣችሁ ለምን የህዝብ መሳቂያ መሳለቂያ ታደርጉናላችሁ” ያሉዋቸው ሲሆን፣ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ጉዳዩን ለማድበስበስና ትችቱን ለማርገብ “ ድርጅታችን ስህተትን ይቀበላል” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። በአቶ ሃይለማርያም ንግግር ያልተደሰቱት የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ካሳ ተከለብርሃን “ ድርጅታችን ስህተትን ማረም ብቻ ሳይሆን እስከመቼነው በስህተት ላይ ስህተት የሚሰራው ፣ ስህተት ከመስራታችን በፊት ስህተት የማንሰራ መሆን አንችልም ወይ” ብለዋል።
በአዲስ አበባ ስላለው የመሬት ችግር በተነሳበት ውይይት ደግሞ አቶ መኩሪያ ሃይሌ “አዲስ አበባ ከተማ ተጣባለች ምን ይሻላል?” ሲሉ የፍትህ ሚ/ሩ በቅድሚያ ቤተ መንግስት አጠገብ ያለውን ቦታ ወደላይ ስሩበት ብለው መልስ ሰጥዋቸዋል።
አቶ አለማየሁ ተገኑ በበኩላቸው “ የማስትር ፕላኑ ነገር ስንት ጊዜ ይከለሳል? አልቆለት የለም ወይ?” የሚል ጥያቄ አንስተዋል። በእነዚህና በሌሎች አጀንዳዎች ላይ የተደረጉት ውይይቶች ሙሉ ዝርዝር ዘገባ ሲደርሰን የምናቀርብ መሆኑን ለመግልጽ እንወዳለን።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment