Friday, June 3, 2016

እነ አቶ በቀለ ገርባ በእስር ቤት የሚደርስባቸውን ስቃይ ለፍርድ ቤት ተናገሩ ።

ግንቦት ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፰ / ኢሳት ዜና :-  ዛሬ በባዶ እግራቸውና  በቁምጣና በውስጥ ካናቲራ ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19 ወንጀል ችሎት  የቀረቡት የኦሮሞ ፌዴራሊስት  ዶሞክራሲያዊ ንቅናቄ አመራር አቶ በቀለ ገርባ  ፦በባለፈው ቀጠሯቸው ጥቁር ልብስ ለብሰው ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ሲሉ  የእስር ቤቱ ፖሊሶች   ጥቁሩን ልብስ እንዲያወልቁ ሲያዟቸውአናወልቅም”  ማለታቸውን  በማውሳት፤ «የፈለግነውን የመልበስ ሕገ-መንግስታዊ መብታችን ነው፡፡ ጥቁር ልብስ የለበስነውም፤ 50ሺህ በላይ የአንድ ብሄር ተወላጆች እስር ቤት መገኘታቸውንና በዚህ ዓመትም በጥቂት ወራት ውስጥ 200-300 የሚደርሱ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች በመገደላቸው የተሰማንን ሀዘን ለመግለጽ ነው፡፡»ብለዋል።
ሀዘናችንን ልንገልጽ የነበረው የፍርድ ቤትን አሰራርን ምንም በማይነካ መልኩ በሰላም ነውያሉት አቶ በቀለ፤ ይህን ማድረግ  አይቻልም ተብለው ከመሰደባቸውም ባሻገር  ዛቻ  እንደተሰነዘረባቸው ገልጸዋል፡፡ ትናንት ከሰዓት በኋላ ዛሬ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ሰዎች ተለይተው ከየክፍላችን እንዲመጡ መደረጋቸውን የጠቀሱት የኦፌኮን አመራር፤ ልብሶቻቸውን ይዘው እንዲወጡ ከተደረጉ በኋላ  ከልብሶቻቸው መካከል ጥቁር ልብስ እየተፈለገ መወሰዱን ይናገራሉ፡፡
ይህን ተከትሎ ልብሶቻችንን በሙሉ ልትመልሱልን ይገባልብለው ጥያቄ ማንሳታቸውን የገለጹት አቶ በቀለ፤ይህን በመጠየቃችን ወደጨለማ ክፍል ወሰዱን፡፡ ከመካከላችን የተወሰኑትንም ክፉኛ ደበደቧቸው፡፡ የተደበደቡት ሰዎች እዚሁ ስላሉ ለችሎቱ መናገር ይችላሉ፡፡ ልብሶቻችን ሜዳ ላይ ተበትኖ ስለነበረ ሌሎች እስረኞች የሚፈልጉትን ወሰዱ  ወይም ተቀራመቱት፡፡ የተረፈውን አምጥተው ክፍላችን ውስጥ አስቀመጡት፡፡ዛሬም ድረስ ምግብ አልበላንም፡፡ እጆቻችን ጠዋት ድረስ በካቴና ታስሮ ነበር፡፡ በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ድርጊት ነው የተፈጸመብን፡፡ብለዋል።
አቶ በቀለ አክለውም፦የኦሮሞ ተወላጅ ብቻ እየተመረጠ ተደብድቧል፡፡ የታሰርንበት ቦታ በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ተቋም ነው፡፡አንተ ነህ እንዲህ የምታደርገው፡፡ እናገኝሃለንብለውኛልም፡፡ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ/ ተቀያሪ ማቆያ ቦታ ያዘጋጅልን፡፡ አሁንም ተመልሰን ቂሊንጦ ስንሄድ ምን እንደሚደርስብን አናውቅም፤ ስጋት አለን፡፡ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች እስካልተቀየሩ ድረስ ሕይወታችን የከፋ አደጋ ላይ ነው፤ በጣም ያሰጋናል፡፡ ለቀጣይ ቀጠሮ መገኘታችንምም እርግጠኞች አይደለንም፡፡ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በእስር ቤት ቤተሰቦቻቸውም  እንዳይጎበኙ  መከልከላቸውንና ዛሬም ፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ከገቡ በኋላ ሰዎች እንዳያዩ መድረጋቸውን የተናገሩት አቶ በቀለ፤፡፡ እንደዜጎች እየተቆጠርን አይደለም፡፡ መንግስት ለምን እንዲህ የተድበሰበሰ ነገር ይሠራል? ›› ሲሉ ጠይቀዋል።

አቶ በቀለ 22 ሰዎች  ጋር በጸረ-ሽብርተኝነት ወንጀል ተከስሰው የፍርድ ሂደታቸውን  እየተከታተሉ እንደሚገኙ ይታወቃል። ዛሬ ችሎት ከቀረቡት መካከል ሌሎች አምስት ተከሳሾችም ልክ አንድ አቶ በቀለ በባዶ እግራቸው ሆነው ጥቁር ቁምጣና የውስጥ ካናቲራ ለብሰው ይታዩ እንደነበር በስፍራው የተገኘው ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ በፌስ ቡክ ገጹ ባሰፈረው መረጃ ገልጿል።

No comments: