የቀድሞው አንድነት የኮምቦልቻ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊና በአሁኑ ወቅት የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪና የአካባቢው የምርጫ እጩ አቶ ዘሪሁን ገሰሰ ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 14/2007 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ኮምቦልቻ በማምራት ላይ እንዳለ ሸዋሮቢት ላይ በደህንነቶች መታፈኑ የታወቀ ሲሆን እስካሁንም የት እንዳለ አለመታወቁን ቤተሰቦቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
አቶ ዘሪሁን ቀደም ሲል ‹‹የሰማያዊ ፓርቲ አባል መሆን አትችሉም፡፡ ለትግስቱ አወሉ እውቅና ካልሰጣችሁ እናስገርፋችኋለን›› እየተባሉ ከፍተኛ ጫና እንደሚደርስባቸው ለነገረ ኢትዮጵያ መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡ ‹‹ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ያለህን ግንኙነት አቁም፡፡ በዚህ ሶስት ቀን ውስጥ ለቅቀህ ውጣ፡፡ በስልክ ከማንም ጋር እንዳታወራ፡፡ የነገርንህንም ለማንም መንገር የለብህም›› ተብያለሁ ሲል አቶ ዘሪሁን ጫና ይደረግበት እንደነበር ለነገረ ኢትዮጵያ መግለጹ ይታወሳል፡፡
አቶ ዘሪሁን በትራንስፖርት ውስጥ ከአዲስ አበባ አብረውት በተሳፈሩ የደህንነት ሰዎች ሸዋሮቢት ላይ ታፍኖ ለጊዜው በአንድ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ቆይታ አድርጎ የነበር ቢሆንም ወዲያውኑ ወደ አዲስ አበባ መዛወሩን ቤተሰቦቹ ከፖሊስ ጣቢያ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ሸዋሮቢት ሄደን ዘሪሁንን ማግኘት አልቻልንም፡፡ ፖሊሶች እንደነገሩን ከሆነ ዘሪሁን ሲቪል በለበሱ የደህንነት ሰዎች ወደ አዲስ አበባ ተወስዷል፡፡ አዲስ አበባ የት ቦታ እንደወሰዱት ግን አላወቅንም፡፡ ፖሊስን ለምን ለሲቪል ሰዎች አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ስንላቸው ‹እኛ ምን እናድርግ የበላይ ትዕዛዝ ነው፡፡ የደህንነት ሰዎች መሆናቸውን መታወቂያ አሳይተውናል› አሉን፡፡ አሁን እኛ ወደ አዲስ አበባ ሄደን ለማጣራት ጉዞ ላይ ነን›› ስትል ባለቤቱ ለነገረ ኢትዮጵያ ተናግራለች፡፡
No comments:
Post a Comment