Sunday, February 22, 2015

ህወሃት ምንድን ነው? – ለታው ዘለቀ

በቅርቡ የህወሃት ኣርባኛ ዓመት ለየት ባለ መንገድ መከበሩ ገርሞኛል። በየዓመቱ እንደሚከበር ሁላችን እናውቃለን። ይሁን እንጂ የዓርባኛ ዓመቱ በዓል እንዲህ ለምን እንደተወራለት ለምን የሌላ ኣገር መሪ ሳይቀር እንደተጋበዘበት ኣልገባኝም። ብዙ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ለየት ያለ ድግስ የሚደረገው የኢዮቤልዩ በዓል ሲከበር ነው። የሆነው ሆኖ የመነሻ ኣሳቤ ይሄ ኣይደለም። ህወሃት ኣርባኛ ዓመት በዓሉን ሲያከብር እኔ በህወሃት ተፈጥሮ ስደመም ነበር። በርግጥ ኢትዮጵያ ኣሁን ላለችበት የተመሰቃቀለ ህይወት ሲንከባለሉ የመጡ ኣንዳንድ ችግሮች ኣስተዋጾ ቢያደርጉም የችግሩ ከፍተኛ ኣስተዋጾ ኣድራጊ ግን ህወሃት ነው። በየክልሉ የህወሃት ተከታዮች ኣስተዋጾኣቸው እንዳለ ሆኖ የህወሃት ድርሻ ግን በጣም ገዝፎ ይታያል። ግን …ግን ለምንድነው በህወሃት መራሹ መንግስት ጊዜ ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ኣስከፊ ችግር ውስጥ የገባችው? ብለን መጠየቅ ካማረን የህወሃትን ተፈጥሮና ኣነሳስ በሚገባ መረዳትን ይጠይቀናል። ብዙ ሰው ህወሃትን የሚገልጸው ዘረኛ…… ኣምባገነን በሚል ነው። እውነት ነው ህወሃት ጎጠኛና ኣምባገነን ነው::ከዚህ በተሻለና በጠራ ሁኔታ የህወሃትን ስርና መሰረት መመርመሩ የበለጠ የህወሃትን ተፈጥሮ እንድንረዳው ያደርገናል። ኢትዮጵያ በየጊዜው የሚገጥማት ችግር በርግጥ እንዴት ከዚህ ከህወሃት ተፈጥሮ ጋር እንደሚመጋገብ አብርቶ ያሳየናል። ከዚህም በተጨማሪ የሃገሪቱን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ጉዳይ የበለጠ እንድንረዳው ያደርጋል። ህወሃት ምንድን ነው?  ምን ዓይነት ጉዳይ ኣንገብግቦት ነው የዛሬ ኣርባ ዓመት ወደ በረሃ የገባው? ብለን ከጠየቅን የህወሃት ኣባላት እንደሚሉት የነጻነት (Liberty) ጥያቄ ጉዳይ ኣይደለም። የነጻነት ጥያቄ ስል ትግራይንም ማለቴ ነው። ህወሃት የታገለው ለትግራይ ነጻነትም ኣይደለም ማለቴ ነው። ህወሃት ወደ ጫካ ሲገባ በርግጥ በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ ድባብ ማለትም “የብሄር ብሄረሰብ ጥያቄ” የሚባለው ነገር ኣስተዋጾ ቢያደርግም ዋናው የዚህ ቡድን ጥያቄ የነጻነት ጥያቄ፣ የእኩልነት ጥያቄ፣ ወይም የዴሞክራሲ ጥያቄ ሳይሆን  በወቅቱ ያበሸቀውና ወደ ጫካ የሰደደው ጉዳይ የኢኮኖሚ ጉዳይ፣ የከፋ ድህነት ጉዳይ ነው። የህወሃት መስራቾች በወቅቱ ስርዓት ኣኩርፈው ወደ ጫካ ሲገቡ በነበራቸው ግምገማ መሰረት ትግራይ በጣም የተጎዳች፣ ረሃብ ያጠቃት ናት። ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ህይወት ከትግራይ የማይለይ፣ የሃብት ክፍፍሉ በኣጠቃላይ ህዝብ ደረጃ ኣብዛኛውን የጎዳ መሆኑን ለማወቅም ሆነ ይህንን ለመመርመር ኣልፈቀዱም። በጠባቡ የትግራይን የኢኮኖሚ ህይወት፣ የገበሬውን ህይወት ኣይተው የትግራይ ሃርነት ትግል ጀመሩ። የዚህ ህዝብ ችግር በሃገር ጥላ ስር ኣብሮ ይፈታል የሚለው ነገር ያበሽቃቸው ነበር። የኣንድነትን ሃይሎች እንደነ ኢህዓፓ ኣይነቶችን እንደጠላት ያዩትም ለዚህ ነው። ትግራይን ነጥለው ሲያዩ ችግሩን ለመረዳት በጣም የቀለላቸው ይመስላል። ለመጡበት ቀየ የራራው ልባቸው ለኦሮሞው ለኣማራው ለሌላው ድሃ ህዝብ ኣልራራም ኣላቸው። እንዴውም ይህንን ስሜት ሳይንሳዊ ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ ሲጥሩ ታዩ። በመጀምሪያ ኣካባቢህን ከዚያ ሃገር ምናምን… እያሉ  በዚያ ስሜታቸው ከማፈር ይልቅ ለማስተማመን (justify ለማድረግ) ብዙ ጣሩ። ከፍ ሲል እንዳልነው ህወሃቶች “ትግራይ ሃርነት” ይበሉት እንጂ መራራው ጥያቄ ትግራይን ከሆነ ጨቋኝ ስርዓት ኣላቆ ኣንድ ነጻ ኣገር ለማድረግ ኣልነበረም። ጥያቄው የፖለቲካና የኣስተዳደር ነክ የነጻነት ጥያቄ ስላልሆነ በትግላቸው የመጀመሪያ ወራት ኣንዳንድ ኣባላት የመገንጠል ጥያቄ ኣንስተው የነበረ ቢሆንም ገና በማለዳ ይህ ኣሳብ ተቀጨ። ከፍ ሲል እንዳልኩት መራራው ጥያቄ የኢኮኖሚ ኦፖርቹኒቲ እንዴት ለኛ ሰፈር ይሰፋል? የሚል በመሆኑ ለዚህ ጥያቄ ብዙ መስዋእትነት ተከፈለ። ሌላው ኢትዮጵያዊ በደርግ ስርዓት ተጨቁኖ ስለነበረና ለውጥ ሽቶ ስለነበር የህወሃትን ተፈጥሮ መመራመር ኣልፈለገም። የኣንድ ኣካባቢ ኣርማ ለጥፈው ቢመጡም በኣንድያ የሃገር ስሜት ስር ያደገው ሰፊ ህዝብ ይህ ኣስተዳደጉ ስለ ህወሃት እንዳይመራመር ትኩረቱን ጋረደው። ኣንዳንዱ ሰው ደግሞ ከጅምሩ ብሄርተኞች መሆናቸው ባይዋጥለትም እስቲ ይሁን፣ ወንድሞቻችን ናቸው፣ ማእከላዊውን ስልጣን ሲይዙት፣ ኢትዮጵያ የምትባለውን ኣገር ሲያዩ፣ የሌላውን ህዝብ የከፋ ችግር ጠጋ ብለው ሲያዩ፣ ኣለማቀፋዊ መጋለጥ ሲኖራቸው ይተውታል ብሎ በልበ ሰፊነት ሲጠብቅ እነሆ ህወሃት ኣርባ ኣመቱን ትናንትና ሲያከብር ወይ ፍንክች ኣልተለወጠም። ወያኔ የዛሬ ሃያ ሶስት ዓመት የኢኮኖሚ ጥያቄ ዋና ጥያቄው ኣድርጎ ስልጣን ላይ ሲወጣ የኦፖርቹኒስቲክ ባህርይ (Opportunistic behavior) በሃጋሪቱ ፖለቲካ ኣካባቢ በሰፊው  ሰፈነ። ይህ ባህርይ የፖለቲካውን ጨዋታ ሁሉ እንዳይሆን እንዳይሆን ኣድርጎ ኣበላሸው:: ማህበራዊ ሃብታችንን በተለይም የመተማመን (የ trust) ሀብታችንን በጣም ጎዳብን። ህወሃት ትግራይ ትግራይ ይበል እንጂ በትግሉ ጊዜ ለትግራይ የገባውን ቃል መፈጸም ኣልቻለም። ከሁሉ በላይ የትግራይ ህዝብም በወያኔ ጎጠኛ ስሜት ተከፋ። ኣብዛኛውን የትግራይን ህዝብ ወደማይፈልገው ስሜት ውስጥ ከተተው። ስለዚህም ህወሃት ከትግራይም ሌላ ክብ ሰርቶ የዚያን ክብ እርሻ ለወጠ። የዚያን ጠባብ ክብ ኣባላት ነጋዴዎች ኪስ በገንዘብ ጠቀጠቀ።ስልጣኑን ለማቆየት ይረዳኛል በሚል በየክልሉ ጥቂት ጥቂት ክቦችን እየሰራ እነሱን የከፍተኛ የኢኮኖሚ ኦፖርቹኒቲ ተጠቃሚ እያደረገ እልፉን ህዝብ ሜዳ ላይ ጣለው። ቶሎ እንድናድግ ሃብት በኣንድ ኣካባቢ ይደልብልን በሚል ማታለያ ኣንዳንዴም የልማታዊ መንግስትን ስም ለጠፍ እያደረገ የኢኮኖሚውን ኦፖርቹኒቲ ሁሉ በጣም በጠበበ የህብረተሰብ ክብ ውስጥ ጠቀጠቀው። ይህ ቡድን መነሻው የኢኮኖሚ ችግር በመሆኑና የታገለውም ለዚህ በመሆኑ ነው ይህን የሚያደርገው። ይህ ቡድን ለኢኮኖሚ ጉዳቱ ማገገሚያ ኣድርጎ የወሰደው የፖለቲካ ስልጣንን መሳሪያ በማድረግ በመሆኑ በሃገሪቱ ፍትህ ኣድሮ ሲቀጭጭ ይታይ ጀመር። ያሳዝናል። ህወሃት ገና ከመነሻው የዚህ የኢኮኖሚ ጥቅም ጉዳይ ኣናዶት ጫካ መግባቱ ብቻ ሳይሆን የጎዳን ይህንን ጠባብ የሆነ የኢኮኖሚ እድል ለማስፋት ኢትዮጵያ የምትከፍለው ዋጋ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ነው። የጥቂት የህወሃት ደጋፊዎችን እርሻ ለመለወጥ፣ የጥቂት የሰርዓቱ ደጋፊ ነጋዴዎችን ኪስ ለመሙላት ኢትዮጵያ የባህር በር እስክታጣ፣ ኢትዮጵያ ድንበሩዋ ተቆርጦ እስክታንስ፣ በዘር ፖለቲካ ማህበራዊ ሃብታችን እስኪፈርስ ድረስ ዋጋ ትከፍላለች።እስከዚህ ጥግ የሄደ መስዋእትነት ይከፈላል። ይሄ ነው እጅግ ኣሳዛኙ ነገር። እነዚህን ኣላፊ ወይም ኣነስተኛ የኢኮኖሚ ድጋፎችን ለማድረግ ስለምን ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቱዋ እስኪደፈር ዋጋ ትከፍላለች? ብለን ስናስብ እስከ ሃቹ ያስደምመናል። ህወሃት ቢገነዘብ ኖሮ ይህን በዙሪያው የኮለኮለውን ጠባብ ቡድን ኣሁን የጠቀመውን ያህል ለመጥቀም ኢትዮጵያ ይሄን ያህል ዋጋ መክፈል ኣልነበረባትም። በኣምባ ገነን ኣገሮች ሙስና እንዳለ ሁሉ በሙስና የተለያዩ ጥቅሞችን ማደረግ ቢቻል የህወሃት ክፋት እስከዚህ ጥግ ይባል ነበር። ይህ ግን ኣልሆነም። ስርዓቱን ለመጠበቅ ሲባል፣ የነዚህን ጠባብ ቡድኖች ጥቅም ለመጠበቅ ሲባል በሱዳን በኩል ተቃዋሚ እንዳይነሳ የጠገበ መሬት ቆርሶ እስከ መስጠት መድረሱ በጣም ያስገርማል። ኢትዮጵያን የሚያህል ትልቅ ኣገር የባህር በር ጥያቄን ኣምርራ ከመጠየቅ ይልቅ ዝምታን መርጣ የነዚህን ጠባብ ጉጅሌዎች ኪስ መሙላት ይሻላል ለወያኔ። ይህ ስርዓት ከቀደሙት የሚለየው በዚህ ነው። የቀደሙት ስርዓቶች ኣምባገነን ሆነው የሆነ ክብን እየጠቀሙ ብዙውን ኣግልለው ይኖሩ ነበር። እነዚህ መንግስታት ይህን ቡድናቸውን ወይም ጉጅሌዎቻቸውን የሚጠቅሙት ግን የድሃውን ጉልበት እስከመበዝበዝ በሚደርስ ጭካኔ ነው። ህወሃት ግን ድሃውን ከመበዝበዝ ኣልፎ ኢትዮጵያን ራሱዋን ሉዓላዊነቱዋን ታሪካዊ ማንነቷን ሁሉ ሸጦ ነው ቡድኑን የሚጠቅመው። ደርግ ለዚህ ምሳሌ ነው። ሁሉ እንደሚያስታውሰው ጨካኝ በመሆኑ ኢትዮጵያ ብዙ ዋጋ ከፈለች። ነገር ግን ለስልጣኑ ሲል የሃገሩን ሉዓላዊነት ኣላስደፈረም። ደርግ ለስልጣኑ ሲል በሉዓላዊነት ላይ ቢነሳ ኤርትራን እንድትገነጠል ማድረግ ብቻ ይበቃው ነበር። ኤርትራን በሰላማዊ መንገድ እንድትገነጠል ቢስማማ ወይም ቀደም ብሎ በኮንፌደሬሽን ኣስተዳደር ችግሩን ቢፈታ ሃይሉን ኣሰባስቦ ወያኔን ያጠፋ ነበር። ህወሃት ወደ ስልጣን እንዲመጣ የሻእቢያ ኣስተዋጾ እጅግ የጎላ እንደነበር ይታወቃል። በመሆኑም ያለፉት መንግስታት በስልጣን ለመቆየትና ለግል ጥቅም ልክ የነበራቸው ሲሆን ያሁኑ መንግስት ግን ኢትዮጵያን መስዋእት እያደረገ ኣላፊ የሆነ ጥቅማጥቅም የሚቃርም በመሆኑ በታሪካችን ኣይነተው የማናውቀው ጉደኛ መንግስት ያደረዋል። በቅርቡ ኣርባ ኣመቱን ያከበረው ህወሃት በኣርባ ኣመት ቆይታው ምንም ኣልተማረም። ከጥፋት ወደ ጥፋት ሲያዘግም ነው የምናየው። መሪዎቹ የዛሬ ሃያ ኣመት ካሳዩት ትህትና ያሁኑ ያንሳል፣ የዛሬ ሃያ ኣመት ካሳዩት የፕሬስ ነጻነት የዛሬው ያንሳል። ወያኔ ኣንዱ እንዳይማር ያደረገው ነገር ከመነሻው ትግሉ የኢኮኖሚ እድልን መጠቀም በመሆኑ እንዲሁ ሃብቱን እንደነከሰ መኖርን ስለሚመርጥ ነው።የህወሃት ተፈጥሮ እንደዚህ ነው። ይህ ስርዓት ካልተለወጠ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ኣጠቃላይ የኣካባቢውን ኣገራት ጂኦ ፖለቲክስ በመቀየር በኣፍሪካ ቀንድ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል መገመት ኣያዳግትም። የዘር ፖለቲካውና የመሬት ነጠቃው የኣካባቢውን ጂዖ ፖለቲክስ ወደ ኣልተፈለገ ኣቅጣጫ ሊወስዱ የሚችሉ እምቅ ችግሮች ናቸው። የመሬት ነጠቃ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚና የኦፖርቹኒቲ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ እንድምታውና ተጽእኖው በሚገባ መታወቅ ኣለበት። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በኣፍሪካ ቀንድ ካላት ግዝፈት የተነሳ ኣለመረጋጋት ቢፈጠር በጅቡቲ፣በሶማሊያና በኤርትራ ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ እጅግ ጉልህ ነው።  የኣፍሪካ ቀንድ ሰላም ሲታሰብ ከኢትዮጵያ ሰላምነት ውጭ ማሰብ ኣይቻልም። ወያኔ ትልቅ ውስጣዊ ችግር በውስጡ ደብቆ ይዞ በኣካባቢው ኣገራት ዘንድና በኣለም ኣቀፍ ተቋማት ዘንድ ሰላም እንደሆነ፣ ሃላፊነት ሊሸከም እንደሚችል ለማሳየት ይሞክራል። ይህ ግን እውነት ሳይሆን በርግጥ ኢትዮጵያ በኣሁኑ ሰዓት ማህበራዊ ሃብቱዋ ያለ ልክ ተጎድቶ በከፍተኛ ውጥረት ላይ ያለች ኣገር ናት። ለኣፍሪካ ቀንድ ዋና ስጋት የሆነው የኣክራሪነት ችግር በህወሃት ኣይፈታም ብቻ ሳይሆን ራሱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድባብ ኣክራሪነት የሚታይበት በመሆኑ እምቅ ኣሸባሪነት በህወሃት ኣገዛዝ ውስጥ ተቀብሮ ይኖራል።ህወሃት በተፈጥሮው የኣሸባሪነት ጠላትም ሊሆን የሚያስችል ነገር የለውም። ኣክራሪነት የሚገለጸው ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን ከማንነት ፖለቲካ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ኢትዮጵያ በኣህኑ ሰዓት ይህን ችግር በውስጡዋ ይዛ ያለች ኣገር ናት። በየትኛውም ጊዜ ሊፈነዳ የሚችል የጎሳ ኣመጽን እያፈራች ያለች ኣገር ናት። ከፍ ሲል እንዳልነው የህወሃትን ተፈጥሮ ተከትሎ የመጣው  የኦፖርቹኒስቲክ ጸባይ ብዙዎችን ኣብሽቆ ይታያል። እኛ ኢትዮጵያዊያን የወያኔን ተፈጥሮ ተረድተን የጋራ የሆነችውን ኣገራችንን በጋራ እንደገና ለማነጽ ሳንከፋፈል በጋራ ታግለን ይህን ስርዓት መለወጥ ይኖርብናል። በኣንድም በሌላም መንገድ ለወያኔ የጎሳ ፖለቲካ ሰለባ ሳንሆን ኣንድነትን ኣጥብቀን ልንይዝ በፍቅር ላይ የተመሰረተ የለውጥ እንቅስቃሴ ልናደርግ ይገባናል።   እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ geletawzeleke@gmail.com

No comments: