Friday, February 6, 2015

አቶ ሲሳይ ዘርፉ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላለፈበት



ህዳር 27 እና 28/2007 ዓ.ም በ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ተዘጋጅቶ ለነበረው የአዳር ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ የቅስቀሳ በራሪ ወረቅት ሲበትን ለእስር የተዳረገው የሰማያዊ ፓርቲ አባል አቶ ሲሳይ ዘርፉ ዛሬ ጥር 28/2007 ዓ.ም የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላፈበት፡፡
ታህሳስ 14/2007 ዓ.ም በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መናገሻ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት ቆርቦ የነበረው አቶ ሲሳይ ዘርፉ ‹‹…‹ነጻነት ለፍትሓዊ ምርጫ› ለመላው ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ሁሉ….ተብሎ የተጻፈበት በራሪ ወረቀቶች ለህብረተሰቡ ሲያከፋፍል እጅ ከፈንጅ በመያዙ በፈጸመው የሐሰት ወሬን በማውራት ህዝቡን ማነሳሳት ወንጀል…›› በሚል በፌደራል አቃቤ ህግ ለቀረበበት ክስ ያቀረበው የክስ መቃወሚያ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል፡፡
ከዚህም ባሻገር አቶ ሲሳይ ዘርፉ ጥር 7/2007 ዓ.ም የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበርና ም/ሊቀመንበር የሆኑትን ኢ/ር ይልቃል ጌትነትና አቶ ስለሺ ፈይሳ እንዲሁም የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ኦህዴህ) ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለን በመከላከያ ምስክርነት አቅርቦ የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ‹‹ምስክሮቹ ከወንጀል ድርጊቱ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ምስክርነት ሳይሆን የራሳቸውን የፖለቲካ አመለካከት ሚዛናዊነት በጎደለው መልኩ ነው ያቀረቡት፡፡›› በሚል ምስክሮቹ የሰጡትን የምስክርነት ቃል ውድቅ አድርጓል፡፡
አቃቤ ህግም በተሰጠው የጥፋት ውሳኔ ላይ ‹‹ተከሰሽ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ 82(ሀ) 1/ መሰረት ማቅለያው ታይቶለት ከዚህ ቀደም የወንጀል ድርጊት ያልፈጸመ ስለሆነ የምንጠይቀው የቅጣት ማክበጃ የለንም፡፡ ሆኖም ግን በሰራው የወንጀል ድርጊት የመጨረሻው ጣሪያ ውሳኔ እንዲሰጥልን እንጠይቃለን፡፡›› ብሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ ለካቲት 3/2007 ዓ.ም የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት በመናገሻ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል፡፡
አቶ ሲሳይ ዘርፉ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለበት ዕለት ጀምሮ ዋስትናው ተነፍጎ ቀደም ብሎ በፖሊስ ጣቢያና አሁን ደግሞ ቂሊንጦ እስር ቤት በእስር ላይ ይገኛል፡፡

No comments: