Friday, February 13, 2015

ሰማያዊ ፓርቲ ምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ በርካታ አባላቶቹ እንዳይመዘገቡ እንቅፋት እንደፈጠሩበት ገለጸ


ሰማያዊ ፓርቲ ዛሬ የካቲት 6/2007 ዓ.ም ‹‹የምርጫው ሂደት በኢህአዴግና በምርጫ ቦርድ ከፍተኛ ችግር እየደረሰበት ነው!›› በሚል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የገዥው ፓርቲና የምርጫ ቦርድ አስፈጻሚዎች በፈጠሩት እንቅፋት እና ወከባ ፓርቲው ያቀረባቸው በርካታ ዕጩ ተወዳዳሪዎች የምዝገባ ጊዜው እንዲያልፋባቸው መደረጉንና ከተመዘገቡ በኋላ መሰረዛቸውን ተግለጾአል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ዕጩ ተመዝጋቢዎች የተወለዱበት ዞን መሆኑ እየታወቀ ምስክር አምጡ በሚል ምክንያት እንዳይመዘገቡ መደረጋቸው ተገልጾአል፡፡ በሰሜን ጎንደር ዞን ባሉት ሁሉም ወረዳዎች የምርጫ አስፈጻሚዎች ጽ/ቤቶችን ዘግተው በመጥፋታቸው ዕጩዎች ሆን ተብሎ የምዝገባ ጊዜው እንዲያልፋቸው መደረጉን፣ በሰማያዊ ስር ለመመዝገብ የፈለጉ የሌሎች ፓርቲ አባላት ‹‹መልቀቂያ አምጡ!›› እየተባሉ እንዳይመዘገቡ ምርጫ ቦርድና ገዥው ፓርቲ እንቅፋት እንደፈጠሩባቸው ተገልጾአል፡፡
በተመሳሳይ በሰሜን ሸዋ፣ በሲዳማ፣ በጋምቤላ፣ በጋሞጎፋ፣ በምስራቅና በምዕራብ ጎጃም፣ ዕጩ ተመዝጋቢዎች በገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና ታጣቂዎች ማስፈራሪያ፣ በአካባቢው ሽማግሌዎችና በእምነት ሰዎች በማውገዝ ከዕጩነት እንዲገለሉ ግፊት ተደርጎባቸዋል ሲል ፓርቲው ገልጾአል፡፡ በተጨማሪም በደቡብ ክልል የገዠው ፓርቲ ታጣቂ ኃይል ዕጩዎችን በማሰርና መመዝገቢያ ደብዳቤዎችን መነጠቃቸውን፤ በሰሜን ጎንደር፣ በሲዳማና ከምባታ ዞኖች የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች በታጣቂዎች ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸው መግለጫው አትቷል፡፡
ከዚህም ባሻገር በደቡብ ኦሞ ዞን ሁሉንም መመዘኛ አሟልተው የተመዘገቡ 24 የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች በምርጫ ቦርድ ደብዳቤ እንዲሰረዙ ተደርጓል ተብሏል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ም/ሊቀመንበርና የምርጫ ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት አቶ ስለሽ ፈይሳ ችግር ቢፈጠር እንኳ ችግሩን የሚፈታው ወይንም መመዘኛውን አላሟሉም ሊል የሚችለው የየአካባቢዎቹ የምርጫ ጣቢያ ሆኖ እያለ ምርጫ ቦርድ ደቡብ ኦሞ የተመዘገቡትን ዕጩዎች እንዲሰረዙ በደብዳቤ ማዘዙ የፖለቲካ ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡

No comments: