Friday, February 6, 2015

የቀድሞው የአንድነት አመራሮችና አባላት በስፋት ሰማያዊ ፓርቲን እየተቀላቀሉ ነው


ምርጫ ቦርድ በአንድነት ፓርቲ ላይ ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ የቀድሞ የአንድነት አባላት በስፋት ሰማያዊ ፓርቲን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ፡፡ ዛሬ ጥር28/2007 ዓ.ም በአምስት የምርጫ ወረዳ የተደራጁት የቀድሞው አንድነት ፓርቲ የቦረና ዞን መዋቅር ሙሉ በሙሉ ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀላቸውን የአንድነት መስራች፣ የምክር ቤት አባልና የዞኑ የፓርቲው አደራጅ የነበሩት አቶ ጌታቸው በቀለ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የቡርጅና የሰሜን ቀጠና አስተባባሪዎቻቸውን ጨምሮ መዋቅራቸው ሰማያዊ ፓርቲን ተቀላቅሏል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ጥር 26/2007 ዓ.ም የቀድሞው የአንድነት አመራሮች ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር መቀላቀላቸውን በመግለጫ ካሳወቁ በኋላ በአዲስ አበባና በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ የቀድሞው የአንድነት አመራሮችና አባላት ሰማያዊ ጽ/ቤት ድረስ እየመጡ የአባልነት ቅጽ እየሞሉ ይገኛሉ፡፡ በዛሬው ዕለትም በርከት ያሉ የቀድሞ የአንድነት አመራሮችና አባላት ሰማያዊ ፓርቲ ዋና ጸ/ቤት ድረስ በመምጣት የአባልነት ቅጽ ሞልተዋል፡፡
ሰማያዊን የተቀላቀሉት አመራሮችና አባላት ገዥው ፓርቲና ምርጫ ቦርድ ፓርቲያቸውን አሳልፎ በመስጠቱ የተፈጠረባቸው ቁጭት ይበልጥ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክረው እንዲቀጥሉ እንደሚገፋፋቸው ገልጸዋል፡፡ ሙሉ መዋቅራቸውን ይዘው ወደ ሰማያዊ ፓርቲ የተቀላቀሉት የቦረናው አደራጅ አቶ ጌታቸው በቀለ ገዥው ፓርቲና ምርጫ ቦርድ በፈጸሙት በደል ተስፋ ሳይቆርጡ እንደሚታገሉና ህዝቡም ተስፋ ሳይቆርጥ የቻለውን ሁሉ በማድረግ ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

No comments: