ጌታቸው ሺፈራው
(የግል አስተያየት)
አቶ መለስ እንደ አንድ ‹‹ኢትዮጵያዊ መሪ›› የሚገባቸው ክብር ካለ ቢሰጣቸው ክፋት አልነበረውም፡፡ ሆኖም እየተደረገ የሚገኘው ከሚገባቸው በላይ ማግነን ነው፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ አቶ መለስ የሞቱበትን ጊዜ ያመነበትን ሶስተኛ አመትን አስመክክቶም ይህ ለአቶ መለስ የማይገባ ክብር ገዥው ፓርቲ በያዛቸው ሚዲያዎች በኩል ቀጥሏል፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ አቶ መለስን ለህዝብ ‹‹የተፈጠሩ፣ ለህዝብ የኖሩና ለህዝብ የተሰዉ›› ሲል ከአምላክ የተላኩ ያህል እያስመሰላቸው ነው፡፡ ከዚህ አለፍ ሲል ደግሞ ‹‹የተላኩ›› ከማስመሰል አልፈው የፈጣሪነት ሚና ሰጥተዋቸዋል፡፡ አቶ መለስ ለሁሉም እቅዶች፣ ፖሊሲዎች፣ መፍትሄዎች አመንጭ፣ የሁሉም መጽሐፍት ጸሃፊና ሁሉንም ተቋማት የመሩ ተደርገው እየተወራላቸው ነው፡፡ አቶ መለስ ምን ያህል ጊዜ ቢኖራቸው ነው ይህን ሁሉ መጽሐፍ የጻፉት? ተቋማት፣ ባለሙያዎች፣ አማካሪዎቻቸውና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ምን እየሰሩ ነበር? ይህን ያህል ተዓምር ሰሩ በሚል ሳይሆን ታማኞቻቸውን በመጠቀም ተቋማትንና አጠቃላይ አገሪቱን በራሳቸው አስተሳሰብ እንደሚያጠምቁ በመግለጽ ተቃዋሚዎች መለስ አገሪቱን በብቸኝነት እያስተዳደሩ መሆናቸውን ሲወተውቱ በተቃራኒው ኢህአዴግ ‹‹ፓርቲው የሚከተለው የጋርዮሽ አመራር ነው!›› ሲል የነበረውን ከመቼው ረስቶት ይሆን? ነው ይህ ኢህአዴግ የፈጣሪነት ሚና የሰጣቸው አቶ መለስ እነዚህ ተግባራት በመለኮታዊ ኃይል አከናውነዋቸው ይሆን?
በ1993 ዓ/ም ህወሓት ውስጥ የተፈጠረውን ክፍፍል ተከትሎ አቶ መለስ በበላይነት የመሯቸው የተለያዩ ስብሰባዎች ተካሂደዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ ስለ ቦናፓርቲዝም መበስበስ የተወራበት ስብሰባ ነው፡፡ በዚህ ስብሰባ አቶ መለስ ስለጉዳዩ የሚያትት አንድ መጽሐፍን በማንበብ ለውይይት ሶስት ጽሁፎችን አቅርበዋል፡፡ በተለይ ሁለቱ የመጀመሪያ ጽሁፎች ከተሰብሳቢዎች በርካታ ጥያቄዎች ተነስቶባቸዋል፡፡ አድበስብሰው ሊያልፉ ቢሞክሩም ታጋይነታቸውን እንደዛሬው ጣል እርግፍ አድርገው በፍጹም ታማኝነት ያልቀየሩት የያኔዎቹ ፖለቲከኞች የዋዛ አልነበሩምና መለስን እስከመጨረሻው ሞግተዋቸዋል፡፡ በመሆኑም ሶስተኛና ማጠቃለያ ጽሁፋቸውን ሲያቀርቡ ስህተታቻቸውን ለአፋጠጧቸው ታጋዮች በግልጽ ከመናገር ውጭ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡
‹‹ባለፉት ሁለት ጥናቶች EIGHTEENTH BRUMAIRE የሚባለውን መጽሐፍ ገረፍ ገረፍ አድርጌው የነበረ ቢሆንም ባመዛኙ ቀደም ሲል ካነበብኳቸው ተነስቼ ነበር የጻፍኩት፡፡ ….ቀደም ብዬ የጠቀስኩትን ጽሁፍ እንደማንኛውም ሰው በተደጋጋሚ ያነበብኩት ቢሆንም በትክክል አልተረዳሁትም ነበር፡፡ ቦናፓርቲዝምን፣ ቢዝማርኪዝምንና አብሶሊውቲዝም (ፍጹም ዘውዳዊ አገዛዝን) አንጻራዊ ነጻነት እንዳላቸው ሶስት የተለያዩ አይነት መንግስታት ነበር የወሰድኳቸው፡፡ አሁን ግን እንዳልሆኑ ተረድቻለሁ፡፡›› ብለው ሂሳቸውን ውጠዋል አቶ መለስ፡፡
እንግዲህ አቶ መለስ ፓርቲው አደጋ በተደቀነበት ወቅትና ከፖለቲከኞች ከባድ ፈተና ሲገጥማቸው በነበረው ጊዜ በአንድ ወቅት ገረፍ ገረፍ አድርገው ያነበቡትን አንድ መጽሐፍ ወደ ኢትዮጵያ በመገልበጥ ለማሳመን መሞከራቸውን ራሳቸው በአንደበታቸው ገልጸውታል፡፡ ይህ ከምንም በላይ ትኩረት እንደሚሰጡት የሚታወቀው የራሳቸው ስልጣን ጉዳይ እንጂ የፓርቲ ስልጣን አሊያም በተደጋጋሚ ቸልተኝነታቸውን ያስመሰከሩበት አገራዊ ጉዳይ አልነበረም፡፡ ከምንም በላይ ስልጣናቸውን ለሚወዱት አቶ መለስ ተቀናቃኞቻቸውን ለመርታት በጊዜው ሞጋች ታጋዮች ፊት ሊያቀርቡት ይችል የነበረው ጽሁፍ ከዚህ የተሻለ መሆን ነበረበት፡፡ በእርግጥ አቶ መለስ ያቅርቡት እንጂ ለጸሁፉ በቅርበት ይገኙ የነበሩ ጓዶቻቸውና አማካሪዎቻቸውም ሚና ሊኖር እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ ያም ሆኖ አቶ መለስ ኢትዮጵያንም ሆነ ፓርቲያቸውን ይመሩ የነበሩት ገረፍ ገረፍ አድርገው ያነበቡትን መጽሃፍት በመገልበጥ መሆኑን ከራሳቸው አንደበት መረዳት ይቻላል፡፡ ተቃውሞ ሲገጥማቸው ደግሞ ይኸውን መጽሐፍ እንደገና አንብበውም ሆነ አስነብበው ከማቅረብ ውጭ የራሳቸው የሚባል አዲስ አመለካከትም ያበረከቱበት ጊዜ አልነበረም፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ሲያስተዳድሩ የኖሩት ገረፍ ገረፍ በተደረጉ ጥናቶች ተደጋጋሚ ሙከራ (trial and error) ስልት ነበር ማለት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከማርክሲዝም፣ ሌኒኒዝም፣ ስታሊኒዝም፣ ማኦይዝም፣ ኒዮሊብራሊዘም፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ…..የመሳሰሉት አስተሳሰቦች እንደወረዱም ሆነ ተዳቅለው የተወሰዱ ፖሊሲዎች ኢትዮጵያን ቤተ ሙከራ አድርገዋታል፡፡
ከ1993 በፊት በህወሓት ውስጥ ችግር ሳይከሰት በተለይም በትግል ስልቱ ወቅትም መለስ፣ ህወሓትና ኢህአዴግ ይጠቀሙት የነበረው ተመሳሳይ ስልትን ነው፡፡ የሌኒን የፖለቲካ ስልቶችን በመገልበጥ ‹‹የትግራይ ማርክሲስት ሊኒኒስት ሊግ›› የመሳሰሉትን ጨምሮ ስሞች፣ይወጡ የነበሩ ፖሊሲዎችና ስልቶች በሩሲያና በኢትዮጵያ ምንም ልዩነት ሳይደረግባቸው በቀጥታ የሚተገበሩ ነበሩ፡፡ ምንም እንኳ አቶ መለስን እንደ ወታደራዊ መሃንዲስ ተደርገው የሚቀርቡበት ሁኔታ ከሚገባው በላይ የተጋነነ ቢሆንም አቶ መለስም ሆነ ህወሓት አዲስ ሳይሆን የማኦንን ወታደራዊ ስልት ገልብጠው እንደተጠቀሙበት ይታወቃል፡፡ ሞስኮ፣ ቤጂንግ ወይንም ምስራቅ ጀርመን የታተመ አንድ ግራዘመም መጽሄት ውስጥ የተቀመጠን ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስልት ሳይቀር ህወሓት/ኢህአዴግ እየገለበጠ ኢትዮጵያ ላይ ሲተገብር እንደነበር የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡
ከ1993 በኋላ ያለው ደግሞ ከዚህም የባሰ ሆነ፡፡ አቶ መለስ ገረፍ ገረፍ አድርገው ጽሁፍ ሲያቀርቡባቸው በነበሩት ስብሰባዎች ተቀናቃኞቻቸውን አሸንፈው ብቸኛው የስልጣን ባለቤት መሆን ችለዋል፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ ታጋዮች አቶ መለስን በጥያቄ ሲያጣድፉት የነበሩትና ‹‹የተራገፉት›› ጓዶቻቸው እጣ ፈንታ እንዳይገጥማቸው አቶ መለስ መጽሐፍ ጠቀሱ አልጠቀሱ ያሉትን በሙሉ ተቀብለው የሚያስተገብሩ ታማኞች ለመሆን ተገደዋል፡፡ በመሆኑም ከዚህ በኋላ አቶ መለስ ገረፍ ገረፍ አድርገውም ሆነ ‹‹አስታውሸዋለሁ!›› ብለው ያቀረቡት ጽሁፍ ሁሉ በጥልቅ ምርምራዊ ጥናትነት መቅረብ የጀመረበት ወቅት ነው፡፡
በእርግጥ ኢህአዴግ አሁን እያለ ከሚገኘው በተቃራኒ አቶ መለስ ስብሰባ ላይ የሚያቀርቡት ‹‹ጥናታዊ ጽሁፍ›› ሁሉ የእርሳቸው ስራ አልነበረም፡፡ በተለይ ከ1993 በኋላ ለፓርቲውም ሆነ ለአገሪቱ የቀረቡት ስልትና ስትራቴጅዎች እንዲሁም ፖሊሲዎች በተቋማት የተሰሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ጥናቶች የፓርቲና አገራዊ ጉዳዮች ስም እንጂ በክፍፍሉ ወቅት ስልጣንን ለማዳን እንደተደረገው በሚስጥራዊነት ሳይሆን ተቋማት፣ አማካሪዎችና ሌሎችም ግለሰቦች ሊሰሯቸው የሚችሉ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል ከ1993 ዓ.ም ክፍፍል አንድ አመት በኋላ የወጡት የውጭ ጉዳይ፣ የአቅም ግንባታ፣ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ፖሊሲና ስትራቴጂ የሚያብራሩትን ጥራዞች በማስታወቂያ ሚኒስተር የፕሬስና ኦዶቪዥዋል መምሪያ የተዘጋጁ መሆናቸውን በመጽሐፍቱ መግቢያ ላይ ተቀምጧል፡፡ አቶ መለስ በወቅቱ በማስታወቂያ ሚኒስተር የፕሬስና ኦዶቪዥዋል መምሪያ ውስጥ ተመራማሪ ሆነው ሰርተውም ይሁን የኢትዮጵያ ህዝብ እነዚህን ጉዳዮች አያነባቸውም ተብሎ እነዚህ መጽሐፍቶች ለአቶ መለስ ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡
አንድ የግብርና ፖሊሲና ስትራቴጅን የሚተነትን ጥራዝ ለማዘጋጀት ከአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ጋር የሚውሉት የግብርና ሰራተኞች የሚሰበስቡት መረጃ በየአካባቢው በሚገኘው መስሪያ ቤታቸው ጥናት ይደረግበታል፡፡ በመሆኑም በወረዳ፣ ዞንና ክልል ባሉት ተቋማት በየደረጃው ጥናቱ ተሰርቶና ውይይት ተደርጎበት ለግብርና ሚኒስቴር እና ሌሎች አጋር አካላት ጨምሮ መሪው ቢሮ (ጠቅላይ ሚኒስተር ቢሮ) ድረስ ያሉ አካላት ለፖሊሲው ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ ለመሆኑ አቶ መለስ የግብርና ፖሊሲን የሚጽፉት የግብርና ሚኒስትር ሰራተኞች፣ አመራሮቻቸው፣ አማካሪዎቻቸው፣ የአቶ መለስ የግብርና አማካሪና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ የት ሄደው ነው?
በውጭ ጉዳይ ላይም ያለው እውነት ተመሳሳይ ነው፡፡ በአንድ አገር ኤምባሲ የሚላኩ የየመስኩ አታሼዎች የራሳቸውን ጥናት ሰርተው ኤምባሲው በየወቅቱ ጥናት ይሰራል፡፡ በየአገራቱ የሚገኙ ኤምባሲዎች፣ ስለአገራቱ እውቀት ያላቸው ምሁራን፣ ተቋማት ያደረጉት ጥልቅና ዝርዝር ጥናት አጠር ባለ መልኩ አንዲት አገር አጠቃላይ የውጭ ፖሊሲ እስትራቴጅን የሚመራበት ጭምቅ ፖሊሲ ይወጣዋል፡፡ አቶ መለስ የዓለምን አገራት ተጽዕኖ፣ መልካም ተሞክሮ፣ ለኢትዮጵያ የሚኖራቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና የደህንነት ጥቅምና ጉዳት በዝርዝር ተረድተው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን የመጻፍ ጊዜውም ሙያዊ ብቃቱም አልነበራቸውም፡፡ በአንጻሩ ከ50 በላይ በውጭ አገር የሚገኙ ኤምባሲዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር መስሪያ ቤት፣ የጠቅላይ ሚኒስተሩ አማካሪዎችና ቢሮ ከአቶ መለስ በተሻለ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጥራዙ ላይ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል፡፡
ከዚህም አለፍ ሲል ኢህአዴግ በተለያዩ መስኮች እውቀት አላቸው ብሎ ያመነባቸውን የውጭ አማካሪዎች ሁሉ በከፍተኛ ደሞዝ ምኒልክ ቤተ-መንግስት ድረስ አስመጥቶ ሀሳብ እንዲያካፍሉት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም አቶ መለስ በበላይነት የመምራት እንጂ በየመስኩ ጥናት ለማድረግም ጊዜም ሆነ እውቀት አልነበራቸውም፡፡ እንደ እነ ሌኒን ያሉት መሪዎች አዲስ ሀሳብ ያመነጩ (ቢያንስ ማርክሲዝምን አሻሽሎታልና) የአገሪቱ ፖሊሲዎች በራሳቸው ርዕዮት መነጸር እንዲዘጋጁ ከማድረግና ከመቆጣጠር ውጭ ዝርዝር ፖሊሲዎችን የሚሰሩ አልነበሩም፡፡ ሌኒን ስለ ኢትዮጵያና ሶቬት ህብረት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ማህበራዊ ግንኙነት የሚሰራበት ጊዜም ዝርዝር እውቀት (መረጃ) አልነበረውም፡፡ አቶ መለስን በመለኮታዊ መነጸር ለማሳየት የፈለገው ህወሓት/ኢህአዴግ ግን የኢትዮጵያ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞችን፣ አማካሪዎች፣ የጠቅላይ ሚኒስተሩ ቢሮ፣ ሌሎች የኢህአዴግ ፖለቲከኞች፣ የአገር ውስጥና የውጭ ምሁራን የነበራቸውን ሚና ያለ ሀፍረት ለአቶ መለስ ብቻ አስረክቧል፡፡
ሌላው ይቅርና አቶ መለስ ለመመረቂያ ጻፉት የሚባለውን ጽሁፍ ጭምርም የአማካሪዎቻቸውና የሌሎች ተሳትፎ እንደሚኖርበት አያጠራጥርም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚቀርብን ጽሁፍ አቶ መለስ ገረፍ ገረፍ አድርገው አንብበው ከማቅረብ ይልቅ አማካሪዎቻቸውንም ተጠቅመው ጥልቅ ጽሁፍ ለማድረግ ስለሚጥሩ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ የራሳቸው ነው ቢባል እንኳ አቶ መለስን ልዩ አያደርጋቸውም፡፡ ከአቶ መለስ በተጨማሪ በርካታ አምባገነኖች መጽሐፎችን ‹‹ጽፈዋል››፡፡ ለምሳሌ ያህል ሞሶቬኒ እና ጋዳፌ መጽሐፍ ከጻፉት የአፍሪካ አምባገነኖች መካከል በቀዳሚነት የሚወሱት ናቸው፡፡ የሞሶቬኒ መጽሃፍ ከአቶ መለስ በርዕዮት፣ ፓርቲውን በማጋነንና በመሳሰሉት የሚመሳሰል ነው፡፡ የሞሶቬኒ መጽሐፍትና የአቶ መለስ መመረቂያ የሌሎች ጽሃፍትን ሀሳብ በማጣቀሻነት በመውሰድ የተሰሩ እንጂ አዲስ የፍልስፍና ውጤቶች አይደሉም፡፡
በተቃራኒው ‹‹አረንጓዴው መጽሐፍ›› የሚባለው እና ሶስት ጥራዝ ያሉትን መጽሃፍ የጻፈው ጋዳፌ ሀሳብ አዲስ ፍልስፍናዎች ያካተተ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የአቶ መለስና ሞሴቬኒ ‹‹የምስራቁን ዓለም›› ተሞክሮ በማድነቅና የምዕራባዊያን ስርዓት በመውቀስ ላይ የሚያተኩሩ ሲሆን መንግስት ከፓርላሜንታዊ ዴሞክራሲ የተለየ በአገር ሽማግሌዎችና በሌሎች በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ባላቸው አካላት ሊመሰረት ይገባዋል ያለውን ባህላዊ ስርዓት የሚያስቀምጠው የጋዳፌ መጽሃፍ በአንጻራዊነት አዲስ ሀሳብን የያዘ ነው፡፡ የአቶ መለስ አስተሳሰብና ጻፉት የሚባለው የጋዳፌን ያህል አዲስ ሀሳብ ሳያነሳ ከእነ ሌኒን፣ ማርክስና ሌሎች የራሳቸውን ርዕዮት ያፈለቁ ሰዎች በላይ እየጋነነ ይገኛል፡፡
የፖሊሲ ጥራዞችና መጽሐፍት ይቅርና የአቶ መለስ ንግግሮች ላይ የሌሎች አካላት ሚና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በዓለም ደረጃ የመሪዎችን ንግግር የሚጽፉ ሰዎች (speech writers) ለአብዛኛው የአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እውቀት ያካበቱ ናቸው፡፡ የመሪዎቹን ቃላት የሚፈጥሩ፣ የሚገሩ፣ የሚያሳምሩ ወይንም የሚያስተካክሉ በመሆናቸውም ‹‹word smiths›› ይሏቸዋል፡፡ ባራክ ኦባማ ከምርጫ ዘመቻው ጀምሮ አብዛኛዎቹን ጥቁሮች ያስለቀሰበት፣ ሌሎችን የአሜሪካና የዓለም ህዝቦች አፍ ያስከፈተበት ንግግር ጆን ፋቭሬአው የተባለ ወጣት የንግግር ጸሃፊ ድርሰቶች ናቸው፡፡ ጸሃፊዎች አንድ መሪ ፖሊሲውን፣ አቋሙን ለህዝብ በሚገባ መልኩ፣ ድምጸት፣ ምክንያትና ቋንቋ እንዲገልጽ ያድርጉታል፡፡ በአጭሩ እነዚህ ጸሃፊዎች የአዕምሮ ንብረት የሌላቸው ደራሲዎች ናቸው፡፡ የመሪዎች ወርቃማ አባባሎች እየተባሉ የሚነገሩት ሁሉም የንግግር ጸሃፊዎች አባባሎች ናቸው፡፡ የአንዲት አገር መሪ ብቻ ሳይሆን በየደረጃው የሚገኙ የተቋማት መሪዎችም የንግግር ጸሃፊዎች (speech writers) አላቸው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥም የሚደረገው ተመሳሳይ ነውና ለአቶ መለስ ንግግሮች ስሙ ያልተጠቀሰልን ደራሲ መኖሩ የግድ ነው፡፡ አቶ መለስ አገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያደርጉት እያንዳንዱ ንግግር በስተጀርባ የንግግር ጸሃፊዎች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ አቶ መለስ የሚነቀፉባቸውን ለጊዜው ትተን ኢህአዴግ አሁን እንዲወደሱ የሚጥርባቸው የአፍሪካ ህብረት ላይ ያደረጉት ቀስቃሽ ንግግር እና ሌሎችም ንግግሮች የራሳቸው አይደሉም፡፡ የንግግር ጸሃፊዎች የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት የላቸውምና የአቶ መለስ ወርቃማ ንግግሮች ተብለው በኢቲቪና ኢህአዴግ የሚቀርቡትን የእነዚህ ሰዎች ድርሰቶች መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ሆኖም አቶ መለስ እነዚህን ድርሰቶች በመተወን የተዋጣላቸው መሆናቸው የማይካድ ነው፡፡
ኢህአዴግ እንደሚያጋንነው ግን አቶ መለስ አዲስ የሌኒን፣ ስታሊንን፣ ማኦን፣ ማርክስንና ሌሎችን አስተሳሰቦች በተቋማት፣ ታማኞቻቸው፣ አማካሪዎችና ሌሎችንም ተጠቅመው ለስልጣን በሚጠቅማቸው መልኩ ከማዳቀልና ከማስመሰል ውጭ አዲስ አስተሳሰብ አላሳዩንም፡፡ ልማታዊ መንግስትን በስም ደረጃ ከምስራቅ ኤሲያ፣ የመገንጠል መብትን ከስታሊኗ ሶቬት፣ የሲቪክ ማህበረሰቦች አዋጅን ከሩሲያ፣ ግብጽና ዚምባብዌ፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ከአልባኒያና ቻይና፣ ጠባብ ብሄርተኝነትን ከሶማሊያና ይጎዝላቪያ ‹‹በመልካም ተሞክሮነት›› ከመገልበጥ ውጭ የማሻሻልም ሆነ አዲስ ነገር ሲፈጠር አላየንም፡፡ ይባስ ብሎም ሌኒኒዝም፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ልማታዊ መንግስትና የመሳሰሉት በስም ደረጃ አሊያም አሉታዊ ጎናቸው እንጂ አወንታዊ ጎናቸው ሲተገበሩ የማይታዩ ገረፍ ገረፍ ተደርገው ለአቶ መለስና ለህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣን ብቻ በሚጠቅም መልኩ የተቃኙ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
ኢህአዴግ እንደሚያጋንነው ግን አቶ መለስ አዲስ የሌኒን፣ ስታሊንን፣ ማኦን፣ ማርክስንና ሌሎችን አስተሳሰቦች በተቋማት፣ ታማኞቻቸው፣ አማካሪዎችና ሌሎችንም ተጠቅመው ለስልጣን በሚጠቅማቸው መልኩ ከማዳቀልና ከማስመሰል ውጭ አዲስ አስተሳሰብ አላሳዩንም፡፡ ልማታዊ መንግስትን በስም ደረጃ ከምስራቅ ኤሲያ፣ የመገንጠል መብትን ከስታሊኗ ሶቬት፣ የሲቪክ ማህበረሰቦች አዋጅን ከሩሲያ፣ ግብጽና ዚምባብዌ፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ከአልባኒያና ቻይና፣ ጠባብ ብሄርተኝነትን ከሶማሊያና ይጎዝላቪያ ‹‹በመልካም ተሞክሮነት›› ከመገልበጥ ውጭ የማሻሻልም ሆነ አዲስ ነገር ሲፈጠር አላየንም፡፡ ይባስ ብሎም ሌኒኒዝም፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ልማታዊ መንግስትና የመሳሰሉት በስም ደረጃ አሊያም አሉታዊ ጎናቸው እንጂ አወንታዊ ጎናቸው ሲተገበሩ የማይታዩ ገረፍ ገረፍ ተደርገው ለአቶ መለስና ለህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣን ብቻ በሚጠቅም መልኩ የተቃኙ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
Source:
ነገረ ኢትዮጵያ / Negere Ethiopia
No comments:
Post a Comment