ሰማያዊ ፓርቲ ነሃሴ 16 እና 17/2007 ዓ.ም አንደኛ መደበኛ ጉባኤውን በማንራሸዋ ሆቴል እንደሚያደርግ የፓርቲው የምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰኢድ ኢብራሂም ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ የሆቴል ቅድሚያ ክፍያ ከፍሎ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና የስብሰባ ማሳወቂያ የእውቅና ደብዳቤ ማግኘቱንም ገልጸዋል፡፡ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ በሁለት ቀን ውሎው የኦዲትና ኢንስፔክሽን፣ የብሄራዊ ምክር ቤቱን የሶስት አመት ሪፖርት በማዳመጥ፣ የሊቀመንበር፣ የብሄራዊ ምክር ቤት 37 ሙሉ አባላትና 13 ተለዋጭ፣ 5 የኦዲትና ኢንስፔክሽን አባላትን እንደሚመርጥ ሰብሳቢው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው ባለፉት እቅዶች ላይ ተወያይቶና ገምግሞ ለወደፊትም የሚመራባቸው ጉዳዮች ላይም ይወስናል ብለዋል፡፡
እስካሁን ለዕጩነት ራሳቸውን ያቀረቡት ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ብቻ መሆናቸውንና ምክር ቤቱ ተጨማሪ ዕጩዎችን አቅርቦ ለጠቅላላ ጉባኤው እንደሚያፀድቅም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው ምክር ቤቱ የሚያቀርባቸውን ዕጩዎች ብቁ አይደሉም ብሎ የመጣልም ሆነ ሌሎች ዕጩዎች እንዲቀርቡ የማድረግ መብት እንዳለውም አቶ ሰይድ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ታህሳስ 22/2004 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን ባለፉት ሶስት አመታት ሀገር ቤት ሲንቀሳቀሱ ከቆዩትና አሁንም ከሚንቀሳቀሱት ፓርቲዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment