አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ያደረገው ሰማያዊ ፓርቲ ኢ/ር ይልቃል ጌትነትን በድጋሜ የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡
ትናንት ነሀሴ 16/2007 ዓ.ም ጉባኤውን የጀመረው ፓርቲው በዛሬው ሁለተኛና የማጠቃለያ ውሎው የፓርቲውን ሊቀመንበር፣ የብሄራዊ ምክር ቤት አባላት እንዲሁም የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን አባላት ምርጫን አድርጓል፡፡
ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በድጋሜ ለቀጣዩ ሦስት አመታት ፓርቲውን እንዲመሩ የተመረጡ ሲሆን፣ አምስት የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን አባላትም በጉባኤው ተመርጠዋል፡፡ ጉባኤው የፓርቲውን የብሄራዊ ምክር ቤት አባላትንም መርጧል፡፡
ለፓርቲው ሊቀመንበርነት ቀደም ብለው ፓርቲውን ለሁለተኛ ዙር ለመምራት ራሳቸውን በእጩነት ያቀረቡት ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ብቻ ሲሆኑ፣ ጉባኤው ተጨማሪ እጩዎችን ለመቀበል ባቀረበው ሀሳብ መሰረት ራሱን በእጩነት የሚያቀርብ ይኖራል ተብሎ ቢጠበቅም በእጩነት ራሱን ያቀረበ አልነበረም፡፡
በመሆኑም በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት ጉባኤው ተጨማሪ እጩዎችን በጥቆማ ለማወዳደር ተገድዷል፡፡ በዚህም ጉባኤው ስድስት እጩዎችን የጠቆመ ቢሆንም አምስቱ ‹‹አንወዳደርም›› በማለታቸው ከተጠቆሙት መካከል አቶ ዮናታን ተስፋዬ ብቻ ለመወዳደር ፍላጎታቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ፓርቲውን በህዝብ ግንኙነት ማገልገላቸው የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ለሊቀመንበርነት መወዳደር ችለዋል፡፡
ለሊቀመንበርነት እጩ ሆነው የቀረቡት ሁለቱ እጩዎች በጉባኤው ፊት በተመደበላቸው ጊዜ ገደብ ውስጥ ራሳቸውን ካስተዋወቁና የምረጡኝ ቅስቀሳ ካደረጉ በኋላ ወደ ድምጽ መስጠት መግባት ተችሏል፡፡ በተሰጠው ድምጽ መሰረትም ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ሰማያዊ ፓርቲን ለቀጣይ ሦስት አመታት እንዲመሩ በአብላጫ ድምጽ ተመርጠዋል፤ በዚህም ኢ/ር ይልቃል ከተሰጠው ድምጽ 136 ድምጽ አግኝተው ሲያሸንፉ፣ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በበኩላቸው 60 ድምጽ በማግኘት ፉክክር አድርገዋል፡፡
የምርጫ ውጤቱ ይፋ መሆኑን ተከትሎ ንግግር ያደረጉት ተመራጩ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ሰማያዊ ፓርቲ በሁለቱ ቀናት ጉባኤው ያነሳቸውን ችግሮች ለመፍታት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ በዛሬው ውሎው ቀጣይ የፓርቲውን እንቅስቃሴ አስመልክቶም በጉባኤው አባላት አጠቃላይ ውይይት አድርጓል፡፡ በዚህም ፓርቲው ወደፊት ማደራጀት ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚገባው ጉባኤው አጽንኦት ሰጥቶበታል፡፡
ጠቅላላ ጉባኤው የብሄራዊ ምክር ቤትና የፓርቲው ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ያቀረቡት ሪፖርት ላይ ተወያይቶ ሪፖርቶቹ የፓርቲው ሰነድ ሆነው እንዲፀድቁ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ያካሄደውን ጉባኤ ዛሬ ነሀሴ 17/2007 ዓ.ም አጠናቅቋል፡፡
No comments:
Post a Comment