Tuesday, August 4, 2015

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ድርቅ መግባቱ ታወቀ




ሐምሌ ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ዘጋቢዎቻችን እንዳሉት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከዝናብ እጥረት ጋር ተያይዞ ድርቅ ተከስቷል።በሰሜን ሸዋ፣በዋግ ህምራና በወሎ በርካታ ቦታዎች ዝናብ ባለመዝነቡ ድርቅ ገብቷል፡፡ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ጉዳዩን በዝግ ስብሰባዎች ቢወያዩበትም ፣ መረጃው ወደ አደባባይ እንዳይወጣ ጥረት እያደረጉ ነው። በዋግ ህምራ አካባቢ ለሶስተኛ ጊዜ እርሻ እየተገለበጠ በመታረስ ላይ መሆኑን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንዳመለከተው ደግሞ በግንቦት ወር በሶስተኛዉ የወሩ ሳምንት በሰ/ሸዋ ዞን 8 ወረዳዎች ማለትም በባሶናወራና፣ አንፆኪያ፣ ሲያደብር ዋዩ፣ መርሃቤቴ፣ መንዝላሎ፣ ሃገረማርያም፣ ቀወትና አንኮበር፣ በደቡብ ወሎ ዞን 16 ወረዳዎች እና በደቡብ ጎንደር ዞን 6 ወረዳዎች ስርጭቱ ያልተስተካከለ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ዝናብ ያገኙ ቢሆንም ፣ ሌሎች 64 የክልሉ ወረዳዎች ዝናብ እንዳልነበራቸው ታውቆአል፡፡
በትግራይ ደግሞ ወሩ በገባ የመጀመሪያዉ ሳምንት ቆራሮና ኢሮብ ወረዳዎች ከ1-2 ቀናት ስርጭቱ ያልተስተካከለ አነስተኛ ዝናብ እንዲሁም በተምቤን፣ እንደመሆኒ፣ አህፈሮም ወረዳዎች ለውስን ቀናት ከባድ ዝናብ የነበራቸው መሆኑን ከክልሉ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ ይሁን እንጂ ከሁለተኛዉ ሳምንት በኋላ በታህታይ ኣድያቦ ወረዳ በ10 ቀበሌዎች እንደመሆኒና ኦፍላ ወረዳዎች፣ በደቡብ ምስራቅ ዞን ሳምረ ወረዳ፣ በማእከላዊ ዞን አድዋና በማይጨው ወረዳዎች፣ በተምቤን ወረዳ፣ በሰሜን ምእራብና በምእራብ ዞኖች በቆራሮ፣ አስገደ ጽምብላ፣ ጸለምቲ፣ አዲያቦ፣ እንዲሁም በአወዛጋቢዎቹ ወልቃይትና ፀገዴ ወረዳዎች ከነበረዉ አነስተኛ ዝናብ በስተቀር በአመዛኙ በቀሪዎቹ ሳምንታት የነበረዉ ዝናብ አመርቂ አለመሆኑን መረጃው አመልክቷል።
በደቡብ ደግሞ በወሩ ዉስጥ በአብዛኛዉ የክልሉ አካባቢዎች ስርጭቱ የተስተካከለ ከዝቅተኛ እስከ መካከለኛ ዝናብ የዘነበ ሲሆን ፣ በአንዳንድ አካባቢዎችም አልፎ አልፎ ከበድ ያለ ዝናብ ጥሎአል። ይሁን እንጂ በጋሞ ጎፋ ዞን ዛላ፣ ከምባ፣ ምእራብ አባያ እና የጸሐይ ወረዳዎች፣ በስልጤ ዞን በአሎቾ ወሪሮ ወረዳ እና ሀዲያ ዞን በአመዛኙ ስርጭቱ ያልተስተካከለ ዝናብ ያገኙ እንደነበረ እና በነዚሁ ዞኖች አንዳንድ ቀበሌዎች ላይ ዝናብ እንዳልነበረ ከግብርና ሚኒስቴር መረጃ ማወቅ ተችሏል።
በአፋር በወሩ ዉስጥ በአመዛኙ ዝናብ ያልነበረ ሲሆን፣ በወሩ የመጀመሪያ ሳምንት ከግብርና ስራዎች አንፃር ጠቀሜታው በጣም አነስተኛ የሆነ ዝናብ ዘንቧል። በሱማሌ በአመዛኙ ዝናብ ያልነበረ ሲሆን በግንቦት ወር ሁለተኛ ሳምንት የጂጂጋ ወረዳ በከፊል አነስተኛ ዝናብ ሲያገኝ በወሩ ሶስተኛ ሳምንት ጂጂጋና ሽንሌ ዞኖች ስርጭቱ ከቦታ ቦታ የተለያየ መካከለኛ ዝናብ እንዳገኙ ታውቋል።
የክረምቱ ዝናብ ስርጭት አለመስተካከል ጋር ተያይዞ የምግብ እህል ተረጂዎች ቁጥር በከፍተኛ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተቀማጭነታቸው በአዲስአበባ የሆኑ ለጋሽ ሀገራት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን ስጋት ውስጥ መውደቁ ታውቆአል፡፡
እስካሁን ድረስ የተፈናቀሉ ዜጎች ይኑሩ አይኑሩ የታወቀ ነገር የለም። የዝናብ ስርጭቱ በሚቂጥሉት ሳምንታት ካልተስተካከለ፣ በአገሪቱ በሰው እና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ የሆነ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።
በትግራይ ህወሃት በቅርቡ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር በማውጣት የህወሃትን 40ኛ አመት በአል ሲያከብር ፣ ኦህዴድም ተመሳሳይ መጠን ያለው ገንዘብ አውጥቶ 25ኛ አመት በአሉን አክብሯል። ብአዴንም 35ኛ አመት በአሉን ለማክበር
ተመሳሳይ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። በሁሉም ክልሎች በድርቅና በኑሮ ውድነት ዜጎች እለታዊ ወጪያቸውን ለመሸፈን ተስኖአቸው በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ ከፍተኛ የአገር ሃብት ለክበረበአላት እየወጣ በመባከን ላይ መሆኑን ዘጋቢያችን አክሎ ገልጿል።
Source: Ethsat

No comments: