Friday, November 7, 2014

የመኢአድ አባላት በፀጥታ ሃይሎች መወሰድ

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) የቀድሞ ዋና ጸሃፊ እና አባላት በጸጥታ ሃይሎች ተወስደው ያሉበት አለመታወቁን ፓርቲው አስታወቀ።የአቶ ተስፋዬ ታሪኩ በጸጥታ ሃይሎች ሲወሰዱ በቦታው ነበርኩ የሚሉት ባለቤታቸው ቤታቸው ሲፈተሽ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለመያዛቸውን ተናግረዋል።

12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch
አቶ ተስፋዬ ታሪኩ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ዋና ጸሃፊ ሆነው አገልግለዋል። በፖለቲካ ተሳትፏቸው በ1997 ዓ.ም. ጭምር ተደጋጋሚ እስር እና እንግልት ገጥሟቸዋል የሚባሉት አቶ ተስፋዬ ጥቅምት 28/ 2007 ዓ.ም. ከደጀን ከተማ በጸጥታ ሃይሎች ሲወሰዱ አጠገባቸው እንደነበሩ ባለቤታቸው ወ/ሮ መለሰች ዋሴ ይናገራሉ።
''ቤት ነበርኩኝ። ሰባት ሰዓት ላይ ገቡ ስምንት ሰዓት ላይ ቤት እንፈትሻለን አሉ። የፍርድ ቤት ወረቀት አላችሁ ወይ ስል የፍርድ ቤት ወረቀት የላቸውም። የፍርድ ቤት ወረቀት ከሌላችሁ ግን ቤቴን መበርበር አትችሉም ሲላቸው ለመማታት ሞከሩ። ከአካባቢው ፖሊሶች በመጥራት ፍተሻ ጀመሩ።ምንም ነገር አላገኙም። አስራ ሁለት ሰዓት ተኩል ከቤት ይዘውት ወጡ። ሶስት ሰዎች አሉ እኔ የማውቃቸው ሌሎቹን ግን አላውቃቸውም።''
ወ/ሮ መለሰች ዋሴ ባለቤታቸው በጸጥታ ሃይሎች ሲወሰዱ ለምርመራ መሆኑን እና እንደሚመልሷቸው እንደተነገራቸው ተነግሮኛል ብለዋል። ሆኖም ቤታቸው ካለ ፍርድ ቤት ማዘዣ የተፈተሸበትን፤ባለቤታቸው የተፈለጉበትን እንዲሁም የተወሰዱበትን ቦታ እንዳልተነገራቸው ተናግረዋል።
ወ/ሮ መለሰች ዋሴ ባለቤታቸውንና የሁለት ልጆቻቸውን አባት አቶ ተስፋዬ ታሪኩን ፍለጋ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) ፕሬዝዳንት አቶ አበባው መሃሪ ከአቶ ተስፋዬ ታሪኩ በተጨማሪ ሶስት የፓርቲው አባላት በአማራ ክልል በጸጥታ ሃይሎች እንደተወሰዱ ይናገራሉ።
''ከደብረ ታቦር ሁለት አባሎቻችን ተይዘዋል። ከባህር ዳር መቶ አለቃ ጌታቸው ተይዟል። ደጀን አቶ ተስፋዬ ታሪኩ ተይዟል።ልናጣራ በየቦታው ዞረናል። ያሉበትን አላወቅንም። የመንግስት አካላትን ለመጠየቅ ሞክረን ነበረ ሃላፊነት የሚወስድ አካል ማግኘት አልቻልንም።
በዚህ ዘገባ የአማራ ክልል ፖሊስን ምላሽ ለማካተት ያደረግንው ጥረት አልተሳካም።የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) ከአንድነት ለነጻነትና ለፍትህ ፓርቲ አንድነት ጋር የጀመረውን ውህደት ለመፈጸም እንዲያስችለው ጠቅላላ ጉባኤውን አርብ እና ቅዳሜ በአዲስ አበባ ያካሂዳል። የውህደት ሂደቱ ስምምነት ላይ የተደረሰበት ቢሆንም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ኮሚሽን ፓርቲው የጠቅላላ ጉባኤው አልተሟላም በሚል እንዳቆየው አይዘነጋም።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሰ
Source: dw

No comments: