Wednesday, November 5, 2014

እነ ሀብታሙ አያሌው ለህዳር 2 ተቀጠሩ



በዛሬው ዕለት ጥቅምት 26 ቀን 2007 ዓ.ም ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት የአንድነት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወጣት ሃብታሙ አያሌው፣ የአንድነት ፓርቲ ም/የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ዳንኤል ሺበሺ ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ም/አፈ ጉባኤ የሺዋስ አሰፋ ፣ የአረና ፓርቲ የአመራር አባልና የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር አብርሃ ደስታ እንዲሁም የአ/አ ዩኒቨርስቲ የማስትሬት ተማሪ ዘላለም እና በተመሳሳይ መዝገብ የተከሰሱ ሌሎች 5 ግለሰቦች ጠበቆቻቸው የሚያቀርቡትን የዋስትና ጥያቄ ለመስማት ፍርድ ቤቱ ለህዳር 2 ቀን 2007ዓ.ም ከቀኑ 5 ቀጠሮ እንደሰጠ በስፍራው የተገኙት የፍኖተ ነፃነት ዘጋቢዎች አስታወቁ፡፡
ዛሬ ጠዋት ልደታ ፍርድ ቤት የቀረቡትን የእነሀብታሙ አያሌውን መዝገብ የተመለከተው ፍርድ ቤት ለህዳር 2 ቀጠሮ የሰጠው የተከሳሽጠበቆች ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ነው፡፡ የወጣት ሃብታሙ አያሌው፣ የአንድነት ፓርቲ ም/የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ዳንኤል ሺበሺ ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ም/አፈ ጉባኤ የሺዋስ አሰፋ ፣ የአረና ፓርቲ የአመራር አባልና የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር አብርሃ ደስታ እንዲሁም የአ/አ ዩኒቨርስቲ የማስትሬት ተማሪ ዘላለም ጠበቃ የሆኑት አቶ ተማም አባቡልጉ በክስ ቻርጁ ላይ የከሳሽ አቃቢህግ ስም ያለመቀሱንና የማስረጃ ዝርዝር መግለጫ ያለመኖሩን በመግለፅ “ደንበኞቼ ላይ የቀረበው ማስረጃ ስንት ገፅ እንደሆነ እንኳን አላውቅም” በማለት ለፍርድ ቤቱ አሳውቀዋል፡፡ የሌሎቹ ተከሳሾች ጠበቆችም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ አቃቤህግ በበኩሉ “ማስረጃዎቹ በየጊዜው ስለሚጨምሩ ነው ያላካተትነው፡፡ ሆኖም ሁለት ገፅ መግለጫ አለ” ፍርድ ቤቱም አቃቤ ህግ የማስረጃ ዝርዝር መግለጫውን እንዲያካትት በማዘዝ ጠበቆቻቸው የሚያቀርቡትን የዋስትና ጥያቄ ለመስማት ፍርድ ቤቱ ለህዳር 2 ቀን 2007ዓ.ም ከቀኑ 5 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

No comments: