Wednesday, November 12, 2014

ምርጫ 2007 እና የ‹‹ተመራጩ›› አምባገነን ጉዞ



ጌታቸው ሺፈራው 

በየ ዘመኑ የመንግስት ስርዓቶች ይቀያየራሉ፡፡ የህዝብ አመለካከት አድማስና የሚፈልገው ስርዓትም እንዲሁ፡፡ ይህን ሁሉ በሚገባው መንገድ ለመምራት ደግሞ ገዥዎች ለወቅቱ ሁኔታ የሚያወጣቸውን የአገዛዝ ስርዓት ይዘረጋሉ፡፡ በተለይ ከህዝብም ሆነ ከሌላ አካላት ስልጣንና ህይወታቸውንም እያጡ የሚገኙት አምባገነኖችስልጣናቸውን ለማቆየት የሚደረግን ብልጣብልጥ መንገድ ሁሉ መከተላቸው የተለመደ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት ምርጫ ዘመናዊ ፖለቲካ መለኪያ ነው፡፡ ነገር ግን ምርጫ አምባገነኖችን ስልጣን የሚያሳጣ በመሆኑ በሙሉ ልባቸው ወደ ምርጫ መግባትን አይደፍሩም፡፡ ከዚህ ይልቅ በስመ ምርጫ፣ አምባገነንነታቸውን፣ አፋኝነታቸውን ያጠናክራሉ፡፡ እነዚህን አብዛኛዎቹ ብልጣብልጦች ምርጫን እየጠሉ በስመ ምርጫ ስልጣናቸውን የሚያራዝሙ አምባገነኖች ‹‹ተመራጭ አምባገነኖች›› ይሏቸዋል፡፡

ይህ አይነት ስርዓት ከአፍሪካዎቹ ዚምባብዌ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ዩናጋዳ እስከ ቱርክ ኢራንና ሩሲያ ድረስ ያለውን የብልጣብልጦች ‹‹መንግስት›› የሚያጠቃልል ነው፡፡ በእርግጥ በአፍሪካው በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ገዥው ፓርቲ ደህንነትና መከላከያ ሰራዊቱን በቀኝ እጁ ምርጫን ደግሞ በግራው አንጠልጥሎ ወደ ‹‹ምረጡኝ›› የሚገባበትና ያልፈለገው ነገር ሲከሰት ‹‹ጨዋታ ፈረሰ!›› የሚልበት በመሆኑ ‹‹ተመራጭ አምባገነን/አፋኝ›› የሚባለውን መስፈርትም ብዙም የሚያሟላ አይደለም፡፡ ብልጣብልጥነትን ይልቅ ግትርነት፣ ማን አለብኝነት፣ አሊያም እኔ ከሞት ሰርዶ አይብቀል አይነት የአህያዋ አስተሳሰብ የተጠናወተው ነው ማለት ይቀላል፡፡

ምርጫው ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው፣ በህዝብ ገንዘብ አባላት፣ ተለጣፊ ተቃዋሚዎችን፣ ሚዲያ አደራጅቶ አማራጭ አልባ ‹ተመራጭ›› ከመሆን እስከ ማጭበርበር፣ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ቢሸነፍ በሀይል የምርጫ ድምጽ በመንጠቅ ምርጫውን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የሚቆጣጠረው ስልጣን ላይ ያለው ‹‹ተመራጭ›› አምባገነን/አፋኝ ስርዓት አይነተኛ ባህሪ ነው፡፡

ህገ መንግስት፣ ፍርድ ቤት፣ ምርጫ ቦርድ፣ ሚዲያ (የግል የሚባሉትን ይጨምራል)፣ ተቃዋሚዎቹም እንዳይንቀሳቀሱ ነገር ግን ለእርዳታ ለጋሾች የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዳለ፣ ህዝብም አማራጭ እንዳለው ነገር ግን እንደማይመርጣቸው ለማሳየት ተቋማትን እያዳከመ ለመግዛት ይጥራል፡፡ እነዚህ ተቋማት ስርዓቱ የሚፈልገው ግብ ይደርስ ዘንድ የቲፎዞነት ሚና ከተወጡ ደግሞ በማያሸልመው እየሸለመ፣ በማያስደጉመው ተግባራቸው እየደጎመ በአሯሯጭነት ያስቀጥላቸዋል፡፡ ይህን በእኛ አገር በግልጽ የምናስተውለው ነው፡፡ ኢህአዴግ ፓርቲም መንግስትም ሆኖ የህዝብን ሀብት ‹‹የጋራ ምክር ቤት›› ውስጥ ተካተው ለምርጫው በአሯሯጭነት ለተሰለፉት፣ አብዛኛው የፓርቲው ካቢኔ በአንድ ሰው ለተያዘባቸው ፓርቲዎች ከ100 ሺህ እስከ 390 ሺህ ብር አከፋፍሏል፡፡ በምርጫ ሊቀናቀኑት የሚችሉትን ግን አመራሮቻቸውን እያሰረ፣ ጽ/ቤት እንዳያገኙ፣ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ እንዳያካሂዱ በሀይል እያገደ ከአሁኑ ምርጫውንና እድሜውን ለመወሰን እየጣረ ነው፡፡

እንደ አጠቃላይ ግን ተመራጭ አምባገነንነት/አፋኝነት በምርጫ ስም የሌለን ምርጫ ምርጫ እንዳለ፣ ያላሸነፉትን ምርጫ አጭበርብረውም ሆነ ድምጽ ቀምተው በህጋዊ መንግድ እንዳሸነፉ፣ ነጻ ያልሆኑትን ተቋማት ነጻ እንደሆኑ በማስመሰል ስልጣናቸውን በማራዘም የተካኑ ስርዓቶች መገለጫ ነው፡፡ ብልጣብልጥ ነው ባይባልም ኢህአዴግ ይህን ስልት በዋነኛነት እየተከተሉት ከሚገኙት አፋኞች መካከል የግንባር ቀደምነቱን ቦታ ለመያዝ እየተንደረደረ ነው፡፡


‹‹ተመራጩ›› ኢህአዴግና ምርጫ 2007

ለኢህአዴግ ምርጫ 2007 ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ወሳኝ ይመስለኛል፡፡ በአንድ በኩል ለዴሞክራሲ ጭላንጭል በር ከፍቶ የነበረው ምርጫ 97 በአሳዛኝ መልኩ ካለቀ በኋላ ህዝቡ ላይ የተፈጠረውን የምርጫ ፍዘት (apathy) በማጠናከር ነገር ግን ለተወሰነው የማህበረሰብ ክፍል በምርጫ የሚያምን፣ ተመርጦም የሚመራ ለማስመሰል ይጠቀምበታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኛውን በጀት የሚሰበስብበትን አሁን አሁን የኢህአዴግን ሪፖርት ሳይቀር (የኢኮኖሚ እድገት....የመሳሰሉትን የስታስቲክ ባለስልጣን የተጋገረ ሪፖርት) እንደሪፖርት ማየት የተገደደውን የ‹‹ዓለም አቀፍ›› ማህበረሰብ ለማሞኘትም ይጠቀምበታል፡፡ ምርጫ ለስልጣኑ አደጋ እንደሆነ በምርጫ 97 በደንብ ተምሮበታልና እውነተኛ ምርጫ ግን እንዲኖር ይፈቅዳል ማለት ዘበት ነው፡፡

ያም ሆኖ የ2007 ዓ.ም ምርጫ ለኢህአዴግ አስፈላጊ የሆነውን ያህል መስቀለኛ መንገድ ላይም የሚጥል ነው፡፡ በአንድ በኩል ቀደም ብሎ ያወጀውን የ‹‹አውራ ፓርቲ››ነት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም ዘንድ ‹‹ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ›› ያደረገ ተብሎ ቅቡልነት ለማግኘት ይጠቅመዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ህዝብንም ሆነ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን ‹‹ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ አድርጌ አሸንፌያለሁ›› ብሎ እንደሚያሞኘው ለምርጫ የሚያበቃ ምህዳር መዘርጋቱ እራሱን አጋልጦ መስጠት ይሆንበታል፡፡

በመሆኑም በህዝቡም ሆነ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ቢቻል ነጻና ፍትሃዊ የሚመስል ‹‹ምርጫ›› እንዲኖር ይፈልጋል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ነጻና ፍትሃዊ በሚመስል ምርጫ ውስጥም አደጋ የሚያደርሱበት አካላት ላይ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለበት፡፡ ለገዥው ፓርቲ በምርጫው ቀጥተኛ አደጋዎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ከፓርቲዎቹ ባሻገር ሲቪክ ማህራት፣ ሚዲያ፣ ነጋዴው ማህበረሰብ፣ ሌላው ህዝብ፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በምርጫው ወቅት ተጽዕኖ ከማሳደር ጀምሮ ለስልጣኑ አደጋ አድርጎ ይቆጥራቸዋል፡፡ ነገር ግን ዋነኛዎቹ ተቀናቃኞች ተቃዋሚዎች እንደመሆናቸው ትልቁን ስራ የሚሰራው በእነሱ ዙሪያ ነው፡፡

ተቃዋሚዎቹ በምርጫ 1997 ኢህአዴግን ካስበረገጉት ማግስት ኢህአዴግ መስራት የጀመረው ‹‹ተቃዋሚዎችን ከህዝብ መነጠል፣ ተቃዋሚዎችን ራቁታቸውን ማስቀረት.....›› በሚል አዲስ ‹‹ስልት›› ነው፡፡ በምርጫ 97 ሲቪክ ማህበራት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ለምርጫ ስርዓቱ የራሳቸውን አስተዋጽኦ በማድረጋቸው ምርጫ 97 በኋላ እነሱን የሚያስቆምበት መላ ዘየደ፡፡ የሲቪህ ማህበራት አዋጅ በመሳሪያነት የተጠቀመበት አንዱ ስልት ነው፡፡ ሲቪክ ማህበረሰቦች ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ፣ ኢኮኖሚና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ቢኖርም ይህ ሁሉ ከስልጣኑ የማይበልጥበት ገዥው ፓርቲ በአዋጁ መሰረት እንዳይንቀሳቀሱ በማገድ ‹‹ተቃዋሚዎችን ራቁታቸውን›› የሚያስቀርበት እንደ አንድ ትልቅ ስልት ወሰደው፡፡ በእርግጥ ይህ ከስልጣን ጥማት የመነጨው የገዥው ፓርቲ ስልት ተቃዋሚዎቹን ብቻ ሳይሆን አገሪቱንም ጭምር ራቁቷን የማስቀረት ስልት ነው፡፡

ሚዲያ ተቃዋሚዎች መግለጫ የሚያወጡበት፣ ፖለቲከኞች በቃለ መጠይቅም ሆነ በአስተያየት መልክ ሀሳባቸውን ለህዝብ የሚያደርሱበት፣ ስለ ፓርቲዎችና እንቅስቃሴዎቻቸው ዜናዎች የሚተላለፉበት በመሆኑ ኢህአዴግ የተቃዋሚዎች ጋሻ አድርጎ ይወስዳቸዋል፡፡ ከዚህ አለፍ ሲል ደግሞ ልሳኖቻቸው አድርጎ ይከሳቸዋል፡፡ በመሆኑም የሚዲያ አዋጅ በማውጣት ሚዲያዎቹ በስርዓቱ ላይ ጠንከር ያለ ትችት እንዳይሰነዘር በስም ማጥፋትና በመሳሰሉት ማጥመድ ጀመረ፡፡ ይህ አልበቃ ሲልም ጋዜጠኞችን በማስፈራራት አገር ጥለው እንዲሰደዱ አደረገ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ማተሚያ ቤት እንዳያገኙ ተደረገ፡፡ በቅርቡ ደግሞ የራሱን መዋቅር በማደራጀት በተለይ የግል ጋዜጦችና መጽሄቶች ወደ ክፍለ ሀገር እንዳይከፋፈሉ አከፋፋዮችን በራሱ አደረጃጀት ማዋቀሩ ተሰምቷል፡፡ ይህ አማራጭ መረጃን ለህዝብ የሚያደርሱ ሚዲያዎችን በማፈን ተቃዋሚዎችን ‹‹ራቁታቸውን የማስቀረት›› ለ40ና 50 አመት የታቀደው የ‹‹አውራነት›› በአጭር ጊዜ ደግሞ የ2007 ቅድመ ዝግጅት አንዱ አካል ነው፡፡

ይህ ሁሉ ግን በቂ አይደለም፡፡ ጋዜጠኞችን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራርና አባላትን፣ የሲቪክ ማህበራትና የኃይማኖት መሪዎችን፣ አርሶ አደሮችን፣ ነጋዴዎችን፣ መምህራንን፣ ተማሪዎችን.....በአጠቃላይ ከተቃዋሚዎች ጋርም ሆኖም ይሆን በግል ስርዓቱን የተቃወመ አሊያም ይቃወማል ተብሎ የታሰበን ‹‹ከህዝብ የሚነጥልበት›› አዋጅ አስፈላጊ ነበር፡፡ ለዛም ሲባል የጸረ ሽብር ህጉ ወጣ፡፡ በዚህ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር፣ ጋዜጠኛ፣ የኃይማኖትና የሲቪክ ማህበረሰብ መሪ፣ አርሶ አደር ‹‹አሸባሪ›› ተብሎ በሚከሰስበት ህግ በርካቶች ለእስር ተዳርገዋል፡፡

በአንጻሩ በዚሁ ህግ የታሰሩት አውሮፓውያን በወራት ውስጥ ተለቀዋል፡፡ ምንም ለውጥ አያመጡም የተባሉት የተገንጣይ ቡድን አባላት በፓርላማ አሸባሪ ተብለው አዋጁ ይቅርታ የሚሰጥበት ምንም አንቀጽ ሳይኖረው፣ ፓርላማውም ‹‹አሸባሪነታቸውን›› ሳይሽር በጓዳ እርቅ ወደ አገር ቤት ገብተዋል፡፡ በዚህ ህግ የከሰሷቸውን እነ አንዳርጋቸው ጽጌን በሚሊዮን ዶላር ከየመን እንዳላመጡ በድንገት አዲስ አበባ የተገኙትን ‹‹አሸባሪዎች›› በ24 ሰዓት ‹‹ውጡልን!›› ብለው ለምነዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው አዋጅ፣ ህግ....ተብሎ ለስርዓቱ መግዢያ መሳሪያ፣ መጠቀሚያና ያለ አማራጭ ‹‹ማስመረጫ›› መሆኑን ነው፡፡

የጸረ ሽብር አዋጅ ከየትኛውም አዋጅ በላይ ‹‹ተቃዋሚዎችን ራቁታቸውን ማስቀረት›› የተሰኘውን የኢህአዴግ ስልት ለማስፈጸም መጠቀሚያ መሳሪያ ሆኗል፡፡ እነ አንዱዓለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ አበበ ቀስቶ፣ .... ተቃዋሚዎቹ ጋር እየሄደ ስለ ሰላማዊ ትግል ያስተምር የነበረውና ስለ ለውጥ ትንታኔ የሚሰጠው እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታየ፣ ርዕዮት ዓለሙ...... በማሰር ተቃዋሚዎችን ራቁት የማስቀረት ስልት ለመተግበር ሞክሯል፡፡ የተቀውሞ ጎራው፣ ሚዲያው ተቀዛቀዘ ሲባል እንደገና ሲጠናከር ደግሞ ሀብታሙ አያሌው፣ አብርሃ ደስታ፣ የሽዋስ አሰፋ፣ ዳንኤል ሺበሽ፣ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንና ጋዜጠኞችን አስሮበታል፡፡ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ደግሞ በየ ክፍለ ሀገሩ የሚገኙ የአንድነት፣ የመኢአድ፣ የሰማያዊና የአረናን ጠንካራ አመራሮችና አባላት በጸረ ሽብር ህጉ እየከሰሰ እያሰረ ይገኛል፡፡ አዲስ አበባም ሆነ በየ ክፍለ ሀገሩ የሚገኙ ጠንካራ አባላትንና አመራሮች ላይ የሚደረገው እርምጃ አሁንም እንደሚቀጥል ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ምርጫ የሚመስል ምርጫ አካሂዶ በህዝብ ዘንድም ሆነ በለጋሾች ‹‹ተመራጭ›› ለመምሰል ነው፡፡

የቀድሞው የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ድኤታ አቶ ኤርምያስ ለገሰ በመጽሃፉም ኢህአዴግ በ1997 ውድድሩን ቀድሞ ክፍት ማድረጉ በአመራሩ ዘንድ ስህተት መሆኑ እንደታመነበት ጽፏል፡፡ ምርጫ 2007 ዓ.ም እንደ 1997 ዓ.ም ይሆናል ባይባልም ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜም (ለአንድ ሳምንትም ይሁን ወር) ምርጫውን ምርጫ ለማስመሰል የተወሰኑ ክርክሮች እንዲኖሩ ማድረግ፣ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባዎችን በመጠኑ መፍቀዱ የማይቀር ነው፡፡ በእነዚህ ቀናትም ቢሆን ግን በተለያዩ ብሶቶች የተወጠረው ህዝብ በእሱ ላይ እንደሚነሳበት ያውቃል፡፡ በመሆኑም እስከዛው ህዝብን ያደራጃሉ የሚባሉት ተቃዋሚዎች መዳከም (ራቁታቸውን መቅረት) አለባቸው፣ ሚዲያዎችም ከገበያ መውጣት ይገባቸዋል፡፡ በእነሱ ምትክ ደግሞ ስመ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ እየተከፈላቸው ተቃዋሚዎችን የሚያብጠለጥሉ ሚዲያዎች ወደ ገበያው እንደሚመጡ ይደረጋል፡፡ እንዲህ ከሆነ ብቻ ነው ኢህአዴግ ‹‹ተመርጦ›› ለቀጣዮቹ 40ና 50 አመታት ሊገዛ የሚችለው፡፡ ይህ ደግሞ ኢህአዴግ ከአቶ መለስ የወረሰው እውነተኛውን አማራጭ አሳጥቶ በግድ የመመረጥ የ‹‹ተመራጭ›› አፋኝነት ‹‹ሌጋሲ›› ነው፡፡ እነ ሙባረክ፣ ቤል አሊ፣ ኮምፓወሬ በዚህ ብልጣብልጥነት በርከት ላሉ ጊዜያት ስልጣን ላይ ቆይተው በመጨረሻ ያላሰቡት ደርሶባቸዋል፡፡ ከብልጣብልጥነት ይልቅ ግትርነቱ የሚያጠቃው የኢህአዴግ እንደሌሎቹ ‹‹ቀን እስኪጥለው›› ድረስ የ‹‹ተመራጭ›› አፋኝነቱ ጉዞ እንደቀጠለ ነው፡፡ እንደ ‹‹ተመራጩ አፋኝ›› ስርዓት እቅድ ከሆነ ደግሞ ለ50 አመታት ይቀጥላል፡፡

Source: Negere Ethiopia

No comments: