በ2005 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ይኖሩ የነበሩ የአማርኛ ተናጋሪዎች ላይ ህገ ወጥ የሆነ ማፈናቀል ተፈጽሞባቸዋል፣ ንብረታቸው ወድሟል በሚሉ እና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ በሰማያዊ ፓርቲና በአንድነት ፓርቲ አሳሳቢነት በእነ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም እና በአቶ ዓለሙ ጌቤቦ ክስ የተመሰረተባቸው የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ እና የመተከል ዞን ላይ የተመሰረተው ክስ ዛሬ ጥቅምት 28 ቀን 2007 ዓ.ም በልደታ የፌደራል ፍታብሄር ችሎት ቀጥሎ ውሏል፡፡
በዛሬው የፍረድ ቤት ውሎ ተከሳሾች የቀረበባቸው ክስ አግባብ እንዳልሆነ በማውሳት ክሱ እንዲነሳላቸው ጠይቀው የነበር ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበላቸው እንደቀረ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ለጥር 15/2007 ዓ.ም በተከሰሱበት ጉዳይ ላይ መልስ እንዲሰጡ አዝዟል፡፡
ክሱ የተመሰረተው ባለፈው ዓመት 2006 ዓ.ም መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ የክሱ ይዘት ተብራርቶ መቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ‹‹ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው ባስቸኳይ ይመለሱ፣ ለጠፋው ንብረትና ጉዳትም ካሳ ይሰጣቸው›› የሚል አቤቱታ መቅረቡንም ጉዳዩን የሚመሩት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም ለነገረ ኢትዮጵያ አስረድተዋል፡፡
የተፈጸመው የማፈናቀል ተግባር የኢትዮጵያን ህገ መንግስትም ሆነ ዓለም አቀፍ ህግጋትን የጣሰ ነው ያሉት ዶ/ር ያዕቆብ፣ አሁን የተመሰረተው ክስ ለውጤት ከበቃና ፍርድ ቤቱ ለተፈናቃዮች ከወሰነላቸው ከዚህ በፊት በተመሳሳይ በደል የደረሰባቸው ዜጎችም ፍትህ እንዲያገኙ በር የሚከፍት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
No comments:
Post a Comment