Wednesday, November 26, 2014

በማስፈራራትና በአፈና ትግሉ እንደማይቆም የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር አስታወቀ



• አመራሩ ድብደባ እንደተፈጸመበት ገልጾአል
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
የአንድ ወር የትግል መርሃ ግብር ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎችና ህዝባዊ የለውጥ ንቅናቄዎችን በገዥው ፓርቲ አፈና እና ማስፈራሪያ እንደማይቆም ትብብሩ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
ህዳር 7/2007 ዓ.ም የትብብሩ ህዝባዊ የአደባባይ ስብሰባ በኃይል መበተኑን፣ ይህንኑ አስመልክቶ ህዳር 7/2007 ዓ.ም ለሰማያዊ ፓርቲ ማስጠንቀቂያ መጻፉን እና ለህዳር 21 ለሚደረገው ስብሰባ የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ደብዳቤ በፖስታና በአካል ቢላክለትም ማሳወቂያ ክፍሉ አልቀበልም ማለቱን የገለጸው መግለጫው ስርዓቱ የትብብሩን የትግል መርሃ ግብር ለማስቆም እየጣረ መሆኑን ገልጾአል፡፡
በተጨማሪም የትብብሩ አንድ አባል እና ትብብሩ ህዳር 21/2007 ዓ.ም የሚያደርገውን የአደባባይ ስብሰባ የሚያስተባብረው መኢዴፓ ሊቀመንበርና የትብብሩ ገንዘብ ያዥ የሆኑትን አቶ ኑሪ ሙደሲር ላይ የድብደባ ወንጀል እንደተፈጸመባቸው አመራሩ ገልጸዋል፡፡
ትብብሩ በዛሬው ዕለት ‹‹ማስፈራራትና አፈና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችንና ሠላማዊ ሕዝባዊ የለውጥ ንቅናቄዎችን አይቀለብስም›› በሚል በሰጠው መግለጫ የተገኙት አቶ ኑሪ ሙደሲር ከሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ ወከባ እንደተፈጸመባቸው ገልጸዋል፡፡
አቶ ኑሪ ‹‹መኪናችን ገጨህብን ባሉ 10 ሰዎች ነው የተደበደብኩት፡፡ ከአሁን ቀደምም ፖሊሶች ምንም አይነት ችግር ሳላደርስ ገጨህብን ብለው አዋክበውኛል፡፡ ሰሞኑን መኪናዬን ቢሰብሩብኝም በስህተት የተመታ መስሎኝ ነበር፡፡ አሁን ከደበደቡኝ መካከል ተክለኃይማኖት አካባቢ የሚገኙ ካድሬዎችና ደንብ አስከባሪዎች ይገኙበታል፡፡ መጀመሪያ ላይ ፖሊሶች ‹ቢገጭስ እንዴት 10 ሆናችሁ አንድ ሰው ትደበደርባላችሁ?› ካሉ በኋላ እንደገና ካድሬዎች መሆናቸውን ሲያውቁ እነሱን ትተው እኔን ይወቅሳሉ፡፡ ይህም የሚያሳየው ሆን ተብሎ የተደረገ ነገር መሆኑን ነው›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ህዳር 21/2007 ለሚደረገው የአደባባይ ስብሰባ በአካልም ሆነ በፖስታ ደብዳቤ ቢላክም የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍሉ ባለመቀበሉ የትብብሩ ደብዳቤ በፋክስ እንዲደርሰው እንደተደረገ የትብብሩ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ገልጸዋል፡፡
ሆኖም በፋክስ የተላከውን ደብዳቤ አልቀበል ካለ የትብብሩ አመራሮች በጋራ ደብዳቤውን ለማድረስ እንደሚሄዱ፣ የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍሉ ይህንም አልቀበልም ካለ ሁነቱን በቪዲዮና በፎቶ በመቅረጽ ለህዝብ በማሳወቅ ስብሰባውን እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ በሂደቱም የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል እንደተዘጋጁ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ገልጸዋል፡፡

No comments: