Sunday, December 15, 2013

አቶ ልደቱ ወደ ፖለቲካ ተመለሱ

አቶ ልደቱ ወደ ፖለቲካ ተመለሱ
ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቢሆንም ግን ፈተናውን ወድቋል የሚሉት አቶ ልደቱ አያሌው፤ የኢኮኖሚ እድገቱን መካድ ስህተት ነው፤ እድገቱ ዘላቂነት እንደሌለው አለመገንዘብም ስህተት ነው በማለት የኢዴፓ “ሦስተኛ አማራጭ” የተሰኘ የኢዴፓ አቋምን ይተነትናሉ፡፡ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች መዳከም አንዱ ምክንያት የመንግስት ተጽእኖ እንደሆነ አቶ ልደቱ ገልፀው፤ ነገር ግን ህዝቡን አሰባስቦ በመታገል የመንግስትን ተጽእኖ ማስቆምና ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ይልቅስ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ለመፈተሽና ስህተታቸውን ለማረም አለመዘጋጀታቸው ትልቅ እንቅፋት ሆኗል ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ፣ በጭፍን ድጋፍና በጭፍን ተቃውሞ ለሁለት ስሜታዊ ጽንፎች ፖለቲካ እንደሰፈነ ጠቅሰው፤ ስር የሰደደውን የተሳሳተ የጽንፍ አስተሳሰብ በምክንያታዊ አስተሳሰብ በመተካት ሦስተኛ አማራጭ መያዙ ለአገሪቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ይላሉ፡፡ ከ1997 ወዲህ የአገሪቱ ፖለቲካ ቁልቁል እየተንሸራተተ በ15 አመት ወደኋላ መመለሱን ሲያስረዱ፤ አሁንም ከደጡ ወደ ማጡ እንዳይሰምጥ፣ ከዚያም ወደፊት እንዲራመድ ቁልፍ ያለው በገዢው ፓርቲ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በህዝቡ ዘንድ ነው ብለዋል አቶ ልደቱ፡፡ አቶ ልደቱ እነዚሁ 3 ቁልፍ አካላት ካሁን በፊት ምን ስህተት እንደሰሩና ወደፊት ምን እንደሚጠበቅባቸው ከመተንተን በተጨማሪ፤ ለበርካታ ጉዳዮች ላይ የሰነዘሩትን ሃሳብ በዚህ ቃለ ምልልስ እናቀርባለን፡፡
አቶ ልደቱ ለረጅም ጊዜ ጠፍተዋል..ከፓለቲካውም ከሃገሪቱም.. 
ከመገናኛ ብዙሃን ትንሽ ራቅ ስላልኩ የጠፋሁ ይመስላል፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት ለትምህርት ከኢትዮጵያ ውጪ ነው የነበርኩት፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ከሃያ አምስቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አንዱ ብሆንም፣ በጠቅላላ ጉባኤ ከሊቀመንበርነት ስለወረድኩ የፓርቲው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አልመራም፡፡ በነዚህ ምክንያቶች ከመገናኛ ብዙሃን ርቄያለሁ፡፡ ከኢትዮጵያ ፓለቲካ ግን አልራቅኩም፡፡ አሁን ትምህርቴን አጠናቅቄ እዚሁ አገሬ እየኖርኩ ነው፡፡ 
የነበሩበት ትምህርት ቤት ምንድን ነበር የሚባለው… 
ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ኦፍ ለንደን ውስጥ፤ ስኩል ኦፍ ኦሬንታል ኤንድ አፍሪካን ስቴዲስ የሚባል አለ፡፡ እዚያ ነው ዲቨሎፕመንት ስተዲስ ያጠናሁት፡፡ 
ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ ኢዴፓ ‹‹ሶስተኛ አማራጭ›› የሚል ሃሳብ ይዟል፡፡ ይሄ ሃሳባችሁ ከምን አደረሳችሁ? 
‹‹ሶስተኛ አማራጭ›› የምንለውን ነገር በአግባቡ ያለመረዳት ነገር አለ፡፡ እኛም በበቂ ሁኔታ አላስረዳን ሊሆን ይችላል፡፡
ሶስተኛ አማራጭ ሲባል፣ ልዩ የርዕዮተ አለም መስመርን ለመግለጽ ሳይሆን፣ የአቀራረብና የስልት ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፓለቲካ፣ እስከ አሁን ድረስ ሁለት ፅንፍ የያዘ ነው። ሁለትም ነገር መደገፍ ወይም ሁሉንም ነገር መቃወም፡፡ የገዥው ፓርቲ አባል ከተሆነ፤ ተቃዋሚ የሚሰራውን ነገር ሙሉ በሙሉ ማጥላላት፤ የተቃዋሚ አባል ከተሆነ ደግሞ መንግስት የሚሠራውን ነገር ሁሉ መቃወም፡፡ እንዲህ ሁለት ጫፍ የያዘ አሰላለፍ፤ ለአገራችን ፖለቲካ አልጠቀመም፡፡ ከመቻቻል ከመደማመጥ አርቆናል፡፡ ለዚህም ነው፤ ከሁለቱ ጽንፎች የተለየ አማራጭና የተለያየ አቀራረብ ያስፈልጋል የሚል አስተሳሰብ ይዘን የመጣነው፡፡ በመንግስትም ሆነ በተቃዋሚ የተሠራ ነገር ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም ከሆነ ልንደግፈው ይገባል፡፡ የማይጠቅምና የሚጐዳ ከሆነ ደግሞ በተጨባጭ መረጃ መቃወምና እንዲቀየር መታገል ያስፈልጋል፡፡ በስሜታዊ ጽንፍ ሳይሆን በምክንያታዊ አስተሳሰብ ነው ፖለቲካው ሊመራ የሚገባው፡፡ አለበለዚያ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደ ዲሞክራሲያዊ የመቻቻል ባህል ሊቀየር አይችልም። ሁለት ስሜታዊ ፅንፎችን ይዞ፣ ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ፣ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ነው የሚያዋጣን ብለን ሶስተኛ አማራጭ ይዘናል፡፡ ይሄንን አቀራረብ ይዘን ስንመጣ ፈተናዎች ገጥመውናል፡፡
ሁለቱ ጽንፎች ለረዥም ጊዜ ስር የሰደዱና የከረሩ ስለነበሩ፣ ብዙ ሰዎች የእኛን አስተሳሰብ ለመቀበል በጣም አስቸግራቸዋል፡፡ ደግሞም አያስገርምም፡፡ ሰዎች በቀላሉ ይሄን አስተሳሰብ የሚቀበሉ ከሆነ፤ ከመነሻው የአገራችን ፖለቲካ ከባድ ችግር የለበትም ማለት ነው፡፡ የአገራችን ፖለቲካ ግን ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ትልቅ ችግር አለበት፡፡ ስለሆነም፤ ሦስተኛ አማራጭ ብለን ያቀረብነው የምክንያታዊ አስተሳሰብ አቅጣጫችንን ብዙ ሰዎች በቀላሉ ሊቀበሉት አልቻሉም። “ተቃዋሚ ከሆንክ በቃ ማንኛውንም ነገር ትቃወማለህ፡፡ ኢህአዴግም ከሆንክ ማንኛውንም ነገር ትደግፋለህ፤ ሌላ ሦስተኛ አማራጭ የለም” የሚል የተዛባ አመለካከት ይሰነዘርብን ነበር፡፡ “እንዲያውም ሦስተኛው አማራጭ የምትሉት ነገር ወላዋይነት ነው” በማለት ውዥንብር የመፍጠር ነገርም ነበር። በሂደት ግን፣ ብዙ ሰው ጉዳዩን እያብላላው፣ እያጤነውና እየተገነዘበው እንደሆነ አይተናል፡፡ እኛ በምንፈልገው ፍጥነት ህብረተሰቡ ተረድቶታል የሚል እምነት የለንም፡፡ ገና ብዙ ይቀራል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እስከአሁን በመጣበት የጽንፈኝነት መንገድ የትም ሊያደርሰን እንደማይችል ብዙዎች እየገባቸው ነው፡፡ ሁለቱ ጽንፎች የሚፈጥሩት ቅራኔና ውጥረት፣ ከዴሞክራሲ እያራቀን እንጂ ወደ መቻቻል እያመጣን እንዳልሆነ ሰው እየተገነዘበው ነው፡፡
“ሁለቱ የፅንፍ ሃይሎችና ጐራዎች አይጠቅሙም ትክክል አይደሉም” የሚለው አስተሳሰብ እየጐላ መጥቷል፡፡ “ሁለቱም ፅንፎች አይጠቅሙም፤ ችግር አለባቸው” ከተባለ ክፍተት መኖሩን ነው የሚያሳየው፡፡ ያንን ክፍተት የመሙላት ጉዳይ ነው የሶስተኛው አማራጭ ፋይዳ፡፡ ይሄንን አስተሳሰብ ይዘን እንደነበር በተለይ በፓርላማ በነበረን ተሳትፎ በደንብ ማሳየት ችለን ነበር፡፡ ፓርላማ ውስጥ ሌሎች ተቃዋሚዎች ከሚያራምዱት አስተሳሰብ በተለየ ሁኔታ፣ መንግስት ከሚሠራቸው ነገሮችና ከሚያራምዳቸው አቋሞች ውስጥ ለህዝብና ለሀገር የሚጠቅም ነገር ስናገኛቸው በድፍረት ስንደግፍ ታይቷል፡፡ ሰው ለዛ የሚሠጠው ትርጉም ምንም ይሁን እኛ ለሀገርና ለህዝብ ይጠቅማል ብለን እስካመንበት ድረስ በድፍረት ወጥተን፤ ይሄ አቋም ከገዢው ፓርቲም ይምጣ ከተቃዋሚ ፓርቲም ይምጣ ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ እንደግፋለን ብለን ማሳየት ችለናል፡፡ ገዢው ፓርቲ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችን ሲሰራ ደግሞ ከሌሎች ተቃዋሚዎች በበለጠ በመረጃ በተደገፈ ከመተቸትና በጠነከረ መልኩ በመታገል ምክንያታዊነታችንን ማሳየት ችለናል፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥም ጥፋት ወይም ድክመት ሲኖር፣ ተቃዋሚ ነውና እሱን አንነካውም አንልም፡፡ እንዲስተካከል እንተቻለን፡፡ ለሰላማዊ ትግልና ለአገር የማይበጅ፣ ለመቻቻል ፖለቲካ ማይጠቅም ሆኖ ካገኘነው፣ ተቃዋሚውንም ቢሆን በድፍረት የመተቸት አዲስ ባህል ይዘን መጥተን አሳይተናል፡፡ ያን የማይወዱ ሰዎች ብዙ ነበሩ፡፡
በሂደት እየተረዱ ሲመጡ፣ ግን እኛ የያዝነው አቋም ትክክል እንደሆነ መገንዘብ የቻሉ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ ይሄ አቋማችን በአገራችን ያልተለመደ አዲስ አቋምና አካሄድ ስለሆነ፤ አንዳንድ ሰዎች በእኛ ላይ የሚያወሩትን አሉባልታ ማራገብ ተጠቅመውበታል። በእኛ ላይ ከንቱ ጥርጣሬና ጥላቻ እንዲስፋፋ በማድረግ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፈዋል። በሌላ በኩል ግን ከነባሩ የጽንፈኝነት ፖለቲካ የተለየ ምክንያታዊ ፖለቲካ ማራመድ ለዚህ አገር እንደሚያስፈልግ በደንብ ለማሳየት ችለናል፡፡ ስለዚህ ሦስተኛ አማራጭ ይዘን መምጣታችን፣ ጥቅምም ጉዳትም ነበረው፡፡ ከአጭር ጊዜ አንፃር፣ ሊያስወድድ የሚችል የፖለቲካ አቋም አልነበረም፡፡ ለአሉባልታ አጋልጦናል፡፡ ከረጅም ጊዜ አንፃር ግን ይሄ ምክንያታዊ የፖለቲካ መስመራችን እየሰፋና እያደገ፣ በተለይ በአዲሱ ትውልድ ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ የሚመጣ አቋም ነው፡፡ ስለዚህ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የበለጠ እየተጠናከረ ነው፡፡ ግን ሂደቱን እኛ ስለተናገርነውና ስላራመድነው ብቻ ውጤት ያመጣል ማለት አይደል፡፡ ከአጠቃላይ ከአገራቱ ሶሽዬ ኢኮኖሚክ የእድገት ደረጃ ጋር ተያይዞ ነው ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችለው፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወጥቶ ስለተናገረ ብቻ፣ የበቃ የፖለቲካ አመለካከት ያለው ህብረተሰብ ይፈጠራል ማለት አይደለም፡፡ እንደዛ አይነት ህብረተሰብ የሚመጣው ኢኮኖሚያችን ሲያድግና ሲዳብር፤ ትምህርት ሲስፋፋና ከሌላው አለም ጋር መስተጋብራችን የበለጠ ሲጠናከር ነው፡፡ በአጭር ጊዜ የሚቀየር ነገር አይደለም፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ እውን የሚሆንበት ሂደት በጣም የተራዘመ እንዳይሆንና እንዲፋጠን በማድረግ ረገድ ግን የኢዴፓ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
እንግዲህ መንግስት ኢኮኖሚው በደብል ዲጂት እያደገ መሆኑን ይገልፃል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የህብረተሰቡ ኑሮ ግን መንግስት ከሚገልፀው የተለየ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ምን ይላሉ? 
ኢኮኖሚውን በሚመለከት፣ የኛ አመለካከት ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይለያል፡፡ በመጀመሪያ እድገት አለ ብለን እናምናለን፡፡ ነገር ግን መንግስት ሁሌም በሚናገረው መጠን ደብል ዲጂት እድገት አለ ብለን አናምንም፡፡ አንዳንድ አለማቀፍ ድርጅቶች እንደሚገልፁት እድገቱ ወደ ስምንት ሰባት ፐርሰንት አካባቢ ሊሆን ይችላል ብለን እናምናለን፡፡ አቅሙን ለመናገር የሚያስችል በቂ መረጃ በእጃችን የለም፤ ሊኖረንም አይችልም፡፡ ነገር ግን ከአጠቃላይ ግንዛቤ ተነስተን ስናየው፤ መንግስት ከበታች አካላት እያገኘ ያለው መረጃ ትክክል ነው ብለን አናምንም፡፡ በብዙ ምክንያቶች የተዛባ መረጃ ነው ከታች ወደ ላይ የሚመጣው፡፡ የሚመጣውን ዳታ አምኖ መቀበል ያስቸግራል፡፡ በዚህ ምክንያት ፓርላማ በነበርኩበት ጊዜ፣ የመረጃ ምርምራ ወይም ኦዲቲንግ ሲስተም ያስፈልገናል እል ነበር፡፡ የገንዘብ እና የአሠራር ኦዲቲንግ ብቻ ሳይሆን የመረጃዎች ትክክለኛነት ለመፈተሸ ኦዲት መደረግ አለበት የሚል ሃሳብ ስናነሳ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ይሄን ሃሳብ የሚቀበለን አልነበረም፡፡ አሁን ግን መረጃዎችን ኦዲት ማድረግ አለብን የሚል ሃሳብ በመንግስት እየተነሳ እያየን ነው፡፡ ይሄ የኢኮኖሚ እድገት አለ የሚባለው፡፡ መኖሩ ጥር ጥር የለውም፡፡ በምን ይገለፃል? ስለመኖሩ ህብረተሰቡ ውስጥ የምናያቸው እንቅስቃሴዎች በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የልማቱን እንቅስቃሴ እንውሰድ፡፡ በመንግስት በኩል ከፍተኛ መዋለ ንዋይ እየፈሰሰ መሠረተ ልማት እየተስፋፋ ነው፡፡ ይሄ በየትም አገር ቢሆን የኢኮኖሚ እድገትን ያመጣል፡፡ የግሉ ክፍሉ ኢኮኖሚ ከድሮ በተሻለ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍም በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ከፍተኛ የግንባታ እንቅሰቃሴ አለ፡፡ እንዲያም ሆኖ እድገቱ ሙሉ በሙሉ ጤናማ ነው ማለት አይደለም፡፡ ችግሮች የሉበትም ማለት አይደለም፡፡ ዕድገቱ መንግስት በሚለው መጠን ነው ማለት አይደለም፡፡
የእድገቱ መጠን መንግስት እንደሚለው ሳይሆን፣ ስምንትና ሰባት ፐርሰንት ይሆኖል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄም ቢሆን መጥፎ እድገት አይደለም፤ ጥሩ እድገት ነው፡፡ በእርግጥ በኢትዮጵያ ደረጃ ላለ ድሃ አገር ከስድስት ፐርሰንት በታች የወረደ እድገት፤ ኢኮኖሚው እንደተኛ (ሪሴሽን ውስጥ እንደገባ ነው የሚቆጠረው፡፡ በጣም በከፍተኛ ደረጃ ማደግ ነው የሚጠበቅብን፡፡ የሌሎችም አገራትም ታሪክ ያንን ነው የሚያሳየው፡፡ እንደ አሜሪካና እንደ እንግሊዝ አገር አይነት ትልቅ ኢኮኖሚ ውስጥ ሶስትም አራትም ፐርሰንት ማደግ ከባድ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ኢኮኖሚ ተይዞ ግን፤ ደብል ዲጂት ማደግ ይቻላል፡፡ መጣ የሚባለው እድገት በህብረተሰቡ ህይወት ውስጥ መታየት አልነበረበትም ወይ? ሊታይም ላይታይም ይችላል፡፡ አንድ ኢኮኖሚ ማደግ ሲጀምር ሁሉንም ህብረተሰብ ይጠቅማል ማለት አይቻልም፡፡ ይሄ በየትም አገር ሆኖ አያውቅም፡፡ እንኳን ዘጠና ሚሊዬን ህዝብ ያለበት አገር ይቅርና፣ 3ሚሊዮን ህዝብ ባለበት አገርም ኢኮኖሚው ማደግ ሲጀምር ሁሉም ህብረተሰብ ተጠቃሚ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ ቀስ በቀስ ነው ተጠቃሚው እየበረከተና እያደገ የሚመጣው፡፡ ስለዚህ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ድህነት ይታያል። ድህነት ብቻ አይደለም በርሃብም የሚሰቃዩ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች መኖራቸው ግን እድገት የለም ወደሚለው ድምዳሜ አይወስደንም፡፡ እድገትም ባለበት አገር ሰው ይራባል፤ ሰው በድህነት ይማቅቃል፡፡ እንኳን በእኛ በጀማሪ አገር ቀርቶ፣ የዳበረ እድገት አላቸው የሚባሉ አገሮችም የሚቸገሩ ሰዎች አሉ፡፡
እነዛ ሰዎች ስላሉ ግን ያ አገር አላደገም ማለት አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ የካፒታሊስት (የነፃ ገበያ) ስርዓት ውስጥና በአንድ ጊዜ ሃብት በእኩል መጠን ሊዳረስ አይችልም፡፡ በሂደት ነው፡፡ እንግዲህ የመንግስት ሚና እዚህ ላይ ነው የሚጠበቀው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እድገት መኖሩ ጥርጥር የለውም፡፡ ዋናው ችግር ሌላ ነው። አሁን የምናየው እድገት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ መሠረታዊና መዋቅራዊ ለውጥ ሚያመጣ ነው ብዬ አላምንም ዘላቂነት የለውም፡፡ አሁንም የዝናብ እርሻ ጥገኛ ነኝ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ኢኮኖሚ ዘላቂ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ባለፉት ሃያ ዓመታት፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ በተለይ ማኑፋክቸሪንግ ተረስቶ ነው የኖረው፡፡ እኛ ለኢንዱስትሪው ትኩረት መስጠት እንዳለበት ስንናገር አይቀበሉንም ነበር፡፡ በእርግጥ ለእርሻው ትኩረት መስጠት ተገቢ ነው፡፡ የግድ ነው፡፡ ሰማንያ በመቶ ህዝብ በእርሻ ላይ ጥገኛ ሆኖ እርሻውን መዘንጋት አይቻልም፡፡ ግን በተመሳሳይ ሁኔታ ለኢንዱስትሪውም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ፤ ኢኮኖሚው በየዓመቱ ከእርሻ ጥገኝነትን ወደ ኢንዱስትሪው እስካልተሸጋገረ ድረስ፣ የኢኮኖሚ እድገቱ ዘላቂነት አይኖረውም፡፡ በዚህ ከተመዘነ የአገራችን ኢኮኖሚ ፈተናውን ወድቋል፡፡ ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ ወዲህ የገበሬ መጠን ምን ያህል ቀነሰ ብትይ፣ ከሶስት ፐርሰንት በላይ አልቀነሰም፡፡ አሁንም የእርሻ ጥገኛ ነን፡፡ አጭሩ መዋቅራዊ የሆነ ለውጥ አላመጣም፡፡ ግን እድለኞች ሆነን፣ በአለፉት ዘጠኝና አስር ዓመታት ጥሩ ዝናብ አለ፡፡ ይሄ ዝናብ ቢቋረጥ የምናወራለት የኢኮኖሚ እድገት እንክትክት ብሎ ነው የሚወድቀው፡፡ 
ለፓርቲው ስራ እና በትምህርት ወደ ውጭ አገራት ሲጓዙ ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ጋር ስለአገሪቱ ፖለቲካና ወቅታዊ ጉዳይ ይወያያሉ? 
በተለያየ አጋጣሚ ውጭ አገር ሄጄ የኢትዮጵያውያንን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማየት ለማታዘብ እድል አግኝቻለሁ፡፡
በደፈናው ውጭ አገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲህ ነው ብሎ ለመፈረጅ ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም ብዙ ዓይነት ነው፡፡ ዝም ብሎ ስራውን የሚሠራ አለ፡፡ ገባ ወጣ የሚል አለ፡፡ አገር ቤት ገብቶ ብዙ ስራ የሚሠራ አለ፡፡ ከኢትዮጵያ ከወጣ የሰላሳና የአርባ ዓመት የቆየ አለ፡፡ ከሶስት ዓመት በፊት ሄጄ ተመልሻለሁ፡፡ ከፓለቲካው የራቀ አለ፡፡ አይነቱ ብዙ ነው፡፡ በውጭ አገር የለው ተቃዋሚ ሃይል እየሰራው ያለው ፖለቲካ ግን በአብዛኘው ለአገር የሚጠቅም አይደለም፡፡ የነሱ ተፅዕኖ ባይኖር፣ እዚህ አገር ያለው ፖለቲካ የተሻለ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ የዳያስፖራ ፓለቲካ፣ የአገሪቱን ፓለቲካ ወደ ጽንፈኝነት የሚገፉ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሆነ አገሪቱን እየጠቀማት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲበላሽ፣ ወደ ፅንፍ የከረረ አቅጣጫ እንዲሄድ የማድረግ አዝማሚያ ነው የማየው፡፡ 
ግን ኢዴፓን ጨምሮ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅርንጫፍ ቢሮዎች በአሜሪካ በአውሮፓ አላችሁ፡፡ አይደለም? 
አዎ ኢዴፓ በውጭ አገራት ድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ አለን፡፡ ነገር ግን እዚያ ያለው መንፈስ እንከተላለን ማለት አይደለም፡፡ አገር ውስጥ ያለው ሁኔታና በዳይስፖራ ተቃውሞ የሚያስተጋባው ነገር በጣም የተራራቀ ነው፡፡ እነሱ የሚሉትን ከሰማሽ፤ እዚህ አገር አንድ ሰው በጠዋት ከቤቱ ወጥቶ ማታ በሰላም ይመለሳል ብለሽ አታስቢም፡፡ ሰው ስራ ሰርቶ እንጀራ በልቶ ይኖራል ብለሽ አታስቢም፡፡ ይሄ ሲባል ግን፣ ሁሉም አንድ ዓይነት አስተሳሰብ አላቸው ማለት አይደለም፡፡ እንዲያው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዳይስፖራ ከፖለቲካው ርቆ የሚኖር ነው፡፡ ‹‹ሳይለንት ማጆሪቲ›› እንደሚባለው ዓይነት ነው፡፡
በፖለቲካው በጣም ገንነው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ከአገር ከወጡ ብዙ ዓመት የሆናቸውና አንዳንዶቹ ሆን ብለው ኢትዮጵያ ውስጥ ጥሩ ነገር አይፈጠርም ተብሎ ማውራት ተገቢ ይመስላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ተተረማመሰች ብሎ መናገር ይጠቅመናል ብለው የሚያስቡ ሰዎችም አሉ፡፡ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችልና የሚገባው የዳይስፖራው ማህበረሰብ አሁን እያደረገ ያለው ነገር በጣም ጐጂ መሆኑን ተገንዝቦ ይሄን ነገር መለወጥ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ በእርግጥ እነዚህ ሰዎች በቀላሉ የሚለወጡ ናቸው ማለት ይከብዳል። ካልተለዋወጡ ግን ህዝቡ ስለነሱ ያለውን ግምት መለወጥ ይችላል፡፡ ‹‹ውጭ አገር ያለ ፖለቲከኞች የተማሩ፣ ገንዘብ ያላቸው፣ ዲሞክራሲ ባለበት አገር የሚኖሩ ናቸው ስለዚህ ከአገራችን ጥሩ ነው የሚያስቡት፤ እውቀት አላቸው›› ብሎ ማሰብ በራሱ ትክክል ነው ብዬ አላምንም፡፡ ምን ያህል ፖለቲካችንን እየጐዳው እንዳለ እንቅስቃሴያቸውን መገንዘብ አለበት፡፡ 
ዛሬ ዛሬ የፓርላማ ስብሰባዎችን ሲመለከቱ ምን ይሰማዎታል? አንድ የተቃዎሚ ፓርቲ ተመራጪ ብቻ ናቸው፤ በፓርላማ ውስጥ የሚታዩት..
እውነት ነው፡፡ ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በፊት አስራ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ተመራጮች ፓርላማ ውስጥ ነበሩ፡፡ በ1997 ዓ.ም. የተቃዋሚ ፓርቲ ተመራጮች ቁጥር ጨምሯል፡፡ ወደ ሰማኒያ ያህሉ ፓርላማ ገብተዋል፡፡ በ2002 ዓ.ም. ምርጫ ሁላችንም ተጠራርገን ወጣን፤ የአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ ብቻ ነው የቀረው፡፡ ይሄ የሚያሳየው የአገሪቱ የዲሞክራሲ ሂደት ከመሻሻል ይልቅ የኋሊት መመለሱን ነው ፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የተቃዋሚው ጐራ በሂደት እየተጠናከረ ከመምጣት ይልቅ እየተዳከመ መምጣቱን ነው የሚያሳየው፡፡ በዋናነት በ1997 ምርጫ ከተሠራው አጠቃላይ ስህተት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በአንድ በኩል ገዢው ፓርቲ ምህረት የለሽ ሆኖ በሃይል የማፈን ጥረት አደረገ፡፡
በሌላ በኩል አብዛኛው የተቃዋሚ ጐራ፣ ህዝብ የሰጠውንና እጁ ውስጥ የገባውን የምርጫ ውጤት ይዞ በአግባቡ እየተጠቀመ መቀጠል ሲገባው፣ ፓርላማ አልገባም ብሎ ህብረተሰቡን በምርጫ ሂደት ተስፋ እንዲቆርጥ አድርጎታል፡፡ ያኔ በቅንጅት ፓርቲዎች መካከል ቅራኔ ሲፈጠር፤ የአዲስ አበባ አስተዳደርን እንረከብ፤ ‹‹ፓርላማ አንገባም›› በሚለው ውሳኔ የኢትዮጵያን የዲሞክራሲ ሂደት የኋሊት ለአስራ አምስት ዓመት የሚመልስ ስህተት መሆኑን ገልጸን ነበር፡፡ በዚያ ስህተት ሳቢያ ነው ዛሬ ዋጋ እየከፈልን ያለነው፡፡ ያኔ በአግባቡ ያገኘነውን የፓርላማ ወንበር ተረክበን፤ የአዲስ አበባ አስተዳደርንም ተረክበን በመስራት ህዝቡን ከነስሜቱ ይዘን ብንቀጥል፤ ኖሮ እስከአሁን መንግስት የመሆን እድል ይኖረን ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ ያኔ የኛን ሃሳብ መስማት ያልፈለጉ ጎራዎች፤‹‹ መንግስትን በሁለት እና በሶስት ወር እንጥለዋለን፤ ዕድሜ የለውም›› ብለው ነበር የሚናገሩት፡፡ ኢህአዴግ አልቆለታል፤ ነበር የሚሉት። ታሪካዊ ስህተት ነው የተፈፀመው፡፡ አሁንም ቢሆን፣ ተቃዋሚው ጎራ በነገሩ የፅንፍ ፓለቲካ የሚንዙ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ሌላ 15 ዓመት ወደኋላ ይሄዳል፡፡ ኢህአዴግ ወደፊት ለሃያና ለሰላሳ ዓመት በስልጣን ላይ የመቆየት እድል ያገኛል ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ፣ ይሄንን አለን፡፡ አሁን እየታየ ያለው አሳዛኝ የፓለቲካ ሁኔታ ለእኛ አዲስ አይደለም፤ ያኔ የተሠራው ስህተት ውጤት ነው፤ የዘራነውን እያጨድን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እያደገ መሄድ ሲገባው ወደኋላ እየሄደ ነው፡፡ ይሄ ለገዥው ፓርቲ ሆነ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ትልቅ ሽንፈት ነው፡፡ የአገር ሽንፈት ነው፡፡ በዚህ ማንም መደሰት ያለበት አይመስለኝም፡፡ 
ከዚህ በኋላ ተቃዋሚዎች በቀጣዩ ምርጫ ራሳቸውን አጠናክረው መምጣት ይችላሉ?
ተቃዋሚው ጎራ ራሱን እንዲያሻሽልና እንዲጠናከር አስተዋጽኦ ማድረግ የሚገባቸው ሶስት አካላት አሉ፡፡ መንግስት፣ የዲሞክራሲ ሂደቱ የበለጠ እንዲፋፋ አፋዊ ሳይሆን ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ በአብዛኛው ስለ ዲሞክራሲያዊ ሂደት መንግስት እየተናገረ ያለው አፋዊ ነው በተግባር የሚገለፅ አይደለም፡፡ ወረቀት ላይ ይቀመጣል፡፡ በቲቪና በሬዲዮ ሲነገር እንሰማለን፡፡ በተግባር ግን የሚሠራው ከዛ የተለየ ነው፡፡
ሁለተኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ቆም ብለው ማሰብ አለብን፡፡ “የህዝብ ድጋፍ የለውም” የምንለውን ኢህአዴግን ለ22 ዓመታት ታግለን ለውጥ ያላመጣነው ለምን እንደሆነ ቆም ብለው በሃቅና በድፍረት ራሳችንን መመርመር ካልቻልነው፤ ከዛ ሂደት ተምረን መሠረታዊ የሆነ የአካሄድ ለውጥ እስካላደረግን ድረስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሊቀየር አይችልም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከመጠናከር ይልቅ በተቃራኒው እንደውም በሂደት እየተዳከምን የመጣነው ለምንድን ነው? እውን ይሄ የሆነው በኢህአዴግ ተጽዕኖ ብቻ ነው ወይ? የራሳችን የውስጥ ችግር፤ ድክመት፣ ስህተት የለብንም ወይ? ተቃዋሚ ፓርቲዎች እነዚህን ጥያቄዎች መርምረንና ራሳችንን ፈትሸን ራሱን ገምግሞ መሠረታዊ የመፍትሄ ሃሳብ ይዘን ካልመጣን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይሻሻላል ብዬ አላምንም፡፡ ኢዴፓ ይንንን ሃላፊነት ለመወጣት የድርሻውን እየሰራ ነው፡፡ በርካታ ተቃዋሚ ወገኖች ግን ራሳቸውን ለመፈተሽ ዝግጁ አይመስለኝም፡፡ በድፍረት መናገር የምችለው፣ ከኢዴፓ በስተቀር ‹‹እኔ ስህተት አለብኝ፤ እስከአሁን የመጣንበት ጉዞ ስህተት ነበረበት፡፡ ያ ስህተት ነው ደካማ ያደረገን›› ብሎ የገመገመ ሌላ ፓርቲ ያለ አይመስለኝም፡፡ አብዛኛው ተቃዋሚ ‹‹እኛ ስህተት የለብንም፤ ሁሌም ስህተት የሚፈጥረው ከገዢው ፓርቲና ከሌሎች ነው›› ብሎ ነው የሚያስበው፡፡ ራሱን ገምግሞ ተገቢ የመፍትሔ ሃሳብ የማያመነጭ ተቃዋሚ፣ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሂደት ላይ ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም፡፡ ለራሱም፣ ለሀገሩም አይሆንም፡፡ ሶስተኛው አስተዋፅዖ ከህዝብ ነው የሚጠበቀው። ምክንያቱም ህዝብ ነው የጉዳዩ ባለቤት፡፡ እኛ የፖለቲካ ፓርቲ ተሳታፊዎች ነን፡፡ የጉዳዩ ዋና ባለቤት ግን ህዝብ ነው፡፡ ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል፤ ለውጥ የሚመጣው ግን የዳር ተመልካች በመሆን አይደለም፡፡ ገዢው ፓርቲና፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው፡፡
ህብረተሰቡም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል፡፡ ተቃዋሚዎች ተጠናክረው እንዲወጡ የሚፈልግ የህብረተሰብ ክፍል አለ፡፡ ግን ፍላጎት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ህብረተሰቡ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ ስህተቶችን በአግባቡ ማወቅና እንዲታረሙ መታገል አለበት፡፡ ተቃዋሚ ስለሆኑ ብቻ በአዘኔታና በርህራሄ ‹‹ተቃዋሚዎች ናቸውና መተቸት የለባቸውም›› ማለት የለበትም፡፡ ፓርቲዎች ስህተት ሲሰሩ ካየ፣ ህብረተሰቡ መንግስትን ተቃዋሚዎችንም እየተቸ እንዲስተካከሉ ማገዝ አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከህዝብ የመነጨ ስለሆነ ህብረተሰቡ በገንዘብና በእውቀት ካልረዳቸው በስተቀር በሆነ ተአምር ተጠናክረው ሊወጡ አይችሉም፡፡ የህዝቡ መገለጫዎች ናቸው ስለዚህ ህብረተሰቡ ተቃዋሚዎች እንዲጠነክሩ የሚፈልግ ከሆነ፣ በተግባር አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት፡፡ የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ነው የአገራችንን ፖለቲካ ወደተሻለ ደረጃ ሊያደርስ የሚችለው፡፡ 
ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ ገዢው ፓርቲ ያወጣቸው አዳዲስ ህጐች አሉ፡፡ የፀረ ሽብር አዋጅ፣ የፕሬስ ህጉ፤ የፓርቲ ምስረታ አዋጅ፣ የኤንጂኦ ህግ ተቃዋሚዎችን ለማዳከም ገዢ ፓርቲ የፈጠረው ጫና ነው የሚል አስተያየት በስፋት ይደመጣል፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ? 
በአንድ በኩል፤ አዎ መንግስት እየፈፀመ ያለው ድርጊት፤ እያወጣቸው ያሉ ፖሊሲዎችና ህጎች፣ ለተቃዋሚ ጐራ መዳከም የራሳቸው አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ብቸኛ ምክንያቶች ናቸው ማለት ግን አይደለም። ራሱ የተቃዋሚ ጐራ ችግሮችም ለሱ መዳከም ምክንያት መሆኑን ቀደም ብዬ ጠቅሼዋለሁ፡፡ ገዢው ፓርቲ ውስጥ የምናያቸው፣ የጭፍን ስሜታዊነት፣ የሙስና፣ የዘረኝነት፣ የአምባገነንነት፣ ችግሮች፤ ሳይቀነሱ ሳይደመሩ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥም እናያቸዋለን፡፡ ገዥው ፓርቲ የሚጎድለው ዲሞክራሲያዊ ባህሪ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎችም ጎድሎ ይታያል፡፡
ስለዚህ መንግስት የሚፈጥረው ጫና ለተቃዋሚዎች መዳከም አንድ ምክንያት ነው እንጂ ብቸኛ ምክንያት አይደለም፡፡ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ እኮ ጠንካራ ነው የሚባለው፤ መንግስት የሚያደርግበትን ተጽዕኖ ተቋቁሞ ማሸነፍ ሲችል ነው፡፡ መንግስት ተጽእኖ የማያደርግ ከሆነማ ሁሉን ነገር የተመቻቸ ከሆነማ ትግልም አያስፈልግም። አገራችን እንደ አሜሪካ ሆናለች ማለት ነው። መንግስት ተፅዕኖ የማያደርግ ከሆነ፣ በጣም የምንመኘው ደረጃ ላይ በቀላሉ ደርሰናል ማለት ነው፡፡ ተዝናንተን በምዕራቡ ዓለም እንደምናየው በምርጫ እየተወዳደርን አሸናፊና ተሸናፊ ልንሆን እንችላለን ማለት ነው፡፡ ግን እዚያ ደረጃ ላይ ለመድረስ ቀርቶ ጨርሶ አልተጠጋንም፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ጫና የሚያደርግ መንግስት ነው ያለን፡፡ ይህን ለመለወጥም ነው የፖለቲካ ትግል እያካሄድን ያለ፡፡ ህዝቡን አስተባብረንና አታግለን፤ የመንግስት ጫና እንዲቆምና ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ እንችላለን፡፡ ይልቅስ ትልቅ እንቅፋት የሆነብን ውስጣዊ ችግር እንዳለብን መገንዘብ አለማቻላችን ነው፡፡ ውስጣዊ ድክመቶችን ለመፈተሸ አለማድረጋችን ነው ካንሠር ሆኖ የሚበላን፡፡ በ1997 ዓ.ም ምርጫ ተቃዋሚዎች ጥምረት እየፈጠሩ የህዝቡን ትኩረት በመሳብ በምርጫ ውጤት አምጥተዋል፡፡ የፓርቲዎችን ብርቱ ፉክክር የሚያካሂዱበት ነፃነት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ለ2007 ዓ.ም ምርጫ ግን ጥምረት የመፍጠር ህዝቡን የማንቀሳቀስና ብርቱ ፉክክር የማካሄድ ሁኔታ ጎልቶ አይታይም፡፡ ኢዴፓስ ለቀጣዩ ምርጫ ምን ያስባል? በቀጣዩ ምርጫ መሰረታዊ ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡ አንደኛ ነገር ገዢው ፓርቲ ከስህተቱ እየተማረ አይደለም፡፡ አሁንም በየቀኑ የሚነግረን፤ ዲሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ ሞልቶ እንደተትረፈረፈና ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ለማድረግ ምንም ችግር እንደሌላቸው ነው፡፡ ይህቺ አገር በልማት ብቻ ሳይሆን በዲሞክራሲም እያደረገች እንደሆነ ነው ኢህአዴግ የሚነግረን። ይሄ ቀልድ ነው፡፡ በተጨባጭ ያለው ሁኔታ ኢህአዴግ እንደሚለው አይደለም፡፡ የዲሞክራሲ ስርዓት በአግባቡ በዚች አገር እንዲያብብ እያደረገ አይደለም።
ገዢው ፓርቲ ላይ ቁርጠኝነት እየታየ አይደለም፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩልም አብዛኛው ውስጣዊ ድክመታቸውን ሳይፈትሹ ነባሩን አስተሳሰብና አቀራረብ እንደያዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ በ2007 ዓ.ም ምርጫ፣ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ መሠረታዊ ለውጥ ቢመጣ የሚችለው እነዚህ ሁለት ጐራዎች ከስህተታቸውና ከችግራቸው ተምረው የተግባር ማሻሻያዎችን ሲያደርጉ ነው። ይሄን ሲያደርጉ አይታይም፡፡ አሁን የቀረው አንድ ዓመት ነው፡፡ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ መንገዳቸውን ካላስተካከሉ፣ ምርጫው ከአለፉት ምርጫዎች የተሻለ ይሆናል ብዬ አላምንም፡፡ በሌላ በኩል አብሮና ተቀናጀን የመስራት ፍላጎት ቢኖር ኖሮ ያለ ጥርጥር የተሻለ ነገር መስራት ይቻል ነበር፡፡ ተቃዋሚው ጎራ እርስ በርስ ተቻችሎ እንዲሰራ የሚያደርግ ሃይል ቢኖር ጥሩ ነበር፡፡ 
አቶ ልደቱ በሚቀጥለው ሳምንት፣ ከአቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት ወዲህ ያለውን የኢህአዴግ፣ የመንግስትና የአገሪቱን ሁኔታ ይተነትናሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሦስት ዋና ዋና ፈተናዎች ምን እንደሆኑ በመዘርዘር የመፍትሔ ሃሳቦችን ያቀርባሉ። የአረቡን አለም አዝማሚያዎችንና የግብጽና የአባይ ጉዳዮችን እንዲሁም የኢትዮጵያውያን ስደትን በተለከተም አቶ ልደቱ ሃሳባቸውን ይገልፃሉ፡፡
          Addis Admas

No comments: