Saturday, July 18, 2015

ኦባማ የሚመጣው ለማን ነው?



ጌታቸው ሺፈራው
አሜሪካ ከኃይለስላሴ መንግስት ጋር የጠበቀ ግንኙነት የነበራት ቢሆንም ከአሁኑ አንጻር ሲታይ የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች አዲስ አበባ ድረስ መጥተው እንዲጠበቅላቸው የሚፈልጉት እንቅልፍ የሚነሳ ስጋት ነበራቸው ለማለት ግን ይከብዳል፡፡ ያም ሆኖ ግን በወቅቱ ለጥቁር ምቹ ባልነበረችው አሜሪካ ለጥቁር ህዝብ ነፃ መውጣት ስትባዝን የነበረችው ኢትዮጵያ መሪን ከዛሬዎቹ ገዥዎች በተሻለ በክብር አሜሪካን እንዲጎበኙ ጋብዛቸዋለች፡፡ ደርግ ወደ ስልጣን ሲመጣ የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች ኢትዮጵያን የሚጎበኙበት ምክንያት አልነበረም፡፡ የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች ኢትዮጵያን መጎብኘት የነበረባቸው ባለፉት 24 አመታት ነው፡፡ ራሳቸው በተቋሞቻቸው አግዘው ወደ ስልጣን ያመጡትን ህወሓት/ኢህአዴግ ስራ ያለችውን ኢትዮጵያ ቢጎበኙ ብዙም አይገርምም ነበር፡፡ ሆኖም እነ መለስን ‹‹አዲሶቹ›› እያሉ ሲያንቆለጻጽሱ የነበሩት እነ ክሊንተን እንኳ በህወሓት/ኢህአዴግ ስር ያለችውን ኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ሆነው መጎብኘት ያልፈለጉት የራሳቸውን ክብር ዝቅ ስለሚያደርግባቸው ነው፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግም እነሱ ባመኑት መልኩ እንኳ አላገኙትም፡፡ የሰብአዊ መብት፣ ዴሞክራሲና መሰል ቅድመ ሁኔታዎች ጭራሹን ሲሸረሸሩ ከኦባማ አንጻር ሲታይ በጡንቻ የሚያምነው ቡሽ እንኳ በርካታ የአፍሪካ መሪዎች የሚሰባሰቡበት አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ ከመምከር የሚፈልጓቸውን መሪዎች ሀገራቸው ድረስ እየሄዱ ማውራትን መርጠዋል፡፡ ሶማሊያ ውስጥ እንዲዘፈቅ የወከሉትን የህወሓት/ኢህአዴግን መሪዎች አሜሪካ ድረስ ጠርተው ከማነጋገር ባለፈ አዲስ አበባ ውስጥ እጃቸውን ሊጨብጧቸው አልፈለጉም፡፡ ይህም የሆነው የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅም ቢሆን አስጠርተው እንጅ የአምባገነኖቹ ቤተ መንግስት ድረስ መምጣት የሚጠይቋቸውን ተቋማት ለገነቡት፣ ሚዲያና ህዝባቸውን ለሚያዳምጡት አሜሪካኖች ክብር የሚቀንስ በመሆኑ ነው፡፡ ግን ደግሞ የግድ ለሀገራቸው ጥቅም አስፈላጊ ሲሆን አሜሪካኖች ሀፍረታቸውን ዋጥ አድርገው ከአምባገነን ጋር ይቆማሉ፡፡
ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ መሆኑ ከተገለፀበት ጊዜ ጀምሮ በዋነኛነት ሶስት አይነት አስተያየቶች እየተሰጡ ነው፡፡ አንደኛው የማህረሰብ ክፍል ኦባማ መጣ አልመጣ የሚመጣ ለውጥ የለም የሚል ነው፡፡ በቅርቡ ተደርጎ የነበረው የ‹‹3ኛው ፋይናንስ ለልማት ኮንፈረንስ›› ትራፊክ ያጨናነቀበት ሳይቀር ‹‹እሱ መጣ አልመጣ ምን ለውጥ ይመጣል!›› እያለ ትርፉ የትራፊክ መጨናነቅ ብቻ መሆኑን ታክሲ ውስጥም የሚሰጠውን አስተያየት ሳይቀር ታዝበናል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ኦባማ መምጣቱ ለኢህአዴግ እውቅና መስጠት መሆኑን በመግለጽ መምጣቱን የሚቃወም ነው፡፡ ሶስተኛው ደግሞ የኦባማ መምጣት ሀገሪቱ በእድገት ጎዳና መሆኗን የሚያሳይ ብስራት ነው የሚል ነው፡፡ የእኔ ከሶስቱም ይለያል፡፡ ኦባማ ለኢህአዴግ ሲል አልመጣም፣ ኦባማ ኢትዮጵያ በማደጓ ምክንያት አልመጣም፡፡ ኦባማ የሚመጣው በስርዓቱ አፈና ምክንያት ኢትዮጵያ ወደ አደጋ እያመራች በመሆኑ፣ በዚህም የአሜሪካ ጥቅም አደጋ ውስጥ ስለሚገባ ነው፡፡ ኦባማ በመምጣቱ ከተጠቀምንባቸው አወንታዊ፣ ካልተጠቀምንባቸው አሉታዊ ወይንም በዛው የሚረግጡ ጉዳዮች/ጥቅሞች ይኖራሉ፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ነች፡፡ ቻይና ከምዕራባውያን እየነጠቀቻት ያለች ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ በህዝብ ቁጥር ሁለተኛ ሀገር ነች፡፡ ኢትዮጵያ የሶማሊያ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳን፣ የኤርትራ፣ በደህንነት በኩል የደካማዋ ኬንያ ጎረቤት ናት፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ባራክ ኦባማ አይነት ጥቁር መሪ ሊኮራባት የምትገባ ታሪካዊም ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ለአሜሪካ በርካታ ምሁራንና የዳያስፖራ ቁጥር ያላት ሀገር ናት፡፡ ምናልባት በመካከለኛው ምስራቅ እስራኤልና ሳውዲ እንዳሉት ሁሉ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ከዛም አለፍ ሲል በአፍሪካ ለአሜሪካ ታሪካዊ የረዥም ጊዜ ወዳጅ ልትሆን የምትችል ሀገርም ናት፡፡ ታዲያ ባለፉት 24 አመታት የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች ለምን ወደ ኢትዮጵያ አልመጡም? ያልፈለጉት ስርዓቱን ነው ሀገሪቷን? ለእኔ ኢህአዴግ ተቃዋሚዎቹን የሚከስባቸው ኒዮሌብራል፣ አሸባሪ፣ የቀለም አብዮተኛ አይነት እነ አሜሪካን ከበስተጀርባ ያስቀመጡ ፍረጃዎች፣ እንዲሁም የአሜሪካ መንግስትና ተቋማት በስርዓቱ ላይ የሚያነሱት የሰብአዊ መብት ክስ በኢህአዴግና በአሜሪካ መካከል ያለውን ቅራኔ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች ከኢትዮጵያ ርቀው የቆዩት በኢህአዴግ ምክንያት ለመሆኑ ዋነኛው ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ስርዓቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ ይለወጣል ብለው ጠብቀውታል፡፡ ሀገሪቱ አደጋ ውስጥ ከመግባቷ በፊትም አስተማማኝና አማራጭ ኃይል ይመጣል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር፡፡
አሁን ግን ስርዓቱም መሻሻል አልቻለም፡፡ ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ የራሳቸውን ጥቅም የሚጎዳ አዝማሚያ እየታየ ነው፡፡ ኢህአዴግ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ሲል፣ ከ24 አመት በኋላ የትጥቅ ትግል እንደገና በአዲስ መልክ እንዲያውም ዋና መስሪያ ቤቱን አሜሪካ ባደረገ ድርጅት ሲጀመር ለአሜሪካኖች ትልቅ የማንቂያ ደወል ነው፡፡ በዚህ ሰዓት በኢህአዴግ አምባገነንነት ምክንያት ኢትዮጵያን ማጣት አይፈልጉም፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ እንደ ሶማሊያም እንደ ሱዳንም፣ እንደ ኬንያም ብቻ የምትታይ ሀገር አይደለችም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር ከተፈጠረ አፍሪካ የብጥብጥ ቀጠና እንደሚሆን፣ መካከለኛውን ምስራቅ ከአፍሪካዎቹ ነውጠኞች ጋር የሚያገናኝ የሽብር ቦይ እንደሚከፈት ያውቁታል፡፡
በአሁኑ ወቅት የመን እየተበጣበጠች ነው፡፡ ከየመን ጋር በሰፊ ባህር የምትገናኘውና የበርካታ ሀገራት ሰራዊት ቢላክም ያልተረጋጋችው ሶማሊያ ጋር ትገናኛለች፡፡ ከመካከለኛው ምስራቅም ጭምር የሚመነጨውን የሶማሊያን ችግር በዋነኝነት ትቋቋማለች የምትባለው ኢትዮጵያ ነች፡፡ የመንና ሶማሊያ በፈራረሱበት ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር ቢደርስ ይህ ችግር ሙሉ አፍሪካን ያዳርሳል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሶማሊያን ያለውን ችግር የሚመክት ሀገር ስለሌለ ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የሶማሊያን ስደተኞች የምትቀበል ሀገር ነች፡፡ በሌላ ጎኗ ደግሞ ደቡብ ሱዳን አለች፡፡ ደቡብ ሱዳን በአንድ በኩል ‹ሎርድ ሪዚስታንስ አርሚ› የሚፈነጭበት ሰሜን ዩጋንዳ፣ በሌላ በኩል ከምትበጣበጠው ኮንጎ በአንድ በኩል ደግሞ ከዳርፉር ጋር ደቡብ ሱዳን ሌላኛዋ የሁከት አገር ማዕከላዊ አፍሪካም ጎረቤት ነች፡፡ ደካማዋ ቻድ የማዕከላዊ አፍሪካም የሱዳንም አጎራባች ስትሆን ይህን መስመር ቦኮሃራም የሚንጣት ናይጀሪያና የሰሜን አፍሪካው የአልቃይዳ ክንፍ መነሃሪያ ለሆኑት ሊቢያና ኒጀር ጋር ትገናኛለች፡ የመንና ሶማሊያ እንዲሁም ደቡብ ሱዳን መካከል ኢትዮጵያ የምትባል ታኮ ከሌለች አልሸባብ እስከ ሊቢያ፣ ቦኮሃራምና የሰሜን አፍሪካ አልቃይዳ እስከ ኪስማዩ ከዛም አልፎ እስከ የመን የሚፈነጩበት መስመር ወለል ብሎ ይከፈታል፡፡ ኢትዮጵያ በአፈናው ምክንያት ችግር ውስጥ ከወደቀች፣ አሸባሪዎች ከየመን ሊቢያ የሚንሸራሸሩበት፣ አፍሪካን ዋና መረማመጃቸው የሚያደርጉበት ክፉ ምልክት እየታየ ነው፡፡ ወቅቱ ደግሞ ኦባማ በየአካባቢው በአሸባሪዎች ጥቅሟ የሚነካባት፣ የዓለም ፖሊስ የሆነችው አሜሪካ ፕሬዝደንት የሆነበት ነው፡፡
ወቅቱ የጣለበት ኃላፊነትና አጣብቂኝ እንዳለ ሆኖ ኦባማ ከሌሎች ፕሬዝደንቶች የሚለየው የቆዩቱ የሚኮፈሱበትን ጉዳይ ሰብሮ ግንኙነት በመጀመር ነው፡፡ ለዚህም ‹‹እኔ ከመወለዴ በፊት የነበረ ጦርነትን ውስጥ ገብቼ መነታረክ አልፈልግም›› ብሎ ግንኙነት የጀመረባት፣ ከ55 አመት በኋላ ኤምባሲ የከፈተባት ኩባ ትልቅ ምሳሌ ነች፡፡ በዚህ ወቅት ግን የኩባን መሪዎች መክሮና ዘክሮ ኩባን ከማራቅ ይልቅ ወደ አሜሪካ እንድትቀርብ የራሱን ጥረት አድርጓል፡፡ ‹‹ብዙ ጊዜ ራሳችንን ከማሳመን ባለፈ ጉዳይ ውስጥ ስናስገባ የሚብሰን መዘዙ ነው›› ነበር ያለው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ሌላ መዘዝ በሚያመጣ ጉዳይ ለስርዓቱ መፍትሄ ከመስጠት ከሰሙ እኔ እግረ መንገዴን ሄጀ ላነጋግራቸው የሚል አቋም እንዲይዝ ተገድዷል፡፡ ግብፅ ውስጥ እንዲያውም ሌሎቹ ‹‹አክራሪ›› የሚሏቸው ባዘጋጁት መድረክ መጥቶ ታሪካዊ ንግግር ሲያደርግ ማስጠንቀቂያም የግንኙነት አረንጓዴ መስመርም እያሳየ ነበር፡፡ ውየስት ባንክን ሲጎበኝ ለአሜሪካ በጎሪጥ ለማትታየው እስራኤልም ለሙስሊሙ ዓለምም መልዕክትም፣ ማስጠንቀቂያም አስተላልፏል፡፡ ከኢራን ጋር ቁጭ ብሎ ተደራድሯል፡፡ እነዚህ አብዛኛዎቹ ሌሎች ያልደፈሯቸው ከገባቸው ግንኙነታቸውን የሚያድሱበት፣ ካልገባቸው ማስጠንቀቂያ የሰጠባቸው ናቸው፡፡ ኢህአዴግም የሚሰጠው የመጨረሻ እድል ወይንም ማስጠንቀቂያ ነው፡፡
ኦባማ ካለፉት የአሜሪካ ፕሬዝደንቶችም፣ በዓለም በወቅቱ ካሉት ፕሬዝደንቶችም በላይ በርካታ ሀገራትን የጎበኘ ፕሬዝደንት እንደሆነ ይነገራል፡፡ የአሜሪካ መከላከያ ሰራዊት ያለባቸው ኢራቅና አፍጋኒስታን ከሁለት ጊዜ በላይ ተመላልሷል፡፡ ወደ እነዚህ አገራት ሲሄድ በሌላ ስብሰባ ምክንያት ሳይሆን በቀጥታ ነው፡፡ በእርግጠኝነት ኢትዮጵያ ሶማሊያ ውስጥ አሜሪካን ወክላ ባትገኝና የአሜሪካ ሰራዊት ሶማሊያ ውስጥ ቢሆን ኖሮ ኦባማ ከአንዴም ሁለቴ ወደ ሞቃዲሾ ማቅናቱ የማይቀር ነበር፡፡ አሁን ባለው አዎንታዊ ሁኔታ ግን ሶማሊያ ብቻ ሳትሆን ኢትዮጵያም በህወሓት/ኢህአዴግ አፋኝነት ምክንያት የባሰ ችግር ውስጥ እየገባች በመሆኑ የኦባማ አስተዳደር ገንዘብ ደጉሟቸው ሪፖርት የሚያወጡት ተቋማት በየጊዜው እያወጡት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለመውደቅ ስጋት ላይ ያለች ሀገር ነች፡፡
በመሆኑም ይች አፍሪካ የቀጠና ዞን እንዳይሆን ታኮ የሆነችው ሀገርን ሳትፈርስ ደርሰው፣ አሜሪካ ውስጥ ጠርተው፣ መልዕክተኛ ልከው ያስመከሯቸውን የህወሓት/ኢህአዴግ መሪዎች ኢትዮጵያ ድረስ መጥተው ቢገባቸው መምከር ነበረባቸው፡፡ ይህን ሲያደርጉም በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትን አልፈለጉም፡፡ የሚያዙት አምባገነን ስርዓት ጋር ለመጨባበጥ ምክንያት አስፈልጓቸዋል፡፡ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ! ያውም ኬንያ ውስጥ ለሌላ ስብሰባ ከመጡ በኋላ እግረ መንገዳቸውን፡፡ ኦባማ በቀጥታ ኢትዮጵያን ቢጎበኝ እንኳ የሚገርም አይደለም፡፡ ኦባማ ጆርዳን፣ ትሪንዳድና ቴቬጎ፣ ጃማይካ፣ ኮስታሪካ፣ ታንዛኒያን እና ሴኔጋልን የመሳሰሉ ትንንሽና ለሀገሪቱ ጥቅም ከኢትዮጵያ አንጻር ይህን ያህል ጥቅም አላቸው የማይባሉ ሀገራትን ጎብኝቷል፡፡ ከእነዚህ መካከል ከአሜሪካ ጎን የምትገኘውን ጃማይካን ጨምሮ አብዛኛዎቹን ሀገራት ሲጎበኝ ስልጣን ላይ ያለ የመጀመሪያው ፕሬዝደንት ነው፡፡ ባለፉት አመታት ኢህአዴግ ጋር እጅ መጨባበጥ አሳፋሪ ሆኖ ሌሎች ባለመምጣታቸው፣ አሁን ግን የማይታለፍ ሁኔታ ላይ በመደረሱ ኦባማ ኢትዮጵያን የጎበኘ የመጀመሪያው ፕሬዝደንት ሆነ፡፡ ‹‹በእድገቱ ምክንያት ነው›› የሚባለው ግን ውሃ የማይቋጥር ምክንያት ነው፡፡ አብዛኛዎቹን ትንንሽና የኢትዮጵያን ያህል በርካታ መሪዎችን በአንድ ጊዜ የማይገኙባቸው፣ የኢትዮጵያን ያህል ጥቅማቸውን የማያስጠብቁ ሀገራትን የጎበኘው በመጀመሪያው የስልጣን ዘመኑ ሆኖ ኢትዮጵያን ከሁለተኛ ዙር ስልጣኑ በኋላ (ያውም ሊያልቅ ሲል በጥድፊያ) ለመጨረሻ ጊዜ መጎብኘቱ አሜሪካኖች ይችን ማጣት የማይፈልጓትን ሀገር ለመጎብኘት የከለከሏቸው በርካታ ምክንያቶች እንደነበሩ በጉልህ የሚያሳይ ነው፡፡
ኦባማ ለኢኮኖሚ፣ ለፖለቲካዊና ለደህንነት ጉዳይ ሲባል ኢህአዴግ የሚገዛትን ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግን የምታግዘውን፣ ከምዕራባውያን እንዲያፈነግጥ አይዞህ የምትለውን ቻይናንም ጎብኝቷል፡፡ በአምባገነንነት ከሆነ ሳውዲ የሚባል ጋዜጠኛና ሌሎች ጥያቄ የሚያነሱትን በጅራፍ የሚገርፍ፣ አሰቃቂ ግድያ የሚፈፅም ሀገርንም በተደጋጋሚና በቀጥታ ጎብኝቷል፡፡
በርማ ወይንማ ማይናማር በዓለም የሰብአዊ መብት በመጣስ ከሚታወቁት አስር አገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ በወታደራዊ አገዛዝ ስር የሆነችው በርማ ኢህአዴግ ውስጥ ካለችው ኢትዮጵያ ቢበዛ እንጅ የማያንስ በደል የሚፈፀምባት ሀገር ናት፡፡ በርማ ድረስ ሄዶ ከገዥዎቹ ጋር መጨባበጥም ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቶ ከኢህአዴግ መሪዎች ጋር የመጨበጥን ያህል ለአሜሪካውያን የሚያሳፍር፣ የሚያስተች ነው፡፡ የበርማ መንግስት ከዜጎች መሬት በመንጠቅ ለውጭ ባለሀብቶች ይሰጣል፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የመከላከያ ሹሞችና ሌሎችም ባለጊዜዎች ነዋሪዎችን ከቤትና ቀያቸው በማፈናቀል የራሳቸውን ንብረት የሚያካብቱባት ሀገር መሆኗንም ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሪፖርቶች ያመላክታሉ፡፡ ስርዓቱን የሚተቹ በገፍ የሚታሰሩበት አገርም ነው፡፡ ዘመናዊ ባርነትም በስፋት የሚታይበት ሀገር ነው፡፡ ህፃናትን ለቁፋሮ ብቻ ሳይሆን ለመከላከያም ይለምላል፡፡ ከ70 ሺህ በላይ የሰራዊቱ አባላት ከ15 አመት ጀምሮ እስከ 18 አመት እድሜ ያላቸው ናቸው፡፡ በየእስር ቤቱ እስረኞች በአሰቃቂ ሁኔታ የሚገረፉበት ሀገርም ነው በርማ፡፡ የዘር ማፅዳት በተለይም ሙስሊሞች በአደባባይ የሚታረዱበት ሀገር ነው በርማ፡፡ መከላከያው እንደ ፈቀደ ሰው የሚገድልበት ሀገር ነው በርማ፡፡ ይህን ሀገር ግን ኦባማ ለሁለት ጊዜ ያህል ጎብኝቷል፡፡
ምንም እንኳ የበርማ ወታደራዊ አገዛዝ በሙስናም በምንም ብሎ የውጭ ባለሀብቶችን እየጠራ ሰፋፊ መሬትን በመስጠት፣ ግድቦችን በመስራት ልማት እያፋጠንኩ ነው ቢልም ኦባማ ግን ሁለት ጊዜም መሪዎቹን ያገኘው ለመምከርና ለመውቀስ ነው፡፡ ሳን ሱ ኪ የተባለችውን የተቃዋሚ መሪ ጨምሮ በርካቶችን በማሰቃየት ሀገሪቱን ወደ ብጥብጥ ሊያመራት ነው ብለው ስለፈሩ እዛው ቦታው ድረስ ሄደው ምክር ለግሰዋል፡፡ ይህ የሆነው ከእጃችን ትወጣለች ወዳሏት ኢትዮጵያ ከመውጣቱ ከሶስት አመት በፊት ነው፡፡
የአሜሪካ መንግስት ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣበት ዋነኛ ምክንያት የደህንነት እንደሆነ ገልጾአል፡፡ ከዚህም ባሻገር ኢህአዴግ ያለ መረጃ ያሰራቸውን ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያንና ተማሪዎች በአጋጣሚ መፍታቱ ኦባማ የኢኮኖሚ እድገቱ አማልሎት ሳይሆን ኢህአዴግ እየሄደበት ያለው መንገድ የተሳሳተ በመሆኑ የፖለቲካ ማሻሻያዎች እንዲያደርግ ለመገሰፅ እንደሚመጣ ምስክር ሆኗል፡፡ ኦባማ የሚያዘውንና ይፈርሳል ብሎ የሚፈራውን ሀገር ብቻ ሳይሆን አሜሪካም ለውጦችን እንድታደርግ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ አውሮፓ ውስጥና በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ሚስጥራዊ እስር ቤቶችን እንዲዘጉ አድርጓል፡፡ የቀደሙት መሪዎች የማይደፍሩት የጓንታናሞ ጉዳይ የተደፈረው በኦባማ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ በምትባለው አሜሪካ ለብሄራዊ ጥቅሟ ስትል በሌሎች ላይ የምታደርገውን እንድትቀንስ እየሰሩ ያለው ኦባማ ታዛዥ መንግስታት ለስልጣን ሲሉ በህዝባቸው ላይ የሚፈፅሙትን እንዲቀንሱ እየወተወተ ነው፡፡ የሀገራቱ የፖለቲካ ቡድኖችና ሌሎችም የለውጥ አካላት የበኩላቸውን ሲያደርጉ ለአሜሪካ ምቹ ይሆናል፡፡ በእርግጠኝነት ለኢትዮጵያውያን ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ የኦባማ መምጣት ሲሰማ ጥቂቶችን የፈታው ኢህአዴግ ሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ አሁን ካለው የተሻለ እንቅስቃሴ ቢኖር ይበልጡን ተገዶ ሌሎች ማሻሻያዎችን የማያደርግበት ምክንያት የለም፡፡
ያም ሆነ ይህ ኦባማ ላክ ሲባል ጦር የሚልከውን ኢህአዴግን ብሎ ቢመጣ ኖሮ ከ9 አመት በፊትም በመጣ ነበር፡፡ ጋና፣ ሴኔጋል፣ ኤልሳቫዶር፣ ጃማይካ ከመሄዱ በፊት ደግሞ ደጋግሞ ኢትዮጵያ በጎበኘ ነበር፡፡ የቀድሞዎቹ ፕሬዝደንቶችም በመጡ ነበር፡፡ እንዲያውም በዚህ በፈራረሰ ቀጠና መሪዎችን ሰብሰብ ብለው ወደ ሚያገኙባት ኢትዮጵያ ሌሎች ፕሬዝደንቶችም ያልመጡት ኢህአዴግ መልዕክት ተልኮበት፣ አሊያምና ቶሎ ተብሎ ከመምከር የበለጠ ክብር የማይሰጠው ሆኖ ስላገኙት ነው፡፡ በዚህም ከኢህአዴግ ጋር መቆም ስላፈሩ ብቻ ከሚፈልጓት ኢትዮጵያ ርቀዋል፡፡ አሁን ደግሞ የሚያልፈው ኢህአዴግ የማያልፍ ዕዳ እንደሚያመጣ፣ መራቁም መፍትሄ እንደማይሆን ተገንዝበዋል፡፡ ለመምከርና ለማስጠንቀቅም ወስነዋል፡፡
የአካባቢው ሁኔታ፣ የኢህአዴግ የቀልድ ምርጫ በመልዕክተኛም የሚያልቅ አልሆነም፡፡ ጭራሹን ኢትዮጵያ አደጋ ላይ መሆኗን የሚያመላክት እንጂ! በመሆኑም ሚዲያዎቻቸው፣ ተቋሞቻቸው እየተቿቸውም ቢሆን ኢትዮጵያ አደጋ ውስጥ ወድቃ ጥቅማቸው እንዳይነካ ስርዓቱን መክረው መሄድ አለባቸው፡፡ ለአሜሪካ ሲባል ኢትዮጵያን ከውድቀት መታደግ አለባቸው፡፡ ስርዓቱ ከሰማ! ተቃዋሚዎችም ይህን አጋጣሚ ከተጠቀሙበት! ተቃዋሚዎች ካልተጠቀሙበት ደግሞ ስርዓቱ ተመክሮ ሰማም አልሰማም የኦባማ መምጣት እውቅና ይሆንለታል፡፡ ጥቅሙም ጉዳቱም ማን በምን መልኩ ይጠቀምበታል በሚለው ይወስነዋል፡፡

No comments: