በ2004 የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ‹‹መጅሊስ ይቀየር›› ጥያቄ መቀስቀሱን ተከትሎ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ዩንቨርስቲዎች በአንዱ ውስጥ በጉዳዩ ዙሪያ ለመወያየት ስብሰባ ተጠራ፡፡ ስብሰባው ላይ የዩንቨርስቲው የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚደንት የነበረው የእስልምና እምነት ተከታይ እጁን አውጥቶ ‹‹ትላንትና ምንም ነገር እንዳልናገር ከዩንቨርስቲው አስተዳደር ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኝ ነበር፥ ሆኖም…›› ብሎ ሐሳቡን ተናገረ፤ ያ የዩንቨርስቲ የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚደንት በማግስቱ ከኃላፊነቱ ተነሳ፡፡
ይህ በኢሕአዴግ ዘመን ያለውን ግለሰባዊም ሆነ ቡድናዊ መብት ደረጃ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ምሳሌ ሲሆን በዚሁ ተንደርድረን፣ በ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት ጉልህ ሚና የተጫወቱትን ተመሳሳይ አካላት እንመለከታለን፤ ለመሆኑ እነዚህ ሕዝባዊ አካላት እነማን ነበሩ?
የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት የኋላ ኋላ ገጠሬው ቢቀላቀለውም፣ በአብዛኛው የተመራው በከተማ ነዋሪዎች ነው ማለት ይቻላል፡፡ አንዳርጋቸው ጥሩነህ Ethiopian Revolution 1974-1987፡ A transformation from an aristocratic to a totalitarian autocracy (1993) በተሰኘው ጥናታቸው ላይ በአብዮቱ ዋና ተዋናይ የነበሩትን አካላት ከነ[ተቀራራቢ] ቁጥራቸው ዘርዝረዋቸዋል፡፡
“የኢትዮጵያ ንግድ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን 80,000 አባላት፤ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር (አባላቱ የመንግሥት ሠራተኞች ነበሩ፤) ብዛታቸውም 18,000 ነበር፡፡ ከመንግሥት ሠራተኞቹ በተጨማሪ 10,000 የምድር ጦር እና 30,000 የፖሊስ አባላትን ጨምሮ 55,000 የሠራዊት አባላትን የሠራተኛ ማኅበሩ ያካትታል፡፡
በወቅቱ የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር 70,000 ነበር፤ ከነርሱ ውስጥ 6,000ዎቹ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ናቸው፤ (በተጨማሪም በውጭ ሃገራት የዩንቨርስቲ ጥናት ላይ የነበሩ ሌሎች 2,000 ተማሪዎች ነበሩ)፡፡
“ስለዚህ ከጠቅላላው 3 ሚሊዮን የከተማና ከተማ ቀመስ ቦታዎች ነዋሪ ሕዝብ ውስጥ ፖለቲካዊ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ የነበሩት የመንግሥት ሠራተኞች፣ ወታደሮች እና ተማሪዎች ከ300,000 የማይበልጡ የከተማ ነዋሪዎች ነበሩ፡፡”
በየማኅበራቱ የታቀፉት እና ፖለቲካዊ ንቁ የነበሩት ሕዝቦች ቁጥር ከጠቅላላው የከተማ ሕዝብ አንጻር እንኳን ሲታይ ከ10
በመቶ የማይበልጡ እና በወቅቱ ከነበረው ጠቅላላ የሕዝብ ብዛት አንጻር ከ1 በመቶ የማይበልጡ ቢሆንም አብዮቱን ማስነሳት ችለዋል፡፡ አብዮቱ ከተማ እና ኮርፖሬታዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ሳይወሰን አገር አቀፍ እንዲሆን በማድረግና ስር ሰድዶ የነበረውን ንጉሣዊውን ስርዓት በማንገጫገጭ ለማስወገድም ችሏል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው በተለያዩ ማኅበራት ጥንካሬ ነው እንጂ በተሳታፊዎቹ ቁጥር ብዛት አይደለም ብዬ አምናለሁ፡፡ በዝርዝር እንመልከተው፡-
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ)
ኢሠማኮ የተለያዩ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ለጥቅማቸው ለመቆም ያቋቋሟቸው ማኅበራት አቃፊ ኮንፌዴሬሽን ነበር፡፡
ኢሠማኮ በ1965፣ 167 የሠራተኞች ማኅበራትን ያቀፈ ሲሆን ከ80,000 በላይ አባላት ነበሩት፡፡ ኮንፌዴሬሽኑ በ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት ወቅት ውስጥ የነበረው ሚና ከየትኛውም አካል የጎላ ነበር፡፡ ኮንፌዴሬሽኑ በመጀመሪያ የሠራተኞቹን ጥቅም ያስጠብቃሉ ያላቸውን (የደሞዝ ጭማሪ፣ የሠራተኞች የመደራጀት መብቶች) እና ሌሎችም (5 ያክል) ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ይዘት ያላቸውን - ብዙ ምንጮች እንደሚሉት 16 (አንዳርጋቸው ጥሩነህ 17 ነው ይላሉ) ጥያቄዎች አነሳ፡፡ መንግሥት ይህንን ጥያቄያቸውን ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ ጠቅላላ አድማ ለጥር 30/1965 እንደሚጠራም አስጠነቀቀ፡፡ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልካቸው መኮንን ከአድማው ቀነ ቀጠሮ አንድ ቀን ቀድመው ጥያቄዎቹ ከሦስት እስከ ስድስት ወር በሚደርስ ጊዜ መልስ እንደሚያገኙ ብቻ ተናገሩ፡፡ በማግስቱ (የካቲት 1/1965 /ማርች 8/) ግን እስከ መቶ ሺሕ የሚጠጉ ሰዎች የሥራ ገበታቸው ላይ ባለመገኘት የሥራ ማቆም አድማ አደረጉ፡፡ የታሪክ ጸሐፊዎች በዕለቱ ፀጥ-ረጭ የማለቱን ገጠመኝ የሚያስታውሱት በተለይ አዲስ አበባ ‹‹ሽባ ሆነች /በእንብርክኳ ሄደች/›› በማለት ነው፡፡
በወቅቱ ኮንፌዴሬሽኑ የገጠመው ችግር አብዛኛዎቹ ሠራተኞች በአድማው ከሦስት ቀን በላይ መሳተፍ አለመቻላቸው ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት አብዛኛዎቹ ሠራተኞች ኑሯቸው ከእጅ ወደአፍ ስለሆነና ሥራችንን አጥተነው እንቀራለን የሚል ፍራቻ ስለነበረባቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ለጥያቄዎቻቸው በሙሉ መልስ የሚሰጥ ስምምነት የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልካቸው እንዲፈርሙ ማስገደድ አላቃታቸውም፡፡ እንዲያም ሆኖ የአድማው ትልቅ ግብ ተደርጎ እስከዛሬም የሚቆጠረው እንቅስቃሴው ሌሎች በርካታ አድማዎችን እና መንግሥትን ለለውጥ የሚያስገድዱ እበያዎችን ማበረታቱ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር (ኢመማ)
ኢመማ ከ60 ዓመት በላይ ያስቆጠረ አንጋፋ ማኅበር ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንደንጉሡ ዘመን ማብቂያ ሰሞን አቅመ-ትልቅ ማኅበር ሆኖ አያውቅም፡፡ በ1965፣ 18,000 ያህል አባላት ነበሩት፡፡ ማኅበሩ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ቢያንስ ለስድስት ዓመታት ያክል በደሞዝ ጭማሪ እና የደሞዝ ስኬል ጉዳይ ሲነታረክ ከርሟል፡፡ አንዳርጋቸው ጥሩነህ እንደጻፉት የመምህራን ማኅበሩ የካቲት 11/1966 ታክሲዎች የነዳጅ ጭማሪን ተከትሎ በጠሩት አድማ ላይ ተደምሮ የትምህርቱን ሥርዓት በዝምታ ሊያውለው ወሰነ፡፡ ማኅበሩ ጥያቄዎቹን ከመምህራን (የደሞዝ እና የሴክተሩ ክለሳም) በላይ እንዲሆን፤ የሰላማዊ ሰልፍ መብት እንዲከበር፣ የደሞዝ ወለል እንዲበጅ፣ ለፋብሪካ ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ እንዲደረግ፣ ለኢንዱስትሪ ሠራተኞች የጡረታ መብት እንዲከበር፣ ሠራተኞን የማባረሪያው ሕግ እንዲስተካከል እና ሌሎችንም ጥያቄዎችን አነገበ፡፡
የመምህራን ማኅበሩ የደሞዝ ስኬት ይሻሻል ጥያቄውን ከአብዮቱ 6 ዓመት ቀድሞ ያነሳ ቢሆንም መልስ ማግኘት ባለመቻሉ ትግሉን አጠናክሮ፣ የመምህራንን ብቻ ሳይሆን የሌሎችም ሠራተኞች መብቶችን የሚያስከብሩ እና ሌሎችም ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን አንግቦ ተጠናክሮ በመንቀሳቀስ የሌሎቹን ማኅበራት ዓይን ለመግለጥ መቻሉ እንደስኬት ይቆጠርለታል፡፡
የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ማኅበር (USUAA)
የኢትዮጵያ ዩንቨርስቲዎች ማኅበር (ከቀኃሥ - ዩንቨርስቲ በተጨማሪ የሌሎች ሁለት ራስ ገዝ አካባቢዎች ዩንቨርስቲዎችን የሚጨምር ሲሆን) የነበረው አቅም ግን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማኅበር ያነሰ ነበር፡፡ ሆኖም የተማሪዎች ሚና ጉልህ ነው በሚል እስከዛሬም ‹‹የተማሪዎች እንቅስቃሴ›› ውጤት ሆኖ የሚታወሰው የ1966ቱ አብዮት በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ማኅበር (ESUNA) እና የኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ማኅበር በአውሮፓ (ESUE) የታገዘ ነበር፡፡
የዩንቨርስቲ ተማሪዎች እንቅስቃሴ እስካሁንም ድረስ በተቃዋሚ እና ገዢው ወገን ያሉትን አንጋፋ ፖለቲከኞች ያነሳሳ እና ለአብዮቱ ምልከታዎችን ለግሶታል፡፡ አንጋፋዎቹ የ‹‹መሬት ላራሹ›› እና የብሔሮች እኩልነት ጥያቄ ቦታ የተሰጣቸው ያኔ - በተማሪዎቹ አማካይነት ነው፡፡ USUAA (በ1966 መባቻ ላይ የታገደባቸውን) ‘ስትራግል’ የተሰኘ ጋዜጣ በማሳተም የብሔሮች መብት እስከመገንጠል ድረስ የመዝለቅ ጥያቁዎችን ሳይቀር አንስቷል፡፡ መኢሶን፣ ኢሕአፓንና ሕወሓትን የመሰሉ ለተከታዮቹ ረዘም ላሉ ዓመታት ተጽዕኖ ፈጣሪ ፓርቲዎችም የተፈጠሩትም ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ነው፡፡
በተማሪዎቹ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ጉልህ ሚና ኖሮት ነገር ግን ብዙም ያልተወራለት ‹‹Crocodiles Society›› (የአዞዎቹ ማኅበረሰብ) የሚባለው ነው፡፡ ይህ ቡድን የዩንቨርስቲውን እንቅስቃሴ ያጋግሉ የነበሩትን ‹‹ዜና እና አስተያየቶች›› የታተሙበትን በራሪ ወረቀቶች የማዘጋጀት/የማሰራጨት ሚና የነበረው ሲሆን ‹‹መሬት ላራሹ›› የሚለው አጀንዳም የፈለቀው ከዚያ እንደሆነ የባሕሩ ዘውዴ Documenting the Ethiopian Student Movement: An Exercise in Oral History ይጠቃቅሳል፡፡
የተማሪዎች ኅብረት ለአብዮቱ መፋፋም የሐሳብ መዋጮ፣ እና የፓርቲ መመስረት የመጨረሻው ውጤት ቢሆንም የትምህርት ክፍለጊዜዎችን ክፍል ባለመግባት እና የተቃውሞ ሰልፍ በማስነሳትም ጭምር የወቅቱ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ ተግተው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የተማሪዎቹ እንቅስቃሴም ፈተና ነበረበት፡፡ የወቅቱ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚደንት ጥላሁን ግዛው ባልታወቁ ሰዎች (በዝግታ በምትነዳ መኪና ውስጥ በተተኮሰ ጥይት) ተገድሏል፡፡ ጆን ያንግ Peasants Revolution of Ethiopia በተባለ መጽሐፋቸው ጥላሁን ‹‹ከገንጣዮች እንቅስቃሴ ጋር ትተባበራለህ›› በሚል ዩንቨርስቲውን ለቅቆ እንዲወጣ ማስጠንቀቂያ እንደደረሰው ገልጾ ነበር ሲሉ ጽፈዋል፡፡
ከነዚህ በተጨማሪም የ5 ሣንቲም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ የተጠራው የታክሲ ማቆም አድማም ለአብዮቱ መጧጧፍ እና ለንጉሡ ስርዐት የኢኮኖሚ ፈተና ለመሆን በቅቷል፡፡
ትላንት ይማረኝ?
ደርግ ሁሉንም ማኅበራት በራሱ መልክ ለማዋቀር ሞክሮ ነበር፡፡ የነጋዴዎች፣ የከተሜዎች፣ የገበሬዎች… እየተባለ ማኅበር በማኅበር አገሪቱን አጥለቀለቃት፡፡ አንዳርጋቸው ከላይ በጠቀስነው ጥናታዊ ጽሑፋቸው “ከሞላጎደል ሁሉም ዜጋ አንዱ፣ ወይም ሌላኛው ወይም ከአንድ በላይ የሆነ ማኅበር/ራት ውስጥ መታቀፉ የማይቀር ነበር፡፡ ዕድሜዋ ከ18 እስከ 30 የሚደርሳት ሴት ለምሳሌ የገበሬች ወይም የከተሜዎች ማኅበር (እንደምትኖርበት ቦታ ሁኔታ) እና የወጣት አብዮተኞች ማኅበር አባል ትሆናለች፡፡ እንዲሁም፣ የነጋዴዎች፣ የነርሶች፣ የዶክተሮች ብሎም የፓርቲ አባልም ልትሆን ትችላለች፤” በማለት የደርግን ዘመን ማኅበር የረከሰበት ቢሆንም ሁሉም የመንግሥታዊ ስርዐቱን ከማስፈፀም በላይ ፋይዳ እንዳልነበራቸው አመላክተዋል፡፡
በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ደግሞ የተለየ አጨዋወት እናገኛለን፡፡ ኢሕአዴግ በጥቅሉ በመደራጀት (communalism) ያምናል፤ ሆኖም እያንዳንዱን ማኅበር የመቆጣጠር ኃላፊነቱን ግን ካድሬዎቹ እንዲወስዱት ይፈልጋል - እስካሁን ባለው ሁኔታ ተሳክቶለታልም፡፡
የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ማኅበር በ1993 የገጠመው የነጻነት ማጣት ችግር እና የዩንቨርስቲው ቀውስ እስከዛሬ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በወቅቱ የዩንቨርስቲ ተማሪዎቹ 4 ጥያቄዎችን በማንሳት ያመጹ ቢሆንም ከወቅቷ ሚኒስቴር ያገኙት የመጨረሻው መልስ ‹‹ካልፈለጋችሁ ግቢውን ጥላችሁ ውጡ›› የሚል ነው፡፡ ተማሪዎቹ በእምቢተኝነት አድማቸውን በመቀጠላቸው ደግሞ በአድማ በታኞች ብዙዎች ሲጎዱ ለሞት የተዳረጉም እንዳሉ በወቅቱ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ጉባኤ ዝርዝር መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ የዩንቨርስቲው ማኅበር በኢሕአዴግ ዘመን ‹ሕሊና› የተሰኘ ጋዜጣ ሦስት ጊዜ ያህል ብቻ ያሳተመ እና ያሰራጨ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ታግዷል፡፡ አሁን ሁሉም ሊባል በሚችል ሁኔታ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ማኅበራት ፕሬዚደንቶች በውስጠ ታዋቂነት ካድሬዎች ናቸው፡፡
የመምህራን ማኅበሩን የነጻነቱ ዘመኑ በ1999 ከማብቃቱ በፊት ፕሬዚደንቱ የነበሩት ታዬ ወልደሰማያት ታስረው ሲፈቱ ከአገር ተሰደዋል፡፡ የግጭቱ መንስኤ ነው የሚባለው መንግሥት የሚያምነውን ማኅበር አዲሱ ኢመማ በማለት ለመፍጠር መሞከሩ ነው፡፡ ጉዳዩ ፍርድቤት የደረሰ ቢሆንም መንግሥት ግን ዕውቅናውን ለአዲሱ ሰጥቶ የቀድሞውን አፈራርሶታል፡፡ የመምህራን ማኅበሩ የውድቀት ምልክት ነው ብዬ እዚህ ልፈርድበት የሚያስደፍረኝ በ2004 የመምህራን ደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ ለዲፕሎማ ምሩቅ 31 ብር፣ ለዲግሪ ምሩቅ ደግሞ 73 ብር እንዲሆን ሲወሰን ማኅበሩ - ውሳኔውን ማድነቁን በማጣቀስ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ማኅበራት የቆሙለትን አካል ጥቅም በማስጠበቅ ፈንታ የመንግሥትን ፊት እያዩ ማዳነቅ ወይም ማራከስ ሲይዙ ፋይዳቸው ዋጋ ያጣል፡፡
በሌላ በኩል በሕግ ባይከለከልም ሌላ የመምኅራን ማኅበር ለማቋቋም እንደቀድሞው ምቹ የፖለቲካ ሁኔታ እንደሌላ የሚናገሩም አሉ፡፡ The Status of Governance, Academic Freedom, and Teaching Personnel in Ethiopian Higher Education Institutions በሚል በFSS ርዕስ በተደረገ ጥናት ላይ ነጻ የመምህራን ማኅበር ለማቋቋም ማሰብ በጅማ ዩንቨርስቲ መምህራን ‹‹unattainable luxury›› ተብሎ ሲገለጽ የባሕር ዳር ዩንቨርስቲ ተወያዮች ደግሞ ‹‹You never think of forming teachers’ association since the political environment is complex and ambiguous›› በማለት የመምህራን ማኅበር ማቋቋምን እንደተአምር ገልፀውታል፡፡ ይህንኑ በሚያጠናክር መልኩ ያለፈውን ከመፍረሱ በፊት እና አዲሱ እየተቋቋመ ሳለ የነበራቸውን አቋም ሲተቹ፣ አሰፋ ፍስሐ የተባሉ ጸሐፊ Ethiopia's Experiment in Accommodating Diversity: 20 Years’ Balance Sheet ባሉት መጣጥፋቸው ላይ ‹‹ሁለት የመምህራን ማኅበራት አሉ፤ አንዱ ገዢውን ፓርቲ ሌላኛው ተቃዋሚዎችን ይደግፋሉ›› በማለት ከፖለቲካ አጀንዳ የፀዱ (ነጻ) እንዳልሆኑ መስክረዋል፡፡
አዲስ አበባ የወጣቶች ማኅበር አላት፤ የወጣቶቹ ማኅበር ከኢሕአዴግ ደጋፊዎች ወጣቶች ሊግ የሚለይበት አንዳችም ባሕሪ የለውም፤ የቀድሞ የወጣቶች ማኅበሩ ፕሬዚደንት የነበሩት አቶ ታጠቅ አሁን ሁነኛ ሹመት በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የአሁኖቹም ‹‹ወጣትነታቸው›› ሲያልፍበት ይሾማሉ፡፡ ማኅበራቱ የመንግሥትን ሥርዐት መደገፋቸው እንደጥፋት ላይቆጠር ይችላል፤ ሆኖም በመንግሥታዊ ሥርዐቱ ውስጥ የሚወክሏቸውን የኅብረተሰብ አካላት ጥቅም በሕጉ ውስጥ በአግባቡ ካላስጠበቁ ቅቡልነት ያሳጣቸዋል፡፡ አሁን እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፡፡
የሴቶች ማኅበርም አለ፣ ከኢሕአዴግ ደጋፊ የሴቶች ሊግ የሚለይበት የለም፤ በጥቅሉ ሁሉም ማኅበር (የንግዶቹን ጥቃቅን እና አነስተኛ ማኅበራት ጨምሮ) በኢሕአዴግ እና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ክበብ ውስጥ የተቀነበቡ እና አሻግረው ማየት እንዳይችሉ ተደርገው የተሠሩ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ሌሎቹንም በገለልተኛ ወገኖች የሚመሠረቱ ማኅበራት ካድሬዎች በግራም በቀኝም ብለው የፕሬዚደንትነቱን ስፍራ ይቆናጠጡ እና የመንግሥትን ሕልም ማስፈፀሚያ ያደርጉታል፡፡ በካድሬዎች የማይመሩትም የባለሙያዎች ማኅበራት ሳይቀሩ ኢሕአዴግን ላለማስቀየም ወይም ለማኅበሩ ሕልውና ሲሉ እውነትን ለመናገር ከመቆጠብ ጀምሮ የሠሩትን ጥናት ውጤት ለሕዝብ ይፋ ሳያደርጉ የመደርደሪያ ማሞቂያ አድርጎ እስከማቆየት ድረስ ይዘልቃሉ፡፡ በጥቅሉ አሁንም ማኅበራት አሉ፤ ማኅበራቱ ግን እንኳን የሥርዐት መሻሻልና ለውጥ ሊጠይቁ ቀርቶ ቢሳሳትም ባይሳሳት መንግሥትን ከመደገፍ የተለየ ተግባር የላቸውም - የኔ መደምደሚያ ነው፡፡
------
ማስታወሻ፡-
ይህ ጽሑፍ ‹‹ስለለውጥ›› በሚል የሚቀርቡት ተከታታይ ጽሑፎች አካል ነው፤
-----
ተጓዳኝ ጽሑፎች፤
-----
የዚህ ጽሑፍ ዋና ቅጂ በኢትዮጵያ እንዳይነበብ በታገደው
የዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ ይገኛል፡፡