አንተነህ መርዕድ
ላለፉት አርባ አመታት በአምባገነኖች መዳፍና በካድሬዎች ቁጥጥር ስር ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘላቂ ነፃነት እስካላገኘ ድረስ የስርዓት መቀየር ብቻ ለነፃነቱ ዋስትና አልሆነውም፤ አይሆነውምም። አምባገነኖች ጉልበቱን ከመበዝበዝ፣ ከማሰርና ከመግደል አልፎ ስብዕናውን በመግፈፍ የጎደፈ አስተሳሰባቸውንና ፍልስፍናቸውን በዜጎች አዕምሮ በመሙላት አገዛዛቸውን ዘላቂ ያደረጉ ይመስላቸዋል። የሚገርመው ደርግ ሆነ ወያኔ የህዝብ መሰረት ሲያጡ፣ ዙርያ ገባው ገደል ሲሆንባቸው፤ በካድሬዎቻቸው ህዝቡን ሰብስቦ በፕሮፓጋንዳቸው ማጥመቅ ልትበጠስ የደረሰችውን በስልጣን ዘመን የሚያራዝምላቸው ይመስላቸዋል።
ደርግ በመጨረሻው ዘመን እንደ ወያኔ ህዝቡን እየሰበሰበ እውቀት በሌላቸው እበላባይ ካድሬዎች አማካይነት በግዴታ ማርክሲዝም ሌኒንዝምን ቋቅ እስኪል ለመጋት ታግሎዋል። የታለመው ህዝብን የማዘናጋትተልዕኮ አልሰራም፣ በውርደት ከመውደቅ ግን አላዳነውም። ይህንን ባንድ ምሳሌ ልቋጨው። በአዲስ አበባ ዩኒቭርሲቲ ዓለም ያደነቃቸው፣ በእውቀታቸው አንቱ የተባሉ ምሁራን እየተገደዱ በመኮንን አዳራሽ ከቢሮ ሰራተኞች፣ ከዘቨኞች፣ ከፅዳት ሰራተኞች ጋር ታጉረው በእድሜም በዕውቀትም እዚህ ግቡ የማይባሉ ውርጋጥ ካድሬዎች እንጨት፣ እንጨት የሚል የፍልስፍና ፕሮፓጋንዳ ይዥጎደጎድባቸዋል። ከግማሽ በላይ የሚሆነው የተሰላቸው ተሰብሳቢ በየጥጉ እንቅልፉን ይለጥጣል። እውነት መሆኑን ባላውቅም ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አሉት የተባለው እውነቱን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ጮርቃው ወጣት ተማሪ ካድሬ መምህሮቹን ጭምር ብዙ ለማስተማር ቀድሞ የተሞላውንና እሱም በቅጡ ያልገባውን ፍልስፍና ከቀባጣጠረ በኋላ ጥያቄ ወይንም አስተያየት ካላችሁ በማለት ይጠይቃል። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እጃቸውን ያወጡና “ይህንን ነገር ደጋግምችሁ ስታስተምሩን ከረማችሁ። አሁን ፈትኑንና የወደቀ የወደቀውን እንደገና አስተምሩ” ብለው ተቀመጡ ይባላል። ግፍን ከመቃወም ግንባራቸውን የማያጥፉት ፕሮፌሰር መስፍን ይህንን ከማለት እንደማይመለሱ ሁላችንም እርግጠኛ ነን።
በተመሳሳይ ሁኔታ ሰሞኑን ወያኔ ስልጣኑን እንዳስረከበው ደርግ ዜጎችን እየሰበሰበ ብዙ ሚሊዮን ብር ወጭ አድርጎ በግዴታ አስተምራለሁ እያለ ይገኛል። የሚገርመው የወያኔን ትምህርት ተቃዋሚው መብዛቱ ነው። በሁሉም የአገሪቱ ክልል እንደሚደረገው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራኑን ሰብስበው የፌዴሬሽን ምክርቤቱ ሰብሳቢ ካድሬው ካሳ ተክለብርሃን ለምሁራኑ ትምህርት ሊሰጡ ሲሞክሩ ተቃውሞው የበረታ ነበር። እንደ ፕሮፌሰር መስፍን በሚገርም ሁኔታ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ “ለመሆኑ በየትኛው እውቀታችሁ ነው እኛን እናንተ የምታስተምሩት? ካንተ ብንጀምር እውቀትህ ምን ያህል ሆኖ ነው እዚህ ያለነውን ለማስተማር ያስደፈረህ? ለመሆኑ አታፍሩም?” በሚል መሽንቆጣቸውን ስሰማ ደንቆኛል። የበየነ ሃሳብ በከፍተኛ ጭብጨባ ብቻ ሳይሆን በተጨማሪ የተቃውሞ ሃሳቦች በተሰብሳቢው ተደግፏ። ብዙዎችን ያስደነቀው የካሳ ተክለ ብርሃን ቻይነት ነው። ፀጥ ብሎ ወቀሳውንም ስድቡንም ጠጥቶ ስብሰባውን ቀጥሏል። ሌሎች ቢሆኑ በትነውት ይሄዱ ነበር ተብሏል።
አንባቢ በየነ ጴጥሮስን ከመስፍን ወልደማርያም ጋር እኩል ሚዛን ውስጥ እንዳያስቀምጥ አስጠነቅቃለሁ። መስፍን ወልደማርያም ያመኑትን ያለፍርሃት የሚናገሩ፣ የሚናገሩትን ደግሞ የሚያደርጉ፤ ለግል ዝና፣ ስልጣን ሆነ ሃብት የማያጎበድዱ በየጊዜው የተፈተኑ ደፋር ዜጋ ሲሆኑ በየነ ጴጥሮስ ከዚያ በታቃራኒው የቆሙ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል። ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል ይባላልና። የእናት ኢትዮጵያ ሆድ ዝጉርጉር ስለሆነ በየነ ጴጥሮስን ከመስፍን ወልደማርያም መዘነቅ አይቻለንም። ስለነዚህ ሁለት ሰዎች ብዙ ለማለት ቦታው አይደለም ሌላ ቀን እመጣበታለሁ፤ በተለይ ስለ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም። ወደተነሳሁበት ልመልሳችሁ።
የህዝቡ ፀጥ ረጭ ማለትና ታቃዋሚዎች ለሰልፍ ሲጠሩት ግልብጥ ብሎ መውጣቱ እንቅልፍ የነሳው ወያኔ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን፣ መምህራንን፣ የመንግስት ሰራጠኞችን፣ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን፣ የስርዓቱን ደጋፊዎችንና ባጠቃላይ ህዝቡን ከፍተኛ ወጭ አውጥቶ የሚያምስበት ብዙ ምክንያቶች አሉት። ዋና ናቸው የምላቸውን እንደዚህ ላስቀምጥ።
ለመጭው ምርጫ ያደረበትን ስጋት ለማቃለል የውሃ ልኩን ለመለየት
በስለላ መዋቅሩ ሊለዩ ያልቻሉና ይቃወሙኛል ያላቸውን ለቅሞ ለማወቅ
ጥርሳቸው ያለቀ አገልጋዮችን ወርውሮ በአዳዲስ ምልምሎች ለመተካት
እንደደርግ ማርክሲዝም በልማታዊ መንግስት ፅንሰ ሃሳብ ህዝብን ለማደንዘዝ
እየከሸፈ ያለው ከፋፋይ የዘር ፖለቲካ እንዲያንሰራራና በተለይም ሁለቱን አንጋፋ የአማራና የኦሮሞን ህዝብ የተለያየ ስም በመስጠት አንገታቸውን ደፍተው እንዲቆዩ ለማድረግ
የምርጫ ዘመቻ በይፋ ከመታወጁ በፊትና ታቃዋሚዎችም ወደ ህዝቡ ከመቅረባቸው ቀድሞ ለራሱ ጥርጊያ መንገዱን ለማመቻቸት የሚሉትና ሌሎችንም ታሳቢ አድርጎ እንድሆነ ያስታውቃል።
ወያኔ ኢህአዴግ አቅዶ ተነስቷል ካልሁዋቸው ነጥቦች ምን ያህል ተጠቃሚ እንደሚሆን ራሱም የሚያውቀው ጊዜም ቆይቶ የሚመሰክረው ሲሆን “አፋፍ ለአፋፍ መቀደስ የተኛ ሰይጣን መቀስቀስ” እንዲሉ ያልጠበቀውን አስቀያሚ ውጤት እያሳየው ለመሆኑ የኢሳትን ዘገባና ድረገጾችን የሚከታተል ሁሉ የሚገነዘበው ነው። የመጭውን ምርጫ ውሃ ልክ ለመለካት ጊዜና ጉልበት ማባከን ባልተገባው ነበር። በ1997 ዓ ም ምርጫ ወያኔን የማይመርጥ መሆኑን ያሳየ ህዝብ አሁን የባሰ ጭቆናና ግፍ ተንሰራፍቶ ያ ሁሉ በደል ተፈጽሞበት ለወያኔ የሚሳሳ ልብ አይኖረውምና።
ይቃወሙኛል ያላቸውን ለቅሞ ለማውጣትም ቢሆን ጣመን ሊመታው አይገባም። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎት ፍርሃትን አሽቀንጥረው በመጣል ያቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሉአላዊነት ጉዳይ፣ የጎጠኝነት ፖለቲካ ከፋፋፍ ደባ፣ የውሸት የኤኮኖሚ እድገት፣ የፍትህ እጦት፣ የህወሃት የበላይነትበሁሉም ዘርፍ መንገሥ፣ ወዘተ መድረኩ ላይ በግልጽ ተሞግቶባቸዋል። አፄ ምኒልክንና ቀዳማዊ ኃይለስላሴን ይቅርና ደርግን እንኳ የሚወቅሱበት የሞራል ብቃት እንደሌላቸው በመድረኩ ተነግሯቸዋል “በራሷ መብራት እርቃኗን አዩባት” ይሏል የወያኔ የሰሞኑ የውይይት መድረክ ነው። ስለዚህ ስንቱን ለቅሞ አስሮና ተከታትሎ ይጨርሳል??
ልማታዊ መንግስት ማለት ጥቂቶቻችሁን አክብሮ ብዙዎቻችንን ማደህየት ነው? የሚለው ጥያቄ ብቻ የፅንሰሃሳቡን ፉርሽነትና የህዝቡንም ብስለት አረጋግጧል። ለሃያ ሶስት ዓመታት የተደለቀው የዘር ፖለቲካ ለአገሪቱ የተወው ጠባሳ ለመሻር ገና ብዙ መስዋዕት የሚጠይቅ ቢሆንም ኢትዮጵያ አልጠፋቸም። አትጠፋምም። በተለይ የኦሮሞና የአማራ ልሂቃን ካንቀላፉበት መንቃት እንዲሁም ከተሳሳተ አመለካከታቸው ወጥተው ለግል ጠባብ ፍላጎታቸውና ለዝናቸው ሳይሆን ለህዝባቸው ጠቃሚ ነገር ማሰብና መተግበር አለባቸው።
የዘረኝነት መሃንዲስ የሆነው መለስ ዜናዊ ህይወቱ ቢያልፍም እየቆየ የሚፈነዳ ቦምብ ቀብሮ ሄዷል። እንግሊዞች ቅኝ በገዙአቸው አገሮች የፈፀሙትን ያህል ሸር ሰርቷል። ማክሸፍ የኢትዮጵያዊ ሁሉ ሃላፊነት ነው። ሁለት ተጨባጭ ምሳሌ ልጥቀስላችሁ። በዚህ በኩል ትግርኛ ተናጋሪ ወንድሞቼ ብታግዙኝ ምንኛ ደስ ባለኝ። ይህንን ጉድይ በሚገባ የምታውቁትና ባርምሞ ብትቀመጡም እዳው የእናንተም ነውና እንረዳዳ። በአንድ ወቅት መለስ ዜናዊ ትግራይ ሄዶ የአገር አዛውንቶችንና ታዋቂ ግለሰቦችን ይሰበስብና “ምን አድርገናችሁ ነው ድጋፋችሁ የቀዘቀዘው? ተቃዋሚዎችን ለመስማትም ጆሮአችሁን የሰጣችሁት? ከተሳሳትን ታረሙ በሉን እንጂ አረናንና ነፍጠኞችን ለምን ትሰማላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። የአገር ሽማግሌዎች እየተነሱ “ከአብራካችን ልጆቻችንን ያስረከብናችሁና የሞቱት፣ ከሌለን አካፍለን አብልተን በደርግ ጦር እየተለበለብን የደገፍናችሁ አንተ፣ ስዩም፣ አባይ፣ ስብሃት ነጋና ጥቂቶቻችሁ ሚሊየነር ሁናችሁ እኛና ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ እንድንለያይ፣ በድህነት እንድንማቅቅ ነው?ምን ጥሩ ነገር ሰራችሁ?” የሚሉትንና ሌሎችን መሰረታዊ ጥያቄዎች ሲያቀርቡለት የመለሰላቸው እንዲህ ሲል ነው። “አዎን ያላችሁን ሁሉ ትክክል ነው። አጥፍተናል። ድጋፋችሁን አትንፈጉን እናርማለን። አንድ ትልቅ ጥሩ ነገር ግን መስራታችንን አትዘንጉ። ለትግራይ ህዝብ አንገት መድፋት ምክንያት የሚሆኑ አማራና ኦሮሞን ለያይተንላችኋል። አማራን ነፍጠኛ፣ ኦሮሞን ጠባብ ብለን ቅስማቸውን በመስበራችን ትግሬ አንገቱን ቀና አድርጎ የሄደበት ጊዜ እንደዛሬ አልተገኘም” አላቸው። ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ህወሃት በሚገባና በተሳካለት ሁኔታ የሰራውም ይህንን ነበር። ኦሮሞ ወይም አማራ ነኝ የሚልና በተዘጋጀለት ወጥመድ ውስጥ ራሱን አስገብቶ የሚንቀሳቀስ ሁሉ ከዚህ የባሰና የወረደ ድንቁርናና ጅልነት የት ይገኛል?
መለስ በዚህ አላበቃም አብዛኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች በክረምት ትምህርት ቤት ሲዘጋ በጫት፣ በሲጋራና ባልኮል እንዲናውዙ ሲድረግ የትግራይ ወጣቶች ክረምቱን ሙሉ ልዩ ስልጠናና ትምህርት ሲሰጣቸው ይከርማል። ይህ ገና ስልጣን በያዙ ማግስት ጀምሮ አብዛኞቹ አገሪቱ ውስጥ ያሉት ተቋማት ውስጥ ለትግራይ ወጣቶችና ሰራተኞች በየክረምቱ ልዩ ስልጠና ሲሰጥ ቆይቶ አሁን አሁን ትግራይ በሚገኙ ተቋማት ያደርጉታል። በቂ ቦታ ገንብተዋልና። በየወቅቱም መለስ በመካከላቸው የገኝቶ ወጣቶቹን ያበረታታቸዋል። በሌላ ክልል ይህንን አድርጎ አያውቅም። የኢትዮጵያ መሪ ሳይሆንና ኢትዮጵያዊ ሳይሆን የሞተ ቢኖር መለስ ዜናዊ ብቻ ነው። በአንድ ወቅት ለሰበሰባቸው ሰልጣኝ ወጣቶች የተናገረው ግን ንፁህ ህሊና ያላቸውን ተሳታፊዎች አስደንጧል። ባጭሩ እንዲህ ነበር ያለው። “እናንተ እድለኞች ናችሁ። እኛ እንደናንተ በአካባቢያችን ሳንማር በወጣትነት መዳፍ የማትሸፍን ስኳር እየቃምን፣ አቀበት ቁቁለት ወርደን ተዋግተን፣ ሞተን፣ ቆስለን ነው ለዚህ የበቃነውና ለዚህ ያበቃናችሁ። እናንተ ይህችን አገር ለረጂም ጊዜ ለመምራት መዘጋጀት አለባችሁ። ይህ ደግሞ የሚሆነው በትምህርት ከሌላው ስትልቁና ኤኮኖሚውን መቆጣጠር ስትችሉ ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ሁሉን አመቻችተንላችኋ። እናመቻችላችኋለንም። ይህ እድል ካመለጣችሁና አማራና ኦሮሞዎች ስልጣን ከያዙ ተስፋ አይኖራችሁም” ሲል በለጋ አእምሮአቸው ላይ መርዙ ለመጠቅጠቅ ሞክሯል።
መለስ ለትግራይ ሽማግሎችና ወጣቶች የተናገረው መራራ በዘረኝነት የተሞላው ቅስቀሳ ለነሱ በማሰብ ሳይሆን በስልጣን ለመቆየት የትግራይን ህዝብ መሰረት ላለማጣትና የበለጠም ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር በጥርጣሬ እየተያየ እንዲኖር ለማድረግ ነው። የትግራይ ህዝብ ለጥቂት የህወሃት ባለስልጣናት ምቾትና ስልጣን ሲል ከዘላቂው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መለያየት የሚመርጥ አይደለም። ፕሮፓጋንዳውና ጊዜያዊ ጥቅማጥቅም ጥቂቶችን አማልልሎ እንደሆነ እንጂ ብዙሃኑ የትግራይ ህዝብ እውነቱን የሚረዳ ነው። ስለዚህም ነው የትግራይ ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ በበለጠ አፈና ውስጥ የሚገኘው። በነፃነት ሃሳቡን እንዲገልፅና እንዲንቀሳቀስ ቢደረግ የትግራይ ህዝብ በትክክል ምርጫውን ያውቃል። ልክ እንደትናንቱ እንደ አፄ ዮሃንስ፣ እንደ አሉላ ኢትዮጵያዊነቱን ይመርጣል።
የሰሞኑ ትምህርት ያሳየን ነገር ቢኖር የህዝቡን ብስለትና የወያኔን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው። ከኃይለስላሴና ከምኒልክ ያነሰች አገር ይዛችሁ እነሱን መውቀስ አትችሉም። ጦሩን ደህንነቱ፣ ሁሉንም ቁልፍ ቦታና ኤኮኖሚውን በአንድ መንደርልጆች አስይዛችሁ ዴሞክራሲ አለ ለምን ትላላችሁ? ሃያ ሶስት ዓመት መርታችሁ ከአለንበት ውድቀት የከተታችሁን አርባ ዓመት ለመግዛት እንዴት ትመኛላችሁ?…..የመሳሰለው ጥያቄ እንኳን ከቀሪው ህዝብ ሞሰብ መላስ ከሰለቻቸው ብአዴን፣ ኦህዴድ ደህዴድ ዴድ…ዴድ ዴድ ከተባሉ ደጋፊዎቻቸው ጋር እንኳን የሚያካርማቸው አይደለም።
ቸር እንሰንብት
amerid2000@gmail.com
No comments:
Post a Comment