Sunday, October 19, 2014

15 ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ ባቀረበው ሀሳብ ላይ እንደማይወያዩ ገለጹ

ምርጫ ቦርድ ዛሬ ጥቅምት 8/2007 ዓ.ም አረቀቅኩት ባለው የጊዜ ሰሌዳ ላይ እንወያይ በሚል በሀዋሳ በጠራው ስብሰባ 15 የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቦርዱ ባቀረበው ሀሳብ አንወያይም ማለታቸውን የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦህዴግ) እና ትብብር ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ (ትዴኢ) ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

በሀዋሳ ከተሰበሰቡት 20 ፓርቲዎች መካከል ከኢህአዴግና ከሌሎች አራት ፓርቲዎች ውጭ 15 ፓርቲዎች በየተራ እንዲናገሩ የተደረገ ሲሆን ሁሉም ምርጫ ቦርድ ‹‹በጊዜ ሰሌዳው ላይ እንወያይ›› ብሎ ያቀረበውን ሀሳብ መቃወማቸውን አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡ ፓርቲዎቹ ከጊዜ ሰሌዳው በፊት ስለ ምርጫ ምህዳሩና ፓርቲዎች ስለሚደርስባቸው በደልና ስላለባቸው ችግር ተወያይተው መፍትሄ እንዲያገኙ ምርጫ ቦርድን ጠይቀዋል፡፡

ፓርቲዎቹ አክለውም ‹‹የጊዜ ሰሌዳው ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለ ጊዜ ሰሌዳ ተወያይቶ ለመስማማት 10 ደቂቃ አይፈጅብንም፡፡ ብትፈልጉ ወስናችሁ በኢሜልም ልትልኩልን ትችላላችሁ፡፡ የጊዜ ሰሌዳ የፖለቲካችን ችግር አይደለም፡፡ እኛ የምንፈልገው ምርጫ እንዲካሄድ የሚያስችል ሁኔታ መኖሩን ነው፡፡ እሱ እንዲኖር መወያየት አለብን›› በሚል ቅድሚያ መሰጠት ስላለበት ጉዳይ መጠቆማቸው ተገልጾአል፡፡

የምርጫ ቦርድ ያቀረበውን የመወያያ ሀሳብ ከተቃወሙት መካከል የቤንች ህዝቦች ፓርቲ ‹‹ለምርጫ የሚያመች ሁኔታ ሳይኖር ስለ ጊዜ ሰሌዳ አንወያይም፡፡ ለምርጫ አመች ሁኔታ ሳይፈጠር በጊዜ ሰሌዳ ላይ ተወያይተንና ሌሎቹን ጉዳዮች ችላ ብለን መሄድ አንፈልግም፡፡ ይህ ህዝባችን ለከፋና ውስብስብ ጉዳይ የሚዳርግ ነው፡፡ በመሆኑም ህዝባችን ለከፋና ውስብስብ ችግር መዳረግ አንፈልግም›› በሚል ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ምህዳር መኖር እንዳለበትና ስብሰባውም ለዚሁ ጉዳይ ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት ማስገንዘባቸውን አቶ ግርማ ለነገረ ኢትዮጵያ አክለው ገልጸዋል፡፡

በትናንትናው ዕለት ምርጫ ቦርድ አገር አቀፍ ፓርቲዎችን አዲስ አበባ ጊዮን ሆቴል ሰብስቦ የነበር ሲሆን ሰማያዊ፣ መኢዴፓ፣ ኢብአፓ ቦርዱ ስለ ጊዜ ሰሌዳው እንዲወያዩ ካቀረበው ያቀረበውን ሀሳብ በመቃወም ስብሰባውን ጥለው መውጣታቸውን መዘገባችን ይታወቃል፡፡

No comments: