Sunday, October 19, 2014

ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፡ በአሜሪካ ሲያትል ዋሽንግተን ዉስጥ የተሳካ ህዝባዊ ስብሰባ አካሄደ

የግንቦት 7 ንቅናቄ ቅዳሜ ኦክቶበር 11 ቀን 2014 አ.ም በአሜሪካ ሲያትል ከተማ ደማቅ ህዝባዊ ስብሰባ ማካሄዱን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በዚህ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ በሲያትልና አጎራባች ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በነቂስ በመውጣት የታደሙበት እንደነበር ያደረሰን ዘጋቢያችን አገር ወዳድ ኢትዮጵያኑ በስብሰባው ላይ በክብር እንግድነት ከተገኙት የንቅናቄው ሊቀመንበር ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር ሰፊ አገራዊ ውይይት ማካሄዳቸውን ለማወቅ ተችሏል። በሲያትል የተካሄደው ይህ ህዝባዊ ስብሰባ ኢትዮጵያውያን በዘር በሃይማኖት በጎሳ ሳይለያዩ በአንድነት በመሰባሰብ በአገራቸው ጉዳይ ላይ በሰፊው የመከሩበት፤ ኢትዮጵያዊነት እጅግ አምሮና አሸብርቆ የታየበት እንደነበርም ተመልክቷል።
በህዝባዊ ስብሰባው ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ዶ/ር ብርሀኑ ለስብሰባው ታዳሚዎች ባደረጉት ንግግር “የምንገኝበት ወቅት ጊዜያችንን እንደ ከዚህ ቀደሙ መቋጫ በሌለው ውይይትና ጭቅጭቅ የምናጠፋበት ሳይሆን፤ ስለ ነፃነቴ እታገላለሁ የሚል ወደ ተግባራዊው ትግል የሚቀላቀልበት፤ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ትግሉን መቀላቀል የፈራ ዝም ሊል የሚገባበት ወቅት መሆኑን በአንክሮ በማስገንዘብ በተጨማሪ የነፃነት ትግሉን በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳ የሚገኘውን የእርስ በርስ ጥልና ሽኩቻ በአስቸኳይ ቆሞ ሁላችንም በአንድነት በመነሳት በዋናው አላማችን ላይ ማለትም የጉጅሌው ወያኔን አገዛዝ ለማስወገድ መዝመት ይገባናል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል። በተለይ የነፃነት ትግሉ ለመቀላቀል እስካሁን እድሉን ላላገኙና በትግሉ ላይ የራሳቸው የታሪክ አሻራ ማሳረፍ ለሚሹ ወገኖችም የተቀላቀሉን ጥር ማቅረባቸውን ለማወቅ ተችሏል። የቀረበላቸውን ጥሪ በመጠቀም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ኢትዮጵያውያን በአባልነት እንዲሁም በደጋፊነት በመመዝገብ ግንቦት 7 ትን መቀላቀል መቻላቸው ታውቋል። ትግሉ አሁን ላይ የደረሰበትን ደረጃ አስመልክቶ ለታዳሚዎች በስፋት ያብራሩት ዶ/ር ብርሃኑ ተሰብሳቢዎቹ እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ግንቦት 7 ለነደፋቸው የትግል ስልቶች ማለትም ለሕዝባዊ ተቃውሞ፣ ሕዝባዊ እምቢተኝነት እና ሕዝባዊ አመጽ ዛሬ ነገ ሳይባል ምላሽ መስጠት መጀመር እንዳለበት ማሳሰብያ ማቅረቡ ታውቋል። በተለይ እነዚህን ስልቶች በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ በተቀናጀ ሁኔታ መተገበር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቆም ብሎ ሊያስብና ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሊገባ የሚገባበት ሰአት አሁን ነው ያሉት ዶ/ር ብርሃኑ ይህንን በተሳካ ሁኔታ መተግበር ስንችል ጉጅሌዎቹን ከአገራችንንና ከህዝባችን ጫንቃ ማውረድ እንችላለን ሲሉ ተናግረዋል።
ዶ/ር ብርሃኑ ከተሰብሳቢው ለቀረበላቸው በርካታ ጥያቄዎችም አጥጋቢ ምላሽ ሰጥተዋል። በተለይ በኤርትራ በኩል እየተደረገ ያለውን ትግል አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት በተሰብሳቢዎች ዘንድ የነበረውን ብዥታ ማጥራት መቻላቸውንና ተሰብሳቢዎቹ እየተደረገ ላለው ትግል በጭብጨባ ድጋፍ መስጠታቸውን ከስፍረሰው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በመጨረሻም በስብሰባው ላይ በጠላት እጅ ወድቀው የሚገኙት የንቅናቄያችን ዋና ፀሐፊ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሥራዎች በስፋት መወሳታቸውን ለማውቅ የተቻለ ሲሆን ኢትዮጵያውያኑ የአቶ አንዳርጋቸው ስራዎች ሲቀርቡ አብዛኞቹ በሐዘን እና በቁጭት ሲያነቡ እንደነበርም የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በስብሰባው መገባደጃ ላይ ለጨረታ የቀረበው የነፃነት አርበኛው የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ፎቶግራፍም በከፍተኛ ገንዘብ መሸጡ ታውቋል። ኢትዮጵያውያኑ በጋራ እጅ ለእጅ በመያያዝ እየተደረገ ያለውን የነፃነት ትግል ከዳር ለማድረስ ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት መነሳታቸውን በቃለ መሐላ ካረጋገጡ በኋላ ስብሰባው መፈጸሙም ታውቋል።

No comments: