(ሳተናው) የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ኦኬሎ ኦኳይን ጨምሮ ሰባት ጓደኞቻቸው ጥፋተኛ በተባሉባቸው ወንጀሎች እስከ 9 አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ።
ተከሳሾቹ የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ኦኬሎ ኦኳይ፣ ዴቪድ ኡጁሉ፣ ኡቻን ኦፔይ፣ ኡማን ኝክየው፣ ኡጁሉ ቻም፣ አታካ ኡዋር እና ኡባንግ ኡመድ ናቸው።
1ኛ ተከሳሽ ኦኬሎ ኦኳይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር በነበሩበት 1996 ዓ.ም፥ በክልሉ የሚገኙ የአኙዋክና የኑዌር ብሄረሰብ አባላት መካከል ግጭት ተቀስቅሶ በግጭቱ ከ400 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።
ኦኬሎ የግጭቱን መንስኤ በማስመልከት ለመንግስትና ለውጪ አገራት ጋዜጠኞች በሰጧቸው መግለጫዎች ግድያ የፈጸሙት መለስ ዜናዊ ያስታጠቃቸው ሰዎች ናቸው በማለት መናገራቸው በመንግስት ሰዎች አልተወደደም፡፡
ለህይወታቸው የሰጉት ኦኬሎ የግል ሹፌራቸውንና ጠባቂያቸውን በማስከተል አገር ለቀው ከወጡ በኋላ በጋምቤላ ክልል የሚፈጸመውን የኢሰብዓዊነት ተግባር ለማጋለጥ ብዙ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
በመጨረሻም ከስዊዲን ወደ ደቡብ ሱዳን ለሰብዓዊ ተግባር በመጡበት ተይዘው ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡
ኦኬሎ በማዕከላዊ ከፍተኛ ምርመራ ሲካሄድባቸው ቆይቶ በቅርቡ ወደቃሊቲ ወህኒ ቤት እንዲዘዋወሩ ተደርገው በከፍተኛው ፍርድ ቤት ክሳቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡
ኦኬሎ የቀረበባቸውን ክስ እንዳልደፈጸሙ በመግለጽ ቢከራከሩም ፣ፖሊስ ቃላቸውን በኃይል መቀበሉን ቢናገሩም ፍርድ ቤቱ የቀረበባቸውን ክስ አላስተባበሉም በማለት በዘጠኝ አመት ጽኑ እስራት ይቀጡ ዘንድ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
ከኦኬሎ ጋር አንድ ደቡብ ሱዳናዊን ጨምሮ ስድስት ተከሳሾች የጋምቤላን ሰላም ለማወክና ለማፈራረስ የሚል ክስ ቀርቦባቸው የተፈረደባቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
No comments:
Post a Comment