Monday, September 7, 2015

ኤርትራ ኢትዮጵያን አስጠነቀቀች

ጷግሜን ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኤኤፍፒ የአገሪቱን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በመጥቀስ እንደዘገበው፣ የኢህአዴግ መንግስት በኤርትራ ላይ የሚያሰማው የጦርነት ዛቻና አገሪቱን እወራለሁ እያለ የሚያሰማው መግለጫ ጨምሯል። የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት /ህወሃት በተለየ ሁኔታ በኤርትራ ላይ ዛቻ እያሰማ ነው። በክረምቱ ወር ይሰማ የነበረው ፉከራ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ተጠናክሮ መቀጠሉን የማስታወቂያ ሚኒስቴሩ ገልጿል። የህወሃት አገዛዝ ኤርትራን እንዲወር ከአሜሪካ ፈቃድ አግኝቻለሁ እያለ በመናገር ላይ መሆኑን የገለጸው የኤርትራ መንግስት፣ በተለይም ከኤርትራ ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ የሚጠረጥራቸውን ሃይሎች ለማሸማቀቅ እየጣረ መሆኑን ገልጿል። ካለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሃይሎች በትግራይና በአማራ አካባቢዎች ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ፈጽመዋል። የተቃዋሚ ሃይሎች ሃይላቸውን እያጠናከሩ መምጣታቸው፣ ገዢውን ፓርቲ ስጋት ላይ ጥሎታል። በሌላ በኩል የኢህአዴግ ጉባኤ የግንባሩን ችግር አባባሰው እንጅ አልፈታውም ተባለ ሰሞኑን በመቀሌ የተካሄደው የኢህአዴግ 10ኛ ጉባኤ የድርጅቱን ችግር አባባሰው እንጅ አልፈታውም ሲሉ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የፓርቲው አባል ተናገሩ። የአመራር አባሉ እንዳሉት፣ ድርጅቱ " በዚህ ሁኔታ መቀጠል አንችልም በሚሉትና በጥንታዊው መንገድ እንጓዝ በሚሉት መካከል በግልጽ ለሁለት ተከፍሏል። ክፍፍሉ በጉባኤው ወቅት በደንብ ቢንጸባረቅም፣ ከጉባኤው በሁዋላም በግልጽ ፈጦ እየወጣ ነው። ነባሩ አመራር "የኢህአዴግ አካሄድ እየተበረዘ ነው" በሚል የቀድሞ ተሰሚነቱን ለማረጋገጥ እየሞከረ ሲሆን፣ አዲሱ አባል ደግሞ የእስከዛሬው አካሄድ ግንባሩን በስልጣን ላይ ለረጅም ጊዜ አያስቀጥለውም በማለት የተወሰኑ ፖለቲካዊ ለውጦች እንዲኖሩ እየጠየቀ ነው። ከአመት በፊት ከዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋር የተደረገው ውይይት አዲሱ የኢህአዴግ አመራር " በዚህ ሁኔታ መጓዝ የለብንም" የሚል አቋም እንዲይዝ አድርጎታል የሚሉት አባሉ፣ በድርጀቱ ውስጥ ለሚታየው ተስፋ መቁረጥ ዋነኛው መነሻም ይህ ነው ይላሉ። አዲሱ ትውልድ ከስርአቱ ጋር አለመገናኘቱ በይበልጥ የታወቀው ታዳጊ ተማሪዎች ያነሱዋቸው የነበሩት ጥያቄዎች ናቸው የሚሉት አባሉ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የውስጥ የድርጅት ፍትጊያው እንደቀጠለ ነበር ሲል ያስታውሳሉ። የመቀሌው ጉባኤ የችግር መስሚያ እንጅ ለችግሮች መፍትሄ የሰጠ አለመሆኑን የገለጹት አባሉ፣ በመጨረሻ ላይ የተሰጠው ውሳኔም ግንባሩ ነባር አመራሮችንም አዲሱን አመራርም ላለማስከፋት፣ ችግሩን አድበስብሶ ማለፍ ነበር ብለዋል። ግንባሩ መሰረታዊ የሆነ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል መሪ እንደሌለውም ይገልጻሉ። በአባይ ወልዱ የሚመራው ህወሃት ድርጅቱ ሳይበረዝ እንዲቀጥል ይፈልጋል። ይህንኑ አቋም ከሞላ ጎደል የመለስ ዜናዊ ወገን ተደርገው የሚታወቁት እነ አቶ በረከትም ይደግፉታል።

Source: ethsat

No comments: