የተባበረችውን ኢትዮጵያን እንገንባ!
በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ኣቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ሲናገሩ ኣገራችንን የሚበትኑ ኣጥፊ ዘሮች ያሏቸውን ሶስት ጉዳዮች ኣነሱ። ኣንደኛው ጠባብነት፣ ሁለተኛው ትምክህተኛነት፣ ሶስተኛው በሃይማኖት ሽፋን የሚራመድ ኣክራሪነት ናቸው ኣሉ። በመሰረቱ እነዚህን ጉዳዮች ኣቶ ሃይለማርያም ለመጀመሪያ ጊዜ ያነሷቸው ጉዳዮች ኣይደሉም። በ”ኢህዓዴግ” ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚነሱ ሁሌም ሲባሉ የነበሩ ናቸው። ኣቶ ሃይለማርያም ኣዲስ ነገር ኣልተናገሩም።
ለማናቸውም ግን እነዚህ ኣደገኛ ዘሮች ከየት መጡ? ኣገሪቱንስ ወዴት እየወሰዱ ነው? በርግጥ ከብሄር ፖለቲካው ኣዝማሪዎች ኣልፎ ወደ ታች ወርዶ የኔብጤው ተራው ህዝብ ኣካባቢ እነዚህ ዘሮች ጎልተው እየታዩ ነው ወይ? የሚለው ጉዳይና ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ያለመቻሏ ጉዳይ፣ የሰብዓዊ መብት ኣያያዝ ጉዳይ ሃላፊነት ለሚሰማው ኢትዮጵያዊ፣ ለዓለማቀፍ ተቋማትና ለኢትዮጵያ ወዳጅ ሃገራት ዲፕሎማቶች በጣም ኣሳሳቢ ጉዳይ ሆኖባቸው ኣያለሁ።
ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግሩ እንመለስና በመጀመሪያ እሳቸው ራሳቸው ያመኗቸው እነዚህ ሶስት ጉዳዮች በሰፊው የሚታዮት በኣንድ ሃገር ውስጥ ፖለቲካው በጠባቡ ሲቀረጽ፣ ወይም በየቤትህ እደር ኣይነት የፖለቲካ ጨዋታ ሲጀመር ወይም የፖለቲካው ጥብቆ ሲጠብ ነው። ሳይንሳዊ በሆነ ኣገላለጽ የማንነት ፖለቲካ (Identity Politics) የሚባለው ሲሆን በተለይ ብዙህ በሆነ ማህበረሰብ ውስጥ ይህ የፖለቲካ ስርዓት ሲዘረጋ የሚያመጣቸው ወይም ከዚያ የሚፈለፈሉ ችግሮች ብዙ ናቸው። የብሄር ፖለቲካ የማህበራዊ ካፒታል ምስጥ ነው። ለዚህም ነው ምሁሩ፣ ተማሪው፣ የተማረው፣ ያልተማረው ሁሉ ላለፉት ሃያ ዓመታት በላይ የብሄር ፖለቲካን ሲነቅፍ የነበረው:: የማንነት ፖለቲካ እነዚህን ኣደገኛ ነገሮች እንደሚያመጣ ብዙ ሳይንሳዊ ምርምር የሚጠይቅም ኣልነበረም። የብሄር ፖለቲካ ስነ- ልቦናው ራሱ ጠባብነት ነው። ከጎሳው ያላለፈ የፖለቲካ ስብእና ይዞ እንዲያድግ የሚያደርግ የፖለቲካ ኣስተሳሰብ የተጫነው በመሆኑ የጠባብነት መነሻው ይሄው የብሄር ፖለቲካ ነው።
ትምክህተኝነት የሚባለውም ከዚሁ ከጠባብ ኣስተሳሰብ የሚመነጭ የኣንድ ዛፍ ቅርንጫፍ ነው። ሰው ጠባብ ሲሆን ነው የሚመካው። በወንዙ በጎሳው ሲመካ ጠባብ ሆኖ ነውና። ጠባቦች ሁል ጊዜም ትምክህተኝነት ኣያጣቸውም። ሁለቱም ባህርያት የተያያዙ ከኣንድ መራራ የብሄር ፖለቲካ ምንጭ የሚቀዱ ናቸው። ጠቅላይ ሚንስትሩ ሲናገሩ ተማሪው ላይ ተጽእኖው ይታያል እንጂ እነዚህን ዘሮች የሚዘራው ኣስተማሪው ነው ኣሉ። ማን ነው የጠባብነትን ፖለቲካ የሚያስተምረው? ህወሃት “ኢህኣዴግ” ኣይደለምን? ህወሃት “ኢህዓዴግ” ከመምጣቱ በፊት ትግሬው፣ ዓማራው፣ ኦሮሞው ወዘተ ኣብሮ ቁጭ ብሎ ሲጫወት መች የብሄር ነገር ትዝ ብሎት ያውቅ ነበር? ቢታወሰውም እየተቀላለደ ከመኖር ውጭ መራራ ስር ኣልነበረውም። ለእነዚህ ኣደገኛ ዘሮች መፈጠርና ማደግ ጥሩ መፈልፈያ የሆነው ራሱ የፖለቲካው ቤት መሆኑን መረዳት ብዙ ምርምር ኣልጠየቀም።
ቡድኖች ለምንድነው የብሄር ወይም የሃይማኖት ማንነታቸውን ይዘው ወደ ፖለቲካ የሚሳቡት? ካልን የፖለቲካን ሃይል መሳሪያ በማድረግ የቡድንን የወል ጥቅምና የበላይነት ለማረጋገጥ ነው። የፖለቲካው ስልጣን የመሳሪያ ሃይል ያለውንና የኢኮኖሚውን ክፍል ስለሚያዝ ያንን ቡድኖች መቆጣጠር ከቻሉ ለቡድናቸው ኣቋራጭ እድገት ዓይነተኛ መሳሪያ ሆኖ ስለሚያዩት ነው። በዚህ የፖለቲካ ድባብ ውስጥ ኣክራሪነት፣ ልዮነትን ማድመቅ የመከሰታቸው እውነት ለምን ጥያቄ ውስጥ ይከተናል? ሃይማኖታዊ ኣክራሪነትም የሚከሰተው ኣጠቃላይ የፖለቲካው ቅርጽ በማንነት ላይ ሲረብብ ሃይማኖታዊ ማንነታቸውን ይዘው ወደ ስልጣን እንዲሳቡ የሚያደርግ ስነ ልቡናዊ ድባብ ሲፈጠር ነው። በመሰረቱ ሃይማኖትን ማጥበቅ ማለት ኣይደለም ኣክራሪነት ማለት። ሃይማኖታዊ ኣክራሪነት የሚፈጠረው በሃይማኖቱ መሰረት ላይ የቆመ ፖለቲካ ለመመስረት መጣርና በጋራ ህልውና (coexistence) ኣለማመን ነው። በግለሰብ ደረጃም ሆነ በቡድን እንዲህ ዓይነት ባህርያት ሲገለጹ ኣክራሪነት መጣ እንላለን። ይህ ኣክራሪነት በኢትዮጵያ ከታየ ኣካባቢያዊ ኣስተዋጾዎች እንዳሉ ሆነው ራሱ የፖለቲካው ተፈጥሮና የመንግስት ኣያያዝ ከፍተኛ ኣስተዋጾ ማድረጋቸው ኣይካድም። በኣጠቃላይ ምንጩ የማንነት ፖለቲካ ሆኖ ሳለ ለምን የመንግስት ሰዎች እነዚህን ችግሮች እየጠቀሱ ኣጥፊዎች ናቸው እንደሚሉ ዶክተር ዳኛቸው በቅርቡ በ VOA እንዳስረዱት ለማንም ኣይገባም። “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል” ነው ያሉት?
ጠቅላይ ሚንስትሩ ራሳቸው እኮ ቢያንስ እንደ ብሄር ራሳቸውን የሚገልጹበት ታእታይ የፖለቲካ ስብእና ባይኖራቸውም በመልክዓምድር በተወሰነ የፖለቲካ ታእታይ ስብእና የታጠሩና ለፈጠራቸው ህወሃት ኣድርባይ ናቸው። የህወሃት ኣባላትም እንዲሁ የፖለቲካ ውስጣዊ ወይም ታእታይ ሰውነታቸው በብሄር ላይ የቆመ ጠባብ ነው። በርግጥ “ኢህዓዴግ” የሚባለውን ለብሰናል ለማለት ከሆነ ህዝቡ ኣይዋጥለትም። ከዚህ በፊት እንደገለጽኩት “ኢህዓዴግ” የሚባል ድርጅትም በዓለም ላይ የለም። ለምን የለም? ከተባለ ከማንነት ፖለቲካ ተፈጥሮ ጋር ያለውን ፍልስፍናዊውን ጉዳይ ልተወውና ኣንድ ጥቂት ተግባራዊ ነገር በማንሳት ላሳይ።
የዛሬ 40 ኣመት ገደማ ሁሉም እንደሚያውቀው ህወሃት ይቋቋማል።በዚህ ወቅት ህወሃት ሲፈጠር የነበረውን ህልም ተግባራዊ ለማድረግ ውሎ ኣድሮ ያስባል። ወደዚያ የሚያደርሰው ኣድራሽ፣ ኣድራሽ ብቻ ሳይሆን እስከ ፈለገው ጊዜ እንዲቆይ፣ ጊዜ እንዲያገኝ የሚያደርገው፣ የሚያግዘው የፕሮጀክት ግብዓት ፈለገ። ጥሩ ኣድራሽና ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚሆነው የተለያዩ ብሄሮችን ስም የያዙ የፖለቲካ ድርጅቶችን መፈልፈል ሆኖ ኣገኘው። በመሆኑም እንደ ኦህዴድ፣ ብዓዴን የመሳሰሉትን ሁሉ ፈለፈለ። እነዚህ ድርጅቶች የህዝብ ብሶት የወለዳቸው፣ ህዝብ የጠየቃቸው ኣይደሉም። ህወሃት ራሱ ለፕሮጀክቱ ግብዓት ይሆኑለት ዘንድ በኣምሳሉ የቀረጻቸው ናቸው። በሌላ ኣገላለጽ እነዚህ ድርጅቶች ራሳቸው ህወሃት ናቸው። ምንምን እንኳን የተለያየ ብሄር ኣባላትን ይዘው ቢመሰረቱም ተገትረው ብናይም በህወሃት ብሶት፣ በህወሃት ራእይ፣ በህወሃት እጅ የተፈጠሩ በህወሃት የህወሃት ናቸው። ኣንዳንዶቹ ድርጅቶች በተለይም ኦህዴድ እንደሚወራው ኣንዳንድ መሪዎቹ የህወሃት ኣባላት ስማቸውን እየቀየሩ ኣመራር ላይ የነበሩበት ሁኔታም ነበር።
ኣቶ በረከት ስምዖን በህወሃት 40ኛ ዓመት ላይ ንግግር ሲያደርጉ እንዲህ ኣሉ
“እኛ ብአዴኖችም ሁሌም ቢሆን ራሳችንን ከህወሓት ነጥለን ያየንበት ጊዜ የለም። ሁላችንም “ወየንቲ ኢና” (ወያኔዎች ነን) ነው የምንለው።” (በረከት ስምዖን)
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ቴድሮስ ኣድሃኖም ደግሞ ይህንን ያስረግጡልናል።
“አንዳንድ ወገኖች …. ስድብ መስሏቸው “ወያኔ” አሉኝ ከጥቂት አመታት በፊት ለተመሳሳይ ጉዳይ በረከት ስምዖን ያለውን አስታወሱኝ“ሁላችንም ወያኔ ነን” አዎ አሁንም ሁላችንም ወያኔን ነን…..እኔ ወያኔ ኢህአዴግ ነኝ! Je Suis Woyane!…. በዚህም ኩራት ይሰማኛል፡፡እኔ ወያኔ ነኝ! ሁላችንም ወያኔ ነን! ይህን ችግር የሚፈታውም በወያኔነት ነው! …እንበርታ፡፡” (ቴድሮስ ኣድሃኖም)
በኣንጻሩ ከህወሃት ኣባላት መንደር ሁላችንም ኦህዴድ ነን ወይም ደህዴግ ወይም ብዓዴን ለማለት ጨርሶ ታስቦ የማያውቅ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም እነዚህ ድርጅቶች እንደ ፖለቲካ ድርጅት በህወሃት ህሊና የሉምና። እንዴውም ኣቶ መለስ እንኳን ከዚህ ቡድን ተወለድኩ ብለው ጠባብና ትምክህተኛነታቸውን በኣደባባይ ሲናገሩ ተደምጠው ነበር። ይሄ ነው ጠባብነት፣ ትምክህትና ኣክራሪነት የሚባለው።
በኣጠቃላይ የሆነ ኣጀንዳ ይዞ የተነሳው ህወሃት ሲሆን በየመንገዱ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚሆኑትን የፖለቲካ ድርጅቶችን የፈለፈለ ሲሆን እነዚህን ግብዓቶች ይዞ ሁዋላ ላይ “ኢህዓዴግ” የሚል ስያሜ ይዞ ብቅ ይላል። “ኢህዓዴግ” የራሱ የህወሃት ፕሮጀክት ማስፈጽሚያ ሲሆን እንደ ፖለቲካ ድርጅት ግን ኣለ ማለት ኣይቻልም። ለዚህም ነው ራሱ በኣድራሽነት የተሰራውና የሚኖረውም። ግንባር በተፈጥሮው ኣድራሽ ሲሆን ይህ በግንባርነት የተዋቀረ ቤት የዚሁ የህወሃት ሌላው የኣዲስ ኣበባ ቤት ነው።
በርግጥ ወደ ተራው ኣባል ኣካባቢ ስናይ የዋህነት ሊኖር ይችላል። ተሰብስበው ግምገማ ሲባል፣ እቅድ ኣውጡ ኣውርዱ ሲባል “ኢህዓዴግ” በህይወት ያለ ይመስላቸው ይሆናል። የለም። ተላላ መሆን ኣያስፈልግም። ህወሃት እነዚህን ድርጅቶች ሲያቆም ኣዲስ ኣበባን ለመቆጣጠር ብቻ ሳይሆን ከዚያ በሁዋላ ደህንነቱንና ወታደሩን እንዲሁም ኢኮኖሚውን እስኪቆጣጠር ግብዓት ስለሚሆኑት ነው። በርግጥም በኣሁኑ ሰዓት በነዚህ ድርጅቶች እገዛ ህወሃት እነዚህን ህልሞቹን ኣሳክቷል። ኣቅጣጫ ነው ያጣው። በመሆኑም የነዚህ ድርጅቶች ኣባላት መታለሉን ማቆም ኣለባቸው። መንቃትና ለለውጥ መነሳት ያስፈልጋል። በቂምና በበቀል ላይ ሳይሆን ሁሉን ነጻ የሚያወጣ የወደፊቱን በማሰብ ላይ የተመሰረተ ቢሆን ነው የሚሻለው።
በኣጠቃላይ የሚንስትሮቻችን የመሪዎቻችን ታእታይ የፖለቲካ መሰረት የወንዝ ፖለቲካ በመሆኑ ከዚህ የብሄር ፖለቲካ ዘር የሚወለደው ያው ጠባብነትና ኣክራሪነት ከመሆን ኣያልፍም።ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ቴድሮስ ኣድሃኖም ከፍ ሲል እንዳየነው እኔ “Je Suis ወያኔ ነኝ” ብለዋል። ይሄ እውነተኛ የፖለቲካ መሰረታቸው ሊሆን ይችላል። የሚገርመው ግን እኚህ ሰው ኣንድ ጊዜ ኒዮርክ በተደረገ ስብሰባ ላይ “ ኒውዮርክ ሜልቲንግ ፖት ናት” ብለው በስሜት ተናገሩ። መልቲንግ ፖት የህወሃት ኣስተሳሰብ ጸር ነው። ባህላዊ ውህደት ማለት ነው ሜልቲንግ ፓት ማለት። እኚህ ሰው ምን ኣልባት ተለውጠው ከሆነ ይህን ያሉት እንዳንል የኒውዮርኩን ንግግር ካደረጉ በሁዋላ ነው እኔ “ Je Suis ወያኔ ነኝ” የሚሉን። እሳቸው ይህን ይበሉ ፣ እኔ ደግሞ Je Suis ኢትዮጵያዊ! እናንተስ?
እንግዲህ ጠቅላይ ሚንስትር ኣቶ ሃይለማርያም ይህን ዘር ኣጥፊ ነው ብለው ካመኑ በዚህ የወንዜ ፖለቲካ ቤት ውስጥ መዋል ማደር የለባቸውም። ሌሎች ምስጢሩ ያልገባቸው የዋህ የህወሃት፣ የብኣዴን፣የደህዴግ ወዘተ ኣባላት ከዚህ የፖለቲካ ኣስተሳሰብ ወጥተው ጠባብነትን የህወሃትን የበላይነት መዋጋት ኣለባቸው። የጠባብነትና የትምክህት ዋና የሆነውን የብሄር ፓለቲካ ቤት ግድግዳውንና ጣራውን ለመንደል የውስጥ ኣርበኞች መሆን ኣለባቸው። ለለውጥ መነሳት ኣለባቸው።የተባበረችውን ኢትዮጵያን ለመገንባት ትውልዱ ሁሉ ኣምርሮ መነሳት ኣለበት።የተባበረችውን ኢትዮጵያን የምንገነባው ደግሞ ከብሄር ፖለቲካ ስንወጣ፣ ስምምነት ውስጥ ስንገባ ነው። ይህ ስምምነት የህዝብ ውክልና በሌላቸው በዚህ ኣርባ ኣመት ባፈራናቸው እዚህም እዚያም በተኮለኮሉ ፓርቲዎች መካከል ኣይደለም። ወደ ባህላዊ ቡድኖች ታች ድረስ ወርዶ ህዝቡ ተወያይቶ ቁሳዊና መንፈሳዊ ባህሉን ኣዋጥቶ ኣገሩን እንዲገነባ የሚያደረግ ሰፊ ስምምነት ነው።ለዚህ ደግሞ ኣገሪቱ የሆነ የጽሞናና የሽግግር ጊዜ የሚያስፈልጋት ሲሆን በዚህ ከፍተኛ ኣሳብ ላይ ሁሉም መጠቅለል ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ህወሃት የዘራው ዘር ከፍተኛ ኣደጋ ውስጥ ሊጥለን ይችላል።
ኣዲሲቱ የተባበረችው ኢትዮጵያ ከብሄር ፖለቲካ ወጥታ በተሻለ ውቅር ልትሰራ ይገባል። የማንነት ኪሳራ እንዳይመጣብን በኣንድ በኩል የተደራጀ የባህል መንግስት መስርተን ባህላችንን እየተንከባከብንና እየተደሰትን በሌላ በኩል ፖለቲካዊ ቤት መስራት እንችላለን። እንደ ኢትዮጵያ ብዙ መልካም ታሪክና ባህላዊ እሴቶች ያሉዋትን ኣገር ለማስተዳደር የዚህ ዓይነት ሲስተም መዘርጋቱ ሰላምን፣ ልማትና ዴሞክራሲን ያፋጥንልናል። ከዚህም በላይ ለዜጎች ርካታን ይሰጣል።
ከልጅነት ጊዜየ ጀምሮ በእድሜ የበሰሉ ሰዎች የሚሰጡት ትምህርት ይማርከኝ ነበር። ኣረጋውያን ሲያወሩ ጠጋ ብሎ ማዳመጥ ርካታን ይሰጠኛል። ከእለታት ኣንድ ቀን እንዲሁ ኣንድ የእድሜ ባለጸጋ ኣገኘሁና በተፈታ ስሜት ወግ ጀመርን። እኚህ ሰው ከሚናገሩት የሚበዛው ያለፈው ዘመን ምን ያህል የተሻለ እንደነበር ነው። ምን ኣልባት በኢኮኖሚ ጥንት የተሻሉ ነበሩ ማለት ነው፣ ኣሁን ኑሯቸው ኣሽቆልቁሏል ማለት ነው፣ ብየ እንዳላስብ ኣይደለም። ልጆቻቸው የተሻለ ገቢ ኣላቸው። እሳቸውም ድሃ የሚባሉ እንዳይደሉ ኣውቃለሁ። ምንድነው ወደ ኋላ የሚጎትታቸው? ምን ኣጥተው ነው? የሚል ጥያቄ ይዞኝ ነበር። በሳቸው የልጅነት ጊዜ በእግር ነበር ይጓዙ የነበሩት፣ ኣሁን በመኪና ይሄዳሉ፣ የተሻለ ልብስ ፣ የተሻለ ጫማ፣ የተሻለ ምግብ፣ የተሻለ ነገር…. እንዳላቸው መረዳት ችያለሁ። እኚህ ሰውም ይህንን ሁሉ ይደሰቱበታል። ይሁን እንጂ ያጡት ነገር ደግሞ ወደ ሁዋላ ሲጎትታቸው ኣየሁና ሁዋላ ላይ ለራሴ የተረዳሁት ነገር እኚህ ሰው ያጡት ባህል ነው ማለት ነው ብየ ደመደምኩ። በለውጥ ስም የሚወዱዋቸውን ባህሎቻቸውን ኣጥተዋል። ኣንቱ የተባሉ ሽማግሌዎችን ከሰፈራቸው ኣያዩም፣ ክብረ በዓላትን ሲያዩ ይገረማሉ፣ የጠፉ ባህላዊ ተቋማት ይናፍቋቸዋል፣ ወዘተ።
እኚህ ሰው ዘመናዊውን ዴሞክራቲክ የሆነ መንግስት ማየት ይፈልጋሉ። በርግጥ ደግሞ ባህላዊ ተቋሞቻቸው ቢያንስ ከነ ሙሉ ሃይላቸውም ባይሆን በቅርስነት በህይወት ማየት እንደሚፈልጉ ተማርኩ። እኚህ ሰው ኢትዮጵያን ቢወዱም ኣገራቸው የድሮ ሞገሷን የተገፈፈች ኣድርገው እንደሚያስቡ ገመትኩ። ርግጥ ነው ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ባህልን ማጣት እንደ ሃገርም እንደ ዜጋም ይከነክናል ይጎዳልም።ሌሎች የኢኮኖሚ ህይወታቸው እያደር እየደቀቀ የመጣ ሰዎችም እንዲሁ የድሮውን ጊዜ ሲናፍቁ ብዙ ጊዜ እሰማለሁ። ጥያቄያቸው ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ባህላቸውንም እንደናፈቁ መረዳት ይቻላል።
ለዚህ ነው ኣዲሲቱ ኢትዮጵያ የተደባለቀውን ፖለቲካዊ ማንነትና ባህላዊ ማንነት በመለየትና በተለያየ ቤት እንዲያድሩ በማድረግ የተሻለ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋታል የሚያስብለን ። የተባበረችውን ኢትዮጵያን የምንመሰርተውም እንዲህ በጠነከረ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መሰረት ላይ መሆን ኣለበት። ለዴሞክራሲ፣ ለለውጥ የምናደርገው ትግል ሁሉ Je Suis ኢትዮጵያ መርሃችን ኣድርገን የተባበረችውን ኢትዮጵያን እንገንባ። ኢትዮጵያውያን የተባበረችውን ኢትዮጵያን ገንብተን ትኩረታችንን ሁሉ በምግብ ዋስትና ላይ ልናደርግ ይገባናል። ተመልከቱ እስቲ። ኢትዮጵያ ባለፉት ኣስር ኣመታት ያለማቋረጥ በጥንድ ቁጥር እያደገች ነው ተባለ። ጠቅላይ ሚንስትሩ በቅርብ ጊዜ ኢትዮጵያ በምግብ በብሄራዊ ደረጃ ራሷን ቻለች ኣሉ።
እነሆ በማግስቱ ዛሬ በጥቂት ወራት ውስጥ ለ4.5 ሚሊዮን ህዝብ ኣስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋል ተባለ። የተባበሩት ህዝቦች ድርጅት የሰባዊ መብት ኣጋር ድርጅትና መንግስት ይህን ገልጸዋል። በእኔ እምነት ይህም ይፋ የሆነው በተባበሩት ህዝቦች ድርጅት ቅስቀሳ እንጂ መንግስት ይህ ነገር ወደ ኣደባባይ ሳይወጣ የሆነው ቢሆን የሚመርጥ ነው የሚመስለኝ። የሚገርመው ዛሬ በብሄራዊ ደረጃ ራሳችንን በምግብ ቻልን ያሉን ጠቅላይ ሚንስትር ለተራቡ ሰዎች ቀለብ ለመግዛት ከሚያስፈልገው ተጨማሪ $230 ሚሊዮን ውስጥ $33 ሚሊዮን የሚሆነውን ብቻ ነው መንግስት መሸፈን የሚችለው። ቀሪውን 200 ሚሊዮን ገደማ ዶላር ባስቸኳይ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ርዳታ እንዲያደርግ ልመና ጀምረናል። ይህ ማለት ደግሞ በምግብ በብሄራዊ ደረጃ ራሳችንን ኣልቻልንም ነበር ማለት ነው። ለብዙ ዓመታት በጥንድ ቁጥር ኣድጊያለሁ ዓለም ያጨብጭብልኝ ስትል የነበረች ኣገር ዛሬ ለጥቂት ወራት እንኳን ዜጎቿን መታደግ ኣልቻለችም። ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብስ ምነው ዛሬ ጠዋት በምግብ ራሳችንን ቻልን ብልችሁ የለም እንዴ? ቢለን ……ያሳፍራል። ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች በውነት ኣጃንዳቸው ሁሉ ይህ ነው ሊሆን የሚገባው። ይህቺን ኣገር በምግብ ራስዋን የማስቻል ስራ ነው መቅደም ያለበት። ሰው በሚራብበት ኣገር የብሄር ፖለቲካ ቅብጥርሴ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው። ለውጥና ሪፎርሜሽን ይመግበናል፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮቻችንን ይፈታልና ለለውጥ ታጥቀን እንነሳ።
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
geletawzeleke@gmail.com
Source: goolgule
No comments:
Post a Comment