ከነሐሴ 16 እስከ ነሐሴ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ለመጀመርያ ጊዜ በተካሄደው የሰማያዊ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ ፓርቲውን ለመጪዎቹ ሦስት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ በድጋሚ የተመረጡት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፣ ያዋቀሩትን አዲስ ካቢኔ መስከረም 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ለብሔራዊ ምክር ቤቱ አቅርበው አፀደቁ፡፡
ብሔራዊ ምክር ቤቱ ያፀደቀው አዲስ ካቢኔ በአብዛኛው አዳዲስ አባላትን ያካተተ ሲሆን፣ ከቀድሞው ካቢኔ አባላት መካከል የተካተቱት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ዮናታን ተስፋዬ ብቻ ናቸው፡፡
ፕሬዚዳንቱ ለብሔራዊ ምክር ቤቱ አሥር የካቢኔ አባላትን እንዲያፀድቅላቸው አቅርበው ምክር ቤቱ የሰባቱን ዕጩዎች ምርጫ ሲያፀድቅ፣ ለሁለት አባላት ድምፅ እንዳልሰጠና አንድ ዕጩ ደግሞ ራሳቸውን ከዕጩነት እንዳገለሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከምክር ቤቱ ድምፅ ያላገኙት ሁለቱ የካቢኔው ተጠቋሚ አባላት የፋይናንስ ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት አቶ ወረታው ዋሴና የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት አቶ እያስፔድ ተስፋዬ ሲሆኑ፣ ራሳቸውን ከዕጩነት ያገለሉት ደግሞ የፓርቲው የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ስለሺ ፈይሳ ናቸው፡፡
በዚህም መሠረት አቶ ነገሰ ተፈረደኝ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ አቶ ዮናታን ተስፋዬ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ አቶ አበበ አካሉ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ፣ አቶ ጋሻው መርሻ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፣ ወይዘሮ መዓዛ መሐመድ የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ፣ አቶ እስክንድር ጥላሁን የጥናትና ስትራቴጂ ኃላፊ፣ እንዲሁም አቶ አዲስ ጌታነህ የሕግ ጉዳይ ኃላፊ ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት አቶ ነገሰ ተፈረደኝና የውጭ ግንኙነት ኃላፊው አቶ አበበ አካሉ ከቀድሞው አንድነት ፓርቲው የተቀላቀሉ አባላት ናቸው፡፡
የደኅንነትና የአባላት ክትትል ኃላፊ ሆነው እንዲያገለግሉ በዕጩነት ቀርበው የነበሩት ፓርቲውን በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ስለሺ ፈይሳ፣ ዕረፍት በመፈለግና ለሌሎች ዕድል ለመስጠት ሲሉ ራሳቸውን ከዕጩነት ማግለላቸውን አቶ ዮናታን አስረድተዋል፡፡
ከዕጩነት ራሳቸውን ያገለሉት አቶ ስለሺ ‹‹ሰማያዊ የወጣቶች ፓርቲ ነው፡፡ ስለዚህ እኔ ለወጣቶች ሥፍራውን ብለቅና በምክር ቤቱ ውስጥ በንቃት ብሳተፍ የተሻለ ይሆናል በሚል ራሴን ከዕጩነት አግልያለሁ፤›› በማለት ምክንያታቸውን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
የፋይናንስ ጉዳይ ኃላፊ ሆነው ፓርቲውን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ወረታው ዋሴን በተመለከተ፣ ‹‹ምንም እንኳን በአዲሱ ካቢኔ እንዲካተቱ ዕጩ ሆነው በፕሬዚዳንቱ አማካይነት ቀርበው የነበረ ቢሆንም፣ ምክር ቤቱ ድምፅ ስላልሰጣቸው አልተመረጡም፤›› ሲሉ አቶ ዮናታን አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ ድምፅ ሳያገኙ የቀሩት የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት የአቶ እያስቤድ ተስፋዬ ጉዳይ በእንጥልጥል ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዝርዝር ጉዳዩን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
ከካቢኔ አባላት በተጨማሪ ብሔራዊ ምክር ቤቱ የፓርቲውን የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ የመረጠ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት አቶ አበራ ገብሩ ሰብሳቢ፣ አቶ ሳምሶን ገረመው ምክትል ሰብሳቢ፣ አቶ ኃይለ ገብርኤል አያሌው ደግሞ ጸሐፊ ሆነዋል፡፡ አቶ ብርሃኑ መሰለና አቶ ሀብታሙ ደመቀ የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ አባላት በመሆን ተመርጠዋል፡፡
Source: Ethiopian Reporter
No comments:
Post a Comment