‹‹የደበደበኝና የዘረፈኝ ሰው ተለቆ እኔ ታስሬያለሁ›› አቶ ጌትነት በሱፍቃድ
በወላይታ ዞን ቦሎቶሶሬ ወረዳ አረካ ከተማ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የሆኑት አቶ ጌትነት በሱፍቃድ ተደብድበው ንብረቶቻቸውን መዘረፋቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ በምርጫው ወቅት ቅስቀሳ ላይ እያሉም በገዥው ፓርቲ ካድሬዎች ተመሳሳይ ወንጀል ተፈፅሞባቸው እንደነበር የገለፁት አቶ ጌትነት ‹‹በምርጫው ወቅት ቅስቀሳ ላይ እያለሁ በካድሬዎች ተደብድቤ ንብረቴን ተቀምቻለሁ፡፡ ሌሎች የትግል ጓደኞቼም ተመሳሳይ ወንጀል ተፈፅሞባቸዋል፡፡ ሆኖም ከፖሊስ ጣቢያ ጀምሮ እስከ ከንቲባው ፅ/ቤት ድረስ በመሄድ አቤቱታ ብናቀርብም የሚሰማን አላገኘንም፡፡›› ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
በቦሎቶሶሬ ወረዳ የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ጌትነት በሱፍቃድ ከሰማያዊ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳትፈው ከተመለሱ በኋላ ነሃሴ 20/2007 ዓ.ም በአረካ ከተማ ተመሳሳይ ወንጀል እንደተፈፀመባቸው ገልጸዋል፡፡ ደብድቦ ስልካቸውንና የአንገት ሀብላቸውን የቀማቸው ሰው እጅ ከፍንጅ ከተያዘ በኋላ ስልካቸው በፖሊስ እንደተመለሰላቸው የገለፁት አቶ ጌትነት እሳቸው ታስረው እስከ ሌሊቱ 5 ሰዓት ሲቆዩ ወንጀሉን የፈፀመው ሰው ወዲያውኑ መለቀቁን ገልጸዋል፡፡
‹‹የደበደበኝና የዘረፈኝ ሰው ተለቆ እኔ ታስሬያለሁ፡፡ የደበደበኝ ሰው ካድሬ ነው፡፡ ጭራሹን ለፖሊስ ለመክሰስ በሄድኩበት ወቅት ‹እሱም ሊከስህ ስለሆነ አንተም መክሰስ የለብህም፡፡ እንዳትካሰሱ ብለን መዝገቡን ዘግተነዋል› ብለው መልሰውኛል›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የትውልድ ቦታ በሆነው አረካ ከተማ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ ከፍተኛ በደል እንደሚፈፀም በተደጋጋሚ የሚገለፅ ሲሆን አቶ ጌትነትም ‹‹የሚደርሰው በደል ከፍተኛ ነው፡፡ ባለፈውም ለተፈፀመብን አሁንም ለተፈፀመብኝ ወንጀል መፍትሄ አልተሰጠኝም፡፡ ለአንድ ሰው ካድሬዎች በመንጋ መጥተው ነው የሚያጠቁህ፡፡ አቤት የምትልበት አካል የለም›› ሲሉ ገልጸውልናል፡፡
No comments:
Post a Comment