በፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ላይ በተፈጸመው አምባገነናዊ የጭካኔ እርምጃ
ከትግላችን አናፈገፍግም!
ሰማያዊ ፓርቲን ጨምሮ ዘጠኝ ትብብር የፈጠሩ ፓርቲዎች በህዳር ወር ያወጡት መርሐ ግብር አንድ አካል የሆነውን የ24 ሰዓት የተቃውሞ የአደባባይ ሰልፍ ለመተግበር ሥራ ላይ የነበሩ አመራሮች፣ አባሎቻችና ደጋፊዎቻችን ላይ አምባገነኑ ስርዓት በወሰደው የግፍ እርምጃ ምክንያት ከፍተኛ ድብደባ ደርሶባቸው በጨለማ ክፍል ውስጥ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
እስረኞቹ በጨለማና ቀዝቃዛ ክፍል፣ አንድ ራሱን ‹‹መንግስት ነኝ›› የሚል አካል ‹‹እስር ቤት›› ብሎ ዜጎችን ሊያጉርበት ይችላል ተብሎ የማይጠበቅ ሽንት ቤትና ጋራዥ ውስጥ መታሰራቸው አልበቃ ብሎ በቤተሰብ እንዳይጠየቁ ተደርገዋል፡፡ በድብደባው ምክንያት ራሳቸውን የሳቱና ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው አመራሮቻችን፣ አባላትና ደጋፊዎቻችን የህክምና አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም፡፡ አገዛዙ ይህን ሁሉ ግፍ የሚፈጽመው ለሰላማዊ ታጋዮች ባለው ጥልቅ ጥላቻና ጭካኔ በተሞላበት እርምጃው ከትግሉ ያፈገፍጋሉ ከሚል ስሌት ነው፡፡
ሆኖም እኛ ወደ ወደ ትግሉ ስንገባ ትግሉ ምን ያህል መስዋዕትነት እንደሚያስከፍል በሚገባ እናውቀዋለንና በየትኛውም መንገድ ስልጣኑን ለማስጠበቅ የሚጥረው ህወሓት/ኢህአዴግ መሰል የጭካኔ እርምጃ እንደሚወስድ የምንጠብቀው ነው፡፡ በመሆኑም አገዛዙ የወሰደውና ወደፊትም ሊወስደው የሚችለው ከዚህ የባሰም አረመኔነት የተሞላበት እርምጃ ይበልጡን ያጠናክረናል እንጅ ከትግላችን ቅንጣት ያህል ወደኋላ እንድናፈገፍግ የሚያደርገን አለመሆኑን መግለጽ እንወዳለን፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ አከብረዋለሁ እያለ ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ የሚጠቀምበትን ህገ መንግስት ራሱ እየናደው ‹‹ጅራፍ ራሱ ገርፎ..›› እንዲሉ ህገ መንግሥታዊ መብታቸውን በመጠቀም ህጋዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የነበሩ አመራሮቻችን፣ አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን ላይ ‹‹ህገ መንግስቱን በመናድ›› የሚል ክስ አቅርቦባቸዋል፡፡ የሰልፉን ተሳታፊዎች ደብድቦና አፍሶ ባሰረበት ወቅት ‹‹ምንም ችግር ሳይፈጥሩ በቁጥጥር ስር ውለዋል›› እንዳላለ ከስርዓቱ ቁጥጥር ያልወጣው የህግ አካል ‹‹መስቀል አደባባይ ላይ ንብረት ወድሟል፡፡›› በሚል ሌላ ክስ አቅርቧል፡፡ ስርዓቱ ፓርቲያችንና ትብብሩ በጀመረው ሰላማዊ ትግል በመደናገጡ የሚይዘው የሚጨብጠው እንዳጣ ህወሓት/ኢህአዴግ የሚዘውራቸው ተቋማት የተለያየ የፈጠራ ክስና ዘገባ ማቅረባቸው ዋነኛ ማሳያ ነው፡፡
ምክር ቤቱ ፓርቲያችን በሚያደርጋቸው ቀጣይ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ተገቢውንና አስፈላጊውን ውሳኔ እንደሚሰጥ መግለጽ ይወዳል፡፡ በዚህ የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ውስጥ ግምባር ቀደም የሆኑ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎችን ጨምሮ በአሁኑ ሰዓት በእስር ለሚገኙና የህወሐት/ኢህአዴግ የግፍ ሰለባ ለሆኑ ጓዶቻችንና የትግል አጋሮቻችን ሁሉ ያለንን አክብሮት ስንገልጽ ምን ጊዜም ከጎናቸው እንደሆንንና ሰላማዊ ትግሉ በበለጠ ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በማረጋገጥ ነው፡፡
ስለሆነም በሀገራችን ህዝባዊ ሥርዓት ለማምጣትና በህግ የበላይነት የሚያምን መንግስት ለመመስረት በምናደርገው ትግል ሁሉ የሚጠበቅብንን መስዋእትነት ለመክፈልና ሀገራዊ ግዴታችንን ለመወጣት ዝግጁ መሆናችን እየገለጽን መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀንለትና የምናከብረው ህዝብ ከጎናችን እንዲቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት
ህዳር 30/2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ
ኑ! ራሳችንን ነጻ በማውጣት የሀገራችንን እጣ ፈንታ እንወስን!!!
No comments:
Post a Comment